የሴቶችን እርቃን ፎቶ በመቸርቸር የሚተዳደሩት የኢኒስታግራም ቀማኞች

የእርቃን ምሥሎች በአደባባይ ይሸጣሉ

በርካታ ሴቶች ፈተና እየገጠማቸው ነው።

በተለይ ለእርቃን የቀረቡ ፎቶዎቻቸውን በኢኒስታግራም የሚያጋሩ።

የሴቶችን ከፊል እርቃን ፎቶ በመሥረቅ ቆርጠው-ቀጥለው የሚቸበችቡ ቀማኞች ተፈጥረዋል።

እነዚህ ቀማኞች ማንነታቸውን ማንም አያውቀውም።

ነገር ግን የየትኛዋንም ሴት ፎቶ መንትፈው፣ አበጃጅተው፣ ከፊል ራቁት የሆነውን ሙሉ እርቃን አድርገው ለገበያ ያቀርቡታል።

ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ የእርቃን ጉልት የሚገኘው ‘ሬዲት’ በሚባለው መድረክ ነው።

ሬዲት እንደ ፌስቡክና ትዊተር ያለ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነው። ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ የነበረ ነው።

የቢቢሲ ዘጋቢ ከነዚህ መንታፊዎች አንዱን ለማደን የሄደችበትን ርቀት እነሆ፦

በ5 ፓውንድ ሙሉ የእርቃን ፎቶ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“5 ፓውንድ ሙሉ እርቃን ፎቶ 5 ፓውንድ!” ቸርቻሪው ይጣራል። ታላቅ ቅናሽ ሙሉ እርቃን እያለ።

“ፎቶዎቿ ብቻ ሳይሆን የእርቃን ቪዲዮዎቿም አሉኝ” ይላል ደንበኞች ቀዝቀዝ ሲሉበት።

ይህ ሰው ዚፖማድ ይባላል። በሬዲት ከየሚታዩ የፎቶ ቸርቻሪዎች ውስጥ አንዱ ነው።

እርሱ በፈጠረው የጋራ ቡድን የአንዲት ሴት እርቃን ፎቶ ተለጥፎ ይታያል። በሌላ አነጋገር የዚች ሴት እርቃን ፎቶዋ ለጨረታ ቀርቧል።

ከፎቶዋ ሥር የተሰጡ አስተያየቶችን አሰቃቂነት ለመግለጽ ቃላት ጉልበት የላቸውም።

አንዱ አስተያየት ሰጪ ይቺን ሴት መድፈር እንደሚፈልግ የሚገልጽ ነው።

ይቺ ሴት ፎቶዋ ከኢኒስታግራም ተመንትፎ በዚህ ገጽ ተለጥፎ ነው ለጨረታ የቀረበው።

እነዚህ የእርቃን ፎቶዎች በተለያየ መንገድ ዚፓማድን በመሰሉ ቸርቻሪዎች እጅ ሊገቡ ይችላሉ።

አንዱና ዋንኛው መንገድ ታዲያ የሴቶቹ የቀድሞ ወንድ ፍቅረኞች ለበቀል አሳልፈው ስለሚሸጧቸው ነው።

በዚህ ገጽ ላይ የሴቶች እርቃን ፎቶ ብቻ አይደለም የሚገኘው። የሌሎች ሴቶችም የወሲብ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችም ይሸጣሉ።

ብዙዎቹ ለበቀል ያህል የሚፈጸሙ ይሆኑና ቀስ በቀስ ከቁጥጥር ይወጣሉ። ሻጩ በኋላ በድርጊቱ ሊጸጸትም ይችላል። ምን ዋጋ አለው፤ ምሥሉ በሌሎች ብዙ ሺህ ሰዎች እጅ ወድቋል፤ በሰከንድ ውስጥ።

ታዲያ ከነዚህ ጭምብል ካጠለቁ የእርቃን ፎቶ መንታፊዎች መሀል የተወሰኑት ባለ ፎቶዋ ማን እንደሆነች አፈላልገው የሚመጡ ናቸው።

የተወሰኑት ደግሞ ባለ ፎቶዋን በከፍተኛ ገንዘብ ይደራደሯታል። “ጥሩ ገንዘብ ክፈይና የእርቃን ፎቶውን እናንሳልሽ” ይላሉ።

ሬዲት በየቀኑ 50 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።

እንዲህ ዓይነት የእርቃን ፎቶዎችን ከገጹ ለማንሳት ዘለግ ያለ ጊዜን ይወስድበታል።

በዚህ ዓመት በርካታ የዝነኛ ሴቶች ፎቶዎች ወሲብ ሲፈጽሙ እንዲመስል ተደርገው ተቀናጅተው ቀርበው ነበር። ሌሎች ደግሞ የምርም ድርጊቱ ሲፈጸም በድብቅ የተቀረጹ ናቸው።

ይሁንና ሬዲት ገጽ እነዚህን ፎቶዎች ከገጹ ለማጥፋት ዘመን ወስዶበታል።

‘ዲፕፌክ’ ዘዴን በመጠቀም ዝነኛ ሴቶች ወሲብ እየፈጸሙ እንደሆነ አስመስለው የሚያዘጋጁት ሰዎችም አካውታቸው ተዘግቷል።

አይሻ
የምስሉ መግለጫ, አይሻ የእርቃን የወሲብ ምሥሉ ከወጣባት በኋላ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባታል

‘ራሴን ለማጥፋት ሞከርኩ’

ከተጋሩት ምሥሎች አንዱ እጅግ ባፈነገጠ ሁኔታ የሚፈጸም የወሲብ ምሥል ያለበት የአንዲት ሴት ፎቶ ይገኝበታል።

ከምሥሉ ሥር ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንዱ ‘የዚች ሴት ቪዲዮ ይኖራል?’ ሲል ጠየቀ።

‘ሙሉ አልበም አለኝ። 5 ፓወንድ ብቻ። በውስጥ መስመር አነጋግረኝ’ ሲል መለሰ የፎቶ ቸርቻሪው።

አይሻ (ስሟ ለዚህ ጽሑፍ የተቀየረ) ባለፈው ዓመት ነበር ቪዲዮዋ ሬዲት ላይ መውጣቱን ያወቀችው።

በወሲብ ላይ ሳለች በቀድሞ ፍቅረኛዋ በድብቅ እንደተቀረጸች ትገምታለች።

ሙሉ አገር ተነሳባት። ሙሉ ፓኪስታን አበደ።

ማንነቷ በየማኅበራዊ ሚዲያው ተጋራ።

አንድ ማንነቱ የማታውቀው ሰው “ገና ምን አይተሽ! ወሲብ ከእኔ ጋር ካልፈጸምሽ ሌሎች ቪዲዮዎችን አጋራለው” አላት።

“እምቢ ካልሽም ያለሽበት መጥቼ አንቺን መድፈር ነው የምፈልገው” ሲል ዛተባት።

በፓኪስታን ሴት ልጅ ከትዳር በፊት እንኳ ወሲብ መፈጸም አትችልም። ተቀባይነት የለውም።

አይሻ ከዚህ በኋላ ከቤት መውጣት ሁሉ አልቻለችም። የደረሰባት ውርደት ከቁጥጥር ውጭ ሆነ።

ራሷን ከማጥፋት ውጪ አማራጭ አልታያትም። ሙከራ ላይ ሳለች ተደረሰባት። ወላጆቿ ተገለሉ። በማኅበረሰቡ ተወገዙ።

“ከፍተኛ ውርደት የተሰማኝ ወላጆቼን በዚህ ነውር ውስጥ ማስገባቴን ስረዳ ነው” ትላለች።

አይሻ ይህ ቪዲዮዋ ለአደባባይ እንደተሰጣ ወዲያውኑ ለሬዲት አሳውቃ ነበር። እነሱም ያን ቪዲዮ አንስተውላታል።

ከአራት ወር በኋላ ግን በድጋሚ ወጣ። ድጋሚ የወጣውን ለማንሳት አራት ወራትን ወስዶባቸዋል።

ሆኖም ወደ ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያዎች ተዛምቶ ነበር።

የእርቃን ፎቶ ንግድ

ይህ የእርቃን ፎቶ ንግድ የሚደረገው በተወሰኑ ግሩፖች ውስጥ ነው። ነገር ግን ከፍተኛ የደራ ገበያ ያለው ነገር ነው።

ሬዲት ደግሞ የእርቃን ምሥሎችን ቅሬታ ሲቀርብበት ቶሎ አያነሳም።

ሰባት የእርቃን ፎቶዎቻቸው ያለፍቃዳቸው ተመንትፎባቸው የተጋራባቸው ሴቶች ይህንኑ መስክረዋል።

ሬዲት በበኩሉ ክፈተቱ እንዳለ አምኖ ነገር ግን ባለፈው ዓመት ብቻ 88ሺህ የእርቃን ፎቶዎችን ማስወገዱን ተናግሯል።

በዚህ የእርቃን ፎቶ ከሚተዳደረው አንዱ ዞፕሞድ ይባላል። ከስሙ ውጪ አድራሻውንና ማንነቱን የሚገልጽ ነገር በገጹ ላይ አይታይም።

ሆኖም የቢቢሲ ዘጋቢ የእርቃን ፎቶ ገዥ በመምሰል ልታገኘው ችላ ነበር።

“እኔ ሴቶችን ለመጉዳት ብዬ ይህን አላደረጉም” ሲል ጸጸቱን ከመግለጹም ባሻገር እሱ የፈጠረውን የእርቃን ፎቶ ገጽ አጥፍቶታል።

የእርሱ እውነተኛ ማንነት በሬዲት ገጽ እንደሚታየው አልነበረም። በድርጊቱም ከፍተኛ ጸጸት እንደተሰማው ገልጧል።

የቴክ ኩባንያዎችና ማኅበራዊ የትስስር መድረኩን የሚያስተዳድሩ ግዙፍ ኩባንያዎች ቸልታቸው እስከመቼ ነው? የሚለው አሁንም የሚያነጋግር ነው።

እንደ አይሻ የእርቃን ፎቶዋ እርቃን አደባባይ የወጣባት ጆርጂያ ይህን ያደረገባትን የቀድሞ ፍቅረኛዋን በተመለከተ ያላትን ሐሳብ ስትጠየቅ፤ “እኔ እሱን መበቀል አይደለም የምሻው፤ እኔ ይህን ጸያፍ ድርጊት በሌላ ሴት ላይ እንዳይደግመው ነው የምሻው” ትላለች።