ድል የራቃቸው ዩናይትድ እና ሊቨርፑል በተቃውሞ እና በጉዳት ታጅበው ተፋጠዋል

ሞ ሳለህ ጎል በዩናይትድ ላይ ካስቆጠረ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ ሊቨርፑልን ማሸነፍ አለበት።

ኃያሉ ሊቨርፑል ማንችስተርን ረትቶ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያውን 3 ነጥብ ማግኘት ይጠበቅበታል።

ከዚህ ፍጥጫ ሦስት ነጥብ መውሰድ የሚችለው ግን አንድ ክለብ ብቻ ነው።

በጋራ የሊጉን ዋንጫ 39 ጊዜ ያነሱት ባላንጣዎቸው የመጀሪያውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ዛሬ ምሽት ኦልድ ትራፎርድ ላይ ይገናኛሉ።

ሊቨርፑል በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከፉልሃም እና ክሪስታል ፓላስ ጋር አቻ ተለያይቷል።

የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን ደግሞ በብሬንትፎርድ እና ብራይተን አስደንጋጭ ሽንፈት ተከናንቧል።

ሊቨርፑል ወደ ድል ይመለስ ይሆን?

ከሁለቱ ቡድኖች የቅርብ ጊዜ አቋም አንጻር የምሽቱ ጨዋታ ለሊቨርፑል ወደ ድል ለመመለስ ምርጥ አጋጣሚ ነው።

ቀያዮቹ ባለፉት ስምንት የነጥብ ጨዋታዎች በማንቸስተር ሽንፈት አላስተናገዱም።

ማንቸስተር ሊቨርፑልን ያሸነፈው እአአ በ2018 ነው። ከዚያ በኋላ ቡድኑ ሁለት አሰልጣኞችን አባሯል። ክለቡ ሁለት ጊዜያዊ አሰልጣኞችን ከሾመ በኋላ ነው ኤሪክ ቴን ሃግን በቋሚነት የቀጠረው።

ሊቨርፑል ከ2002 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን ማንቸስተር ላይ ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ለሊቨርፑል አስጊ ሆነው ነገር ባለፉት ስድስት ሊጉ ጨዋታዎች ቀድመው ጎል አስተናግደዋል።

ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሮናልዶ አለመራጋጋት እና መጥፎ አቋም

ባለፈው ጥቅምት ሁለቱ ቡድኖች የተገናኙት ማንቸስተር በሌስተር 4 ለ 2 ከተሸነፈ በኋላ ነበር።

ከሳምንት በፊት በብሬንትፎርድ በተሸነፈው ቡድናቸው የበሸቁት የዩናይትድ ደጋፊዎች ከሊቨርፑል ጨዋታ በፊት ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።

የዘንድሮው ሽንፈትም የክለቡን የደጋፊዎች ማሕበር ጠንካራ መግለጫ እንዲያወጣ አስገድዶታል።

“ሁሌም እንደምነለው የአሳ ግማቱ ከአናቱ ነው የሚጀምረው። ለክለባችን መጥፎ አቋም ውስጥ መገኘት ተጠያቂው ባለቤቶቹ የግሌዘር ቤተሰቦች ናቸው” ብሏል።

ቡድኑ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ፣ ትይሬል ማላሲያ እና ክርስቲያን ኤሪክሰንን በቡድኑ አካቶ አሳልፎም አጫውቷል።

የሪያል ማድሪዱን ብራዚላዊውን አማካይ ካሲሚሮንም ለማስፈርም ተስማምቷል።

ቡድኑ ግን ካለፈው ዓመት የውጤት ቀውስ የተላቀቀ አይመስልም።

ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ብቻ አሳክተዋል። አንድ አሸንፈው አንድ አቻ ሲወጡ በቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል።

አጥቂው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከቅድመ ውድድር ዘመን ጨዋታዎች መቅረቱ ቡድኑን ሊለቅ ይችላል የሚሉ ግምቶች እንዲወጡ አድርጓል።

ሮናልዶ በመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ የተጫወተ ሲሆን ከብሬንትፎርድ ጋር ደግሞ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካቷል።

ከሊቨርፑል ጨዋታ በፊትም ፖርቹጋላዊው ስለሱ የሚቀርቡ በርካታ “ውሸቶችን”ተከትሎ “እውነታውን” በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

ዳርዊን ኑኔዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዳርዊን ኑኔዝ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተወገደ በኋላ

በጉዳት እና በቅጣት የተጎዳው ሊቨርፑል

የውድድር ዓመቱ ገና መጀመሩ ቢሆንም ሊቨርፑል ወደ ድል መመለስ ይጠበቅበታል።

አዲስ ፈራሚው አጥቂው ኑኔዝ በቀይ ካርድ ከጨዋታው ውጭ ሆኗል።

“ከኑኔዝ ጋር በተያያዘ 'በሂደት ላይ ያለ ሥራ' መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እሱም የሚረዳው በዚህ መልኩ ነው” ሲሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ሰኔ ላይ ተጫዋቹን ሲያስፈርሙ ተናግረው ነበር።

ኑኔዝ ቡድኑ ከበርንማውዝ እና ኒውካስል ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎችም ያመልጡታል።

ይህ ደግሞ ቲያጎ አልካንታራ፣ ዲያጎ ጆታ፣ ከርቲስ ጆንስ፣ ጆዬል ማቲፕ፣ ሮቤርቶ ፊርሚኖ፣ አሌክሰ ኦክስላዴ-ቻምበርሌይን እና ኢብራሂማ ኮናቴን ላጣው ቡድን ተጨማሪ ራስ ምታት ይሆናል።

“በጣም አስቸጋሪ ሳምንት ይሆንብናል። በየቀኑ ጉዳት ያጋጥመናል” ሲሉ ክሎፕ ገልጸዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በደጋፊዎች ተቃውሞ ምክንያት ሊራዘም ተገዷል። ተቃውሞው በግሌዘር ቤተሰቦች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ከጸጥታ አካላት በላይ በመሆኑ ነው ጨዋታው የተራዘመው።

በወቅቱ ማንቸስተር ለ13 ጨዋታዎች ባለመሸነፉ እና በአውሮፓ ሊግ አስከ ፍጻሜ በመጓዙ ብዙም ስጋት አልነበረም።

አሁን ግን ቡድኑ ከ50 ዓመት ወዲህ ታይቶት በማያውቀው የውጤት ቀውስ ውስጥ ይገኛል።

ከጨዋታው በፊት ተቃውሞ እንደሚኖር አስተባባሪዎች አሳውቀዋል።