ሩሲያዊው ጋዜጠኛ የኖቤል ሜዳሊያ ሽልማቱን ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሸጠ

ዲሚትሪ ሙራቶቭ

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY Images

በሩሲያ ነጻ ጋዜጣ የሚባለው ኖቫያ ዋና አዘጋጅ የሰላም ሽልማቱን በ103.5 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ ሽጧል።

ዲሚትሪ ሙራቶቭ እንደተናገረው ከሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ በሙሉ በዩክሬን ውስጥ በጦርነት ለተፈናቀሉ ስደተኞችን ለመርዳት ይውላል።

ሙራቶቭ በአውሮፓውያኑ 2021 በሩሲያ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን ለማስከበር ባደረገው ፅናት የሰላም ሽልማት ተሰጥቶታል።

ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎም ኖቫያ ጋዜጣ ሥራውን ለማቆም ተገዷል።

ሩስያ በዩክሬን የምታደርገውን ዘመቻ ጦርነት በሚል የገለጸ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ሚዲያ ከፍተኛ ቅጣት ወይም መዘጋት እንደሚጠብቀው ማስጠንቀቋን ተከትሎ ነው።

ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" በማለት ነው የምትጠራው።

የኖቤል የሰላም ሜዳሊያ ሽያጩን ያካሄደው ሄሪቴጅ የተባለው ድርጅት አሸናፊው ማን እንደሆነ አልገለጸም።

በሚያዝያ ወር ሙራቶቭ ሩሲያ ውስጥ በባቡር ተሳፍሮ በሚሄድበት ወቅት ቀይ ቀለም ተወርውሮበታል።

ቀለሙን የደፋበት ግለሰብ “ሙራቶቭ፣ ይህ ለልጆቻችን ነው” ሲልም ጮክ ብሎ ተናግሯል።

ጋዜጠኛው በአውሮፓውያኑ 1993 የሶቭየት ህብረት መውደቅን ተከትሎ ኖቫያ ጋዜጣን ከመሰረቱት የጋዜጠኞች ቡድን ውስጥ አንዱ ነበር።

በአመታት ውስጥ የምርመራ ዘጋቢ አና ፖሊትኮቭስካያን ጨምሮ የጋዜጣው ስድስት ጋዜጠኞች እና ተባባሪዎች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ተገድለዋል።

የወርቅ ሜዳሊያው በኒውዮርክ መሸጡ ዩኒሴፍ በዩክሬን ለተፈናቀሉ ህጻናት የሚሰጠውን ሰብዓዊ ምላሽ ይረዳል ሲል ሄሪቴጅ በመግለጫው አትቷል።

ሙራቶቭ በተቋሙ በተለቀቀው ቪዲዮ ላይ "ዛሬ በጣም አስፈላጊው መልእክት ሰዎች ጦርነት እንዳለ እንዲረዱ እና በጣም የሚሰቃዩ ሰዎችን መርዳት አለብን" ብሏል።

ባለፈው አመት የኖቤል የሰላም ሽልማትን በፊሊፒንስ ራፕለር የተባለውን ድረ-ገጽ ከመሰረተችው ጋዜጠኛ ማሪያ ሬሳ ጋር አሸንፏል።

ሁለቱም ጋዜጠኞች የአገሮቻውን መሪዎች በሰላ ሁኔታ በመተቸት እንዲሁም ለፕሬስ ነፃነት የሚታገሉ ምልክቶች ሆነዋል።