ቀጣይ የምድራችን የህዋ ኃያል ለመሆን የተቃረበችው ቻይና

ህዋ እና የቻይና ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, BBC; Getty Image; Nasa

ቻይና አዲስ የጠፈር ጣቢያ አቋቁማለች። ሦስት ጠፈርተኞችም ጓዛቸውን ሸክፈው ለስድስት ወራት ወደ ጣቢያው አምርተዋል።

የእነማኦ አገር በቀጣይ ዓመታት በዘርፉ ከፊት መገኘት ነው ዕቅዷ። ሦስቱ ጠተፈርተኞችም የዚሁ ህልም አካል ናቸው።

የቲያንጎንግ የጠፈር ጣቢያ ምንድን ነው?

ቲያንጎንግን "የሰማይ ቤተ መንግሥት" እንደማለት ነው። ቻይና ባለፈው ዓመት ነው ወደ የመጀመሪያውን የህዋ ማዕከል ያቋቋመችው። ከዚህ የህዋ ምርምር ማዕከል በተጨማሪ ሜንግቲያን የተባለ እና ሌላም የሳይንስ ቤተሙከራዎች ይከተላሉ።

በቀጣይነትም ዡንተቲያን የተሰኘ ቴሌስኮፕ ሥራ የሚጀመር ሲሆን፣ ይህም ከጠፈር ጣቢያው በቀርብ ርቀት ላይ በመሆን ለጥገና እና ለነዳጅ ለመሙላትም ያግዛል።

ቲያንጎንግ የራሱ ኃይል ማግኛ ዘዴ የተገጠመለት ነው። ሕይወትን ለማቆየት የሚያስፈልጉ ሥርዓቶች እና የመኖሪያ ስፍራም ይኖረዋል።

ቻይና ሁለት ጠፈርተኞች ወደ ህዋ ልካ የጠፈር ጣቢያን የገነባች ሦስተኛዋ አገር ናት። ሶቭየት ሕብረት (አሁንም ሩሲያ ደግማዋለች) እና አሜሪካ ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ይህ ቻይና ቲያንጎንግ ላይ ያላት ትልቁ ህልም ነው። እአአ በ2031 ከሥራ ውጪ እንደሚሆን ቀነ ገድብ የተቀመጠለትን ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ (አይኤስኤስ) እንደሚተካ ተስፋ ተጥሎበታል።

ቻይና ለምን በህዋው መስክ ቀዳሚ ለመሆን አቀደች?

የቻይና እና የአሜሪካ ሽኩቻ እዚህም አለ። የቻይና ጠፈርተኞች ከዓለም አቀፉ የጠፈር ማዕከል ተገልለዋል። ምክንያት ከተባለ የአሜሪካ ሕግ ነው። ሕጉ የህዋ ድርጅቷ ናሳ መረጃ ለቻይና እንዳያጋራ ይከለክላል።

ቻይና ወደ ጨረቃ እና ማርስ ለመድረስ ታልማለች። ምኞቷ በዚህ ብቻ አያበቃም።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ በመሬት አቅራቢያ ከሚገኙት አስትሮይዶች ናሙናዎችን መሰብሰብ ትፈልጋለች።

እአአ በ2030 የመጀመሪያዎቹን ጠፈርተኞቿን ወደ ጨረቃ ለመላክ አቅዳለች። ከማርስ እና ጁፒተር ናሙናዎችን መሰብሰብም ሌላው ውጥኗ ነው።

ቲያንጎንግን "የሰማይ ቤተ መንግሥት" የህዋ ማዕከል በህዋ ላይ የሚኖራት ገጽታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቲያንጎንግን "የሰማይ ቤተ መንግሥት" የህዋ ማዕከል በህዋ ላይ የሚኖራት ገጽታ

ሌሎች አገራትስ ምን እየሠሩ ነው?

ቻይና በህዋ ላይ ያላትን ሚና ታሰፋለች። በተመሳሳይ በርካታ አገራትም ወደ ጨረቃ የመድረስ ዓላማ አላቸው።

ናሳም ከ2025 ጀምሮ ከአሜሪካ እና ከሌሎች አገራት ጠፈርተኞች ጋር ወደ ጨረቃ ለመመለስ አቅዷል።

አዲሱን ግዙፍ የኤስኤልኤስ ሮኬት በኬኔዲ የጠፈር ማዕከል ይፋ አድርጓል።

ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሩሲያ፣ ሕንድና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስም በየራሳቸው ተፍ ተፍ እያሉ ነው።

ሕንድ ከወዲሁ ሁለተኛውን የጨረቃ ተልዕኮዋን ይፋ አድርጋለች። በ2030 የራሷ የጠፈር ጣቢያ እንዲኖራትም ታልማለች።

የአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ ከናሳ ጋር በጨረቃ ተልዕኮ ላይ ይሠራል። ኤጀንሲው የጠፈር ተመራማሪዎች መሬት ካሉ ባለሙያዎች ጋር በቀላሉ እንዲገናኙ የሚያግዙ የጨረቃ ሳተላይቶችን በመዘርጋት ላይ ይገኛል።

የህዋ ሕግጎን ማን ያወጣል?

  • እአአ በ1967 የተደረሰው የተባበሩት መንግሥታት የጠፈር ስምምነት እንደሚለው የትኛውም የጠፈር ክፍል በየትኛውም አገር ባለቤትነት አይያዝም።
  • እአአ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የጨረቃ ስምምነት ተደረሰ። ስምምነቱ እንደሚለው ከሆነ ጠፈር ለገበያ ቀርቦ ሊበዘበዝ አይገባም ይላል። ቻይና፣ አሜሪካ እና ሩሲያ ግን ፊርማችንን አናኖርም ሲሉ ራሳቸውን አግልለዋል።
  • አሜሪካ አገራት የጨረቃን ማዕድን በትብብር እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ የሚገልጽ ስምምነት እያስተዋወቀች ነው።
  • ሩሲያ እና ቻይና ስምምነቱን እምቢኝ ብለዋል። ምክንያቱ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ሕግን የማውጣት መብት ማን ሰጣት የሚል ነው።
የቻይና የህዋ መንኮራኩር ማስወንጨፊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና የህዋ መንኮራኩር ማስወንጨፊያ

ቻይና በህዋ ዘርፍ ምን ታሪክ አላት?

1970 ለቻይና ታሪካዊ ዓመት ነው። የመጀመሪያውን ሳተላይት ወደ ህዋ የላከችበት ዓመት። ወቅቱ ባካሄደችው የባህላዊ አብዮት ሳቢያ ከፍተኛ ምስቅልቅ ውስጥ የባችበት ጊዜ ነበር።

በወቅቱ አራት አገራት ብቻ ናቸው ወደ ህዋ የደረሱት እነሱም፤ አሜሪካ፣ ሶቭየት ሕብረት፣ ፈረንሳይ እና ጃፓን።

ባለፉት 10 ዓመታት ቻይና ከ200 በላይ ሮኬቶችን አምጥቃለች።

የድንጋይ ናሙናዎችን ለመሰብሰብ ቻንግ 5 የተባለ ሰው አልባ መንኮራኩር ወደ ጨረቃ ልካለች። የቻይና ሰንደቅ ዓላም በጨረቃ ከፍ ብሎ ተውለብልቧል። ሰንደቁ ሆን ተብሎ ቀድሞ ከተተከሉት የአሜሪካ ባንዲራዎች የበለጠ ነበር።

ቻይና 13 ጠፈርተኞቿ ህዋ ደርሰዋል። ይህንን ከሁለቱ ተቀናቃኞቿ ጋር እናነጻጽረው። የዩናይትድ ስቴትስ 340 ናቸው። የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት (የአሁኗ ሩሲያ) ከ130 በላይ ናቸው።

ቻይና በዚህ ጥረቷ ሁሉም ነገር ግን አልጋ በአልጋ አልሆነላትም። እአአ በ2021 አንድ የቻይና ሮኬት ተሰብሮ ከህዋ ወድቆ መቃብሩ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ሆኗል። በ2020 ሁለት የማስወንጨፍ ሙከራቿ ከሽፈውባታል።

የቻይና የህዋ ፕሮግራም ወጪ በማን ይሸፈናል?

የቻይና መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው ዢኑዋ የተሰኘው መገናኛ ብዙኃን ቢያንስ 300,000 ሰዎች በቻይና የጠፈር ፕሮጄክቶች ላይ ሠርተዋል ይላል። ይህ ቁጥር አሁን ለናሳ ከሚሠሩት በ18 እጥፍ ይበልጣል።

የቻይና ብሔራዊ የጠፈር ድርጅት እአአ በ2003 የተቋቋመ ነው። መነሻ ዓመታዊ በጀቱም ሁለት ቢሊዮን ዩዋን (300 ሚሊዮን ዶላር) ነበር።

እአአ በ2016 ደግሞ ቻይና የህዋ ኢንዱስትሪዋን ለግል ኩባንያዎች ከፈተች። እነዚህም ከ10 ቢሊዮን ዩዋን (1.5 ቢሊዮን ዶላር) በላይ ገንዘብ በማፍሰስ ላይ መሆናቸውን የቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

ቻይና ለምን ትኩረቷን ወደ ህዋ አዞረች?

ቻይና የሳተላይት ቴክኖሎጂዋን ለማሳደግ ትፈልጋለች። ዓላማዋ ለቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ለአየር ትራፊክ አስተዳደር፣ ለአየር ሁኔታ ትንበያ እና አሰሳ እና ለሌሎችም ዘርፎች ለማዋል ነው።

ብዙዎቹ ሳተላይቶቿ ወታደራዊ ዓላማዎችም አሏቸው። ተቀናቃኝ ኃይሎችንም ይሰልላሉ። የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ውጤታማነትንም ሊረዱ ይችላሉ።

በፖርትመዝ ዩኒቨርሲቲ የህዋ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሉሲንዳ ኪንግ እንደሚሉት ቻይና በከፍተኛ ደረጃ የህዋ ተልዕኮዎች ላይ ብቻ አላተኮረችም። "በሁሉም የሕዋ ዘርፍ ምርጦች ናቸው። የታቀዱ ፕሮግራሞቻቸውን በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችል ፖለቲካዊ ተነሳሽነት እና ሃብት አላቸው" ይላሉ።

የቻይና የጨረቃ ጉዞ ሌላም ተልዕኮዎች አሉት። እንደ ሊቲየም ያሉ ብርቅዬ ብረቶችን ማግኘት ነው።

ፕሮፌሰር ሰኢድ ሞስቴሻር በለንደን ዩኒቨርሲቲ የለንደን የጠፈር ፖሊሲ እና ሕግ ተቋም ዳይሬክተር ናቸው። ቻይና ተደጋጋሚ የማዕድን ፍለጋ ለማድረግ ወደ ጨረቃ መጓዟ አትራፊ ላይሆን ይችላል ሲሉ ፕሮፌሰሩ ይሞግታሉ።

የቻይና የጠፈር መርሃ ግብር ሌላ ዓላማ ያለው ነው ይላሉ። ዓላማው ምን ይሆን ከተባሉ ደግሞ የተቀረውን ዓለም ማስደመም ያለው ፍላጎት ነው ይላሉ። በአጭሩ “የፈርጣማነት እና የቴክኖሎጂ ዕድገት ማሳያ ነው።”