ቻይና ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መሾሟን ይፋ አደረገች

China Flag

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና በግጭት እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለተወጠረው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ልዩ መልዕክተኛ ሾመች።

አንጋፋው ዲፕሎማት ዡ ቢንግ የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።

ዡ በቅርቡ በፓፓዎ ኒው ጊኒ የቻይና አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በአፍሪካ፣ በአሜሪካ እና በኦሺኒያ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገራቸውን ስለማገልገላቸው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ በቅርቡ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ቻይና ለቀጠናው ልዩ መልዕክተኛ እንደምትሾች አስታውቀው ነበር።

ቤጂንግ በምሥራቅ አፍሪካ ሰፊ የሆነ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች አላት። ቻይና በጂቡቲ ግዙፍ የባሕር ኃይል ሰፈር አላት።

ከዚህ በተጨማሪም ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ለሚገኙ አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ከመስጠቷ በተጨማሪ በአገራቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ታከናውናለች።

በኢትዮጵያ ያለው የእርስ በእስር ጦርነት፣ የደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ አለመረጋጋት እንዲሁም የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ለቀጠናው ደኅንነት ፈተና የሆኑ ጉዳዮች ናቸው።

በአፍሪካ ቀንድ ባሉ አገራት ያለው አለመረጋጋት ያሳሰባቸው ኃያላን መንግሥታት ልዩ መልዕክተኞቻቸው ወደ አፍሪካ ቀንድ እየላኩ ይገኛሉ።

በቅርቡ አሜሪካ የሾመቻቸው አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድን በተሰናባቹ አምባሳደር ፌልትማን መተካታቸው ይታወሳል።

የአፍሪካ ሕብረትም የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጎ በመሾች የቀጠናውን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል።

በተመሳሳይ የአውሮፓ ሕብረት እና ሩሲያ የየራሳቸውን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሾመዋል።