አዲሱ ‘የማኅበራዊ ልማት ግብር’ ኑሮን ሊያስወድድብን ይሆን?

ግብር

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በዜጎቹ እየጨከነ ይመስላል፡፡ የሚያስጨክነው የኪሱ መመናመን ይሆናል፡፡

በቀደም ለምሳሌ የነዳጅ ድጎማን አነሳ፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ ቀረጥ ልጥልባችሁ ነው እያለ ነው፡፡ ይህ እየሆነ ያለው ግሽበቱ 33 ከመቶ በደረሰበት ጊዜ ነው፡፡

ይህ አዲስ ቀረጥ አስመጪዎች ላይ ብቻ የሚጣል ቢሆንም ቁንጥጫው እነርሱ ዘንድ ይቀራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

አስመጪዎች ምንም ነገር ሲጫንባቸው እንደ ትኩስ ድንች ወደ ሸማች ሲወረውሩት ነው የኖሩት፡፡

መንግሥት ‘ትኩሱ ድንች’ በነጋዴዎች አፍ እንዲቀር ለማድረግ ደግሞ መንገዱም፣ ስልቱም፣ መላውም የለውም፡፡

ከባድም ነው፤ ለቁጥጥር፡፡ ታዲያ ምን ተሻለ?

መንግሥትን ምን አስገደደው?

የምጣኔ ሃብት አዋቂዎች መንግሥት እንደ ዘንድሮ የተፈተነበት ዓመት የለም ይላሉ፤ በብዙ ምክንያቶች።

የሰሜኑ ጦርነት ዋነኛው ነው።

የኮቪድ ወረርሽኝ እና የዩክሬኑ ጦርነትን ተከታትሎ መምጣት ሌላው ነው። የነዳጅ ዋጋ መናር ደግሞ ሦስተኛው ምክንያት ነው፡፡

የሁሉም ሉላዊ ምስቅልቅ ጦሶች ዳፋቸው ለሁሉም ተርፏል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከማንም ቁጥጥር ውጪ መሆናቸው ነው ጉዳቱ፡፡

መፈናቀል እና የሰላም እጦት ምርት ያሳጣሉ። ምርት ማነስ ደግሞ ገቢን ይጎዳል።

በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ መንግሥት እጅ አጥሮታል፡፡

ከበጀት ጋር በተያያዘ ጠንከር ያለ ፈተና ገጥሞታል።

የዘንድሮ ዓመታዊ በጀት ከቀደመው በ100 ቢሊዮን ብር ገደማ ይልቃል። ጥቅሉ 800 ቢሊዮን ብር ተጠግቶ ነበር። ምን ዋጋ አለው፤ የበጀት ጉድለቱም ያን ያህል ሰፊ ሆነ።

መንግሥት ባመነው ከ200 እስከ 300 ቢሊዮን ብር የበጀት ክፍተት ይጠበቃል።

እርግጥ ነው የኢትዮጵያ በጀት ራሱን ችሎ አያውቅም፡፡ ሁሌም እርጥባን ይሻል፡፡ በድጎማ እና በእርዳታ ነው ሰኔን የሚዘልቀው።

ነገር ግን አጋሮች ጀርባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በራሳቸው ጉዳይ ተይዘዋል። ዩክሬን ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ቀዳሚ አጀንዳቸው አይደለችም።

ቀሪዎቹ ለጋሾች ደግሞ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከመንግሥት ጋር ተኳርፈዋል። ምን ይሻላል?

የነዳጅ ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረትን በማስከተል ከሚጠቀሱት ውስጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ገንዘቡ አንገብጋቢ ለምን ሆነ?

ምስጥ እንጨትን እንደሚበላው ጦርነትም ምጣኔ ሃብትን ቦርቡሮ፣ ቀረጣጥፎ ይበላል፡፡

“ይህ ጦርነት፣ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በሕዝብ መዋጮ የተደረገ ጦርነት ነው” ይላሉ፣ ለዚህ ጽሑፍ ማዳበሪያ ያነጋገርናቸው የፋይናንስ ጉዳዮች ባለሙያ አቶ አብነት በላይ፡፡

‘በቀጥታ’ የሚሉት የቀጥታ መዋጮውን ነው፡፡ ‘በተዘዋዋሪ’ የሚሉት ደግሞ ለጦርነት የዋለው ገንዘብ ምንጭ ዞሮ ዞሮ ከሕዝብ በግብር መልክ ለመሠረተ ልማት የተሰበሰበ ገንዘብ መሆኑን ከመረዳት ነው፡፡

“ያው ሕዝብ በታክስም በምንም ወደ መንግሥት ቋት ያስገባው ገንዘብ ነው ለጦርነት የዋለው።”

መንግሥትን ይበልጥ ያሽመደመደውም ለዚሁ ነው፡፡

ዘንድሮ እጅ ያጠረው በጦርነቱ ብዙ ተቋማት በመውደማቸው ብቻ አይደለም፡፡ ኮቪድ የጎዳውን ኢኮኖሚ ነው ወዲያውኑ ጦርነት የተቀበለው፡፡

ቀድሞውኑም ኮቪድ በሁሉም ሆስፒታሎች ላይ ጫና አሳድሯል።

መንግሥት ለመድኃኒት የሚያወጣው ወጪ በብዙ እጥፍ ንሯል።

እያንዳንዱ ሆስፒታል የበጀት ጨምሩልኝ ጥያቄን እያነሳ ያለውም ለዚሁ ነው። ምን ይሻላል?

80 ቢሊዮን ብር ከየት ይመጣል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጤናው ዘርፍ ብቻ አይደለም ፈተናው፤ በትምህርት ግንባርም ነገሩ ተመሳሳይ ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፤ እሱም ከበቃን ነው ያሉት በቅርብ ነው።

እንዲህ ዓይነት ወፍራም ገንዘብ መንግሥት የለውም። በቀድሞ ጊዜ ቢሆን ከዚያም ከዚህም ብሎ ማምጣት ይቻል ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በልመናም በብድርም የሚሞላ አልሆነም።

የዓለም ባንክ ራሱ 300 ሚሊዮን ዶላር ነው የሰጠው፡፡

“አሁን አሁን ረጂዎች ለመስጠት ቃል የሚገቡት ገንዘብ አንድ ወረዳንም መልሶ የሚያለማ አይደለም” ይላሉ የፋይናንስ አዋቂ አቶ አብነት በላይ።

ታዲያ ምን ተሻለ?

ግብር መጨመር?

መንግሥት የበጀት ጉድለትን ዜጎችን አስጨንቆ መሙላት ይችል ይሆናል።

ለምሳሌ ግብርን በመጨመር፡፡ ነገር ግን አደጋ አለው። የዋጋ ንረት ያስከትላል።

እንደ ሰደድ እሳት የሚቀጣጠል ንረት ሊያመጣብን ይችላል። ዜጎች ላይ የሚጣል ግብር ቤንዚን የማርከፍከፍ ያህል ነው።

ለምን ገንዘብ አይታተምም ታዲያ?

እሱም አደጋ አለው፡፡ ከፍተኛ አደጋ፡፡ ብር የሚያትም መንግሥትና የአልኮል ሱሰኛ አንድ ናቸው፡፡ አንድ መለኪያና አንድ ረብጣ በጨመሩ ቁጥር ሁለቱም ይሰክራሉ፡፡

በተለይ ገንዘብ ደጋግሞ የሚያትም መንግሥት በግሽበት ራሱን እስኪጥል ይሰክራል፡፡

ስለዚህ ካልተገደደ አያደርገውም፡፡

መንግሥት አሁን ያለውን የግሽበት ራስ ምታቱን ማብረድ ይፈልጋል። ቀላል ግን አይደለም። ለምን?

ምክንያቱም የወጪ-ገቢ ሚዛኑ ለተዛባ አገር የዋጋ ንረትን ማቆም፣ በወንፊት ውስጥ ውሃ ለማቆር የመሞከር ያህል ፈታኝ ስለሆነ ነው።

በሌላኛው ግንባር ሌላም ራስ ምታት አለ። በዚህ አገር የራስ ምታቶቹ ብዛት ራሱ ሌላ ራስ ምታት ነው፡፡

በጦርነቱ አከርካሪው የተመታው ኢኮኖሚ ለማገገም ዓመታትን ይፈልጋል። እሱም ሌላ ጦርነት ካልተቀሰቀሰ ነው።

የሰሜኑ ጦርነት ከሰብአዊ ጥፋቱ ባሻገር ብዙ መሠረተ ልማትን አውድሟል። ውድመቱን ለመጠገን ቢሊዮኖች ያስፈልጋሉ። አቶ አብነት ድምሩን ወደ 500 ቢሊዮን ብር ያደርሱታል፡፡

አፋር፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያ…፡፡ ጦርነቱ ግማሽ አገር ነው ያወደመው ማለት ያስደፍራል።

ይህን ሁሉ መልሶ ለመገንባት የአቶ አብነትን ግምት በግማሽ እንኳ ብንቀንሰው ሩብ ትሪሊዮን ብር ከየት ይታጨዳል፡፡

ወይ ግብር ካልተጨመረ፣ ወይ ደግሞ ገንዘብ ካልታተመ ከየት ይምጣ? ከማን ይሰብሰብ?

አንድ መላ መፈጠር ነበረበት።

‘የማኅበራዊ ልማት ግብር’ (Social Welfare levy) የመጣው ታዲያ ከዚህ ሁሉ “የ9 ወር” ምጥ በኋላ ነው።

በእጁ የኤቲኤም ካርድ የያዘ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

‘የማኅበራዊ ልማት ግብር’ ምንድን ነው?

ብዙውን ጊዜ መንግሥት ቁልፍ የሆኑ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለሕዝብ ለማቅረብ ሲፈተን የሚጣል የቀረጥ ዓይነት ነው።

መንግሥት በቀረጥና ግብር የሰበሰበው ጠቅላላ ገንዘብ አንሶ ምኑን ከምኑ ላድርገው ብሎ ሲጨነቅ አዲስ ገቢ ማግኛ መንገድ ያስባል።

ቀደም ሲል እንዳወሳነው የትኛውም አዲስ ገቢ መሰብሰቢያ መንገድ ግን ጦስ አለው።

የዋጋ ንረት እና የገንዘብ ግሽበት የሚባሉ ሁለት ጣጠኞች አሉ።

እነርሱን ነካክቶ ኢኮኖሚውን የሚያበግን ነገር ሁሉ በገንዘብ አስተዳደር ላይ የባሰ ቀውስ ይፈጥራል፡፡

የተሻለው ዘዴ እንዲህ ዓይነት ወጣ ያለ አዲስ ቀረጥን ማስተዋወቅ ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

ኢትዮጵያ ብቻም ሳትሆን በርካታ አገራት መሠረታዊ አቅርቦት ለሕዝባቸው ለማድረስ ብር ሲያጥራቸው ይህን ያደርጋሉ።

‘መሠረታዊ’ የሚባለው ነገር ከአገር አገር ቢለያይም፡፡

የፋይናንስ ባለሙያው አቶ አብነት ይህን ሊያስረዱ በቅርቡ የጎበኟትን ሩሜኒያን እንደ ምሳሌ ያነሳሉ።

“ኢኮኖሚያቸው ዲጂታል እየሆነ ስለመጣ ‘የዲጂታል ሊትሬሲ’ መሠረታዊ ነገር እየሆነባቸው ሄደ። መንግሥት በየአካባቢው ኢንተርኔት ማቅረብ ግዴታ ሆነበት። አለበለዚያ ማኅበራዊ አገልግሎታቸን ማቅረብ ከባድ ሊሆንበት ሆነ። በሩሜኒያ ኢንተርኔት ወደ መሠረታዊ ነገር እየተጠጋ የመጣውም ለዚያ ነው” ይላሉ።

አቶ አብነት የታክስ፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አማካሪ ናቸው።

እንደ እርሳቸው ምልከታ ከሆነ እንዲህ በተተበተበ ችግር ውስጥ ላለ መንግሥት፣ ለ114 ሚሊዮን ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት ቢከብደው የሚደንቅ አይሆንም።

አንደኛ ከበጀቱ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚይዘው ማኅበራዊ አገልግሎት ነው፡፡ ሁለተኛ ብዙዎቹ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በኢትዮጵያ በመንግሥት ቀጥተኛ ወጪ የሚሸፈኑ ናቸው፡፡

አቶ አብነት “ለኔ ኢትዮጵያ የዌልፌር ስቴት ሆና ነው የምትታየኝ፤ በአቅሟ” የሚሉትን ይህን ተመርኩዘው ነው፡፡

ለዚህም ይሆናል ይህ መንግሥት ወደ አዳዲስ የቀረጥ ዓይነቶች ማማተር የጀመረው።

ያማተረው ግን ወደ ዌልፌር ታክስ ብቻ አይደለም፡፡

በሌላ ጊዜ የምንመለስባቸው የ‘ፕሮፐርቲ’ [የንብረት] ታክስ እና የነዳጅ ምርቶች ላይ ያለው ኤክሳይዝ ታክስም በመደርደርያችን ላይ ናቸው፡፡

ሌላም አለ፤ በሂደት ላይ ያለ፡፡ የኢትዮጵያ 2 ሺህ ከተሞች ራሳቸውን እንዲችሉ የመንገድ ክፍያን ለማስተዋወቅ በሙከራ ደረጃ ታስቧል፡፡

መንግሥት ራሱን ከበጀት ጭንቅ ለማውጣት ገና ወደ ብዙ አቅጣጫ እንደሚያማትር እነዚህ አመላካቾች ናቸው፡፡

አዲሱ ግብር በየትኞቹ እቃዎች ላይ ነው የተጣለው?

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በነሐሴ ወር መባቻ ላይ ባካሄደው ስብሰባ ይህን አዲስ ረቂቅ መክሮና ዘክሮ አጽድቆታል።

ይህ ግብር በሁሉም ወደ አገር ቤት በሚገቡ ቁሳቁሶች ላይ የተጣለ ነው።

ይሁንና ነዳጅ እና ማዳበሪያ ከዝርዝሩ ወጥተዋል።

ይህ ለፋይናንስ አዋቂው አቶ አብነት ብልሃት የታከለበት አካሄድ ሆኖ ይታያቸዋል።

ምክንያቱም ነዳጅ እና ማዳበሪያን የሚነኩ ቀረጦች ጦሳቸው ለሰፊው ሕዝብ ስለሚደርስ፡፡

ዲፕሎማቶች የሚያስገቧቸው ዕቃዎችም ከዚህ የዌልፌር ቀረጥ ነጻ ናቸው። ይህ የሆነው ኢትዮጵያ የቪየና ኮንቬንሽን ፈራሚ በመሆኗ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ ውጪ የሱር ታክስ ግዴታ ከሆነባቸው የገቢ ዕቃዎች ውጪ ባሉት ገቢ ዕቃዎች ሁሉ አዲሱ ቀረጥ ተጭኗል።

በእጆቹ ሳንቲም የያዘ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህ ግብር በየዓመቱ ስንት ብር ያስገኛል?

መንግሥት እንደሚለው ከሆነ በአማካይ በየዓመቱ እስከ 22 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ያስችለዋል።

እዚህ ቁጥር ላይ የተደረሰው በየዓመቱ የገቢ ዕቃዎች መጠንን ከግምት በማስገባት ነው። በየዓመቱ ወደ አገር ቤት እስከ 114 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሸቀጥ ይገባል።

በእያንዳንዱ ገቢ ዕቃ 3 ከመቶ ግብር ሲሰላ ወደዚህ አሐዝ ይደረሳል።

የማኅበራዊ ልማት (ሶሻል ዌልፌር) ቀረጥ የግብር ምጣኔው ሦስት በመቶ ነው።

መንግሥት እንደሚለው ይህ ትንሹ የግብር መጠን ሲሆን ተጽእኖ እንዳይኖረው በሚል ነው ሰፊ መሠረት እንዲኖረው ተደርጎ የተበጀ ነው።

አቶ አብነት ይህ የግብር ተመን ውድ ነው ወይስ አይደለም ብለው ለመበየን ይቸገራሉ።

“በገቢ ዕቃዎች ላይ ከሚጣሉ የታክስ ዓይነቶች አንጻር ከታየ በጣም ዝቅተኛው የቀረጥ ምጣኔ ሊባል ይችላል። ከወደሙ መሠረተ ልማቶች ብዛትና ከሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ስፋት አንጻር ሲታይ ደግሞ በተቃራኒው ሊታሰብ ይችላል።”

አዲሱ ግብር ኑሮን ያስወድዳል?

ይህ ግብር በሦስት መንገድ በሕዝብ ላይ ቀጥተኛ ጫና እንዳያደርስ የተሞከረ ይመስላል፤ የናረውን ኑሮ የበለጠ እንዳያንር።

አንደኛው ግብሩ የተጣለው በአስመጪዎች ላይ ብቻ መሆኑ።

ሁለተኛው የግበሩ ምጣኔ አነስተኛ ተደርጎ መሰላቱ።

ሦስተኛ ይህ ግብር እንደ ነዳጅ እና ማዳበሪያ ባሉት ቁልፍ ነገሮች ላይ አለመጣሉ።

ይሁንና አቶ አብነት “ዞሮ ዞሮ ገንዘቡን የምናዋጣው እኛ እንጂ መንግሥት እንደሚያስበው አስመጪ ነጋዴዎች አይደሉም” ይላሉ።

ይህን የሚሉት ያለ ምክንያት አይደለም።

በነጋዴ ላይ የተጣለ ግብር ሄዶ ሄዶ ለሸማቹ መከፋፈሉ እሙን ስለሆነ ነው።

ይህ ሲጠቃለል አዲሱ ግብር በኑሯችን ላይ መጠነኛ ቁንጥጫ ላይኖረው አይችልም፡፡

ኑሮንስ ያከብድ ይሆን?

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የገንዘብ ግሽበት፣ የዋጋ ንረት እና ምጣኔ ሃብታዊ ምስቅልቅ አጋጥሟል።

ነዳጅ በዓለም ገበያ ሰማይ ነክቶ ነው አሁን ቀስ በቀስ ለማረፍ እያኮበኮበ ያለው። መንግሥት ግን ከነዳጅ ድጎማው ቀስ በቀስ እየወጣ ነው።

በዚያ ላይ በጦርነት የደቀቀና ገና እያገገመ ያለን ኢኮኖሚ ይዞ ነው ያለው።

ታዲያ በዚህ ሁኔታ ይህ አዲስ ግብር ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ አያደርገውም?

ለንግድና ኢንቨስትመንት ባለሙያው አቶ አብነት፣ መንግሥት ይህን ቀረጥ ማስተዋወቁ መጥፎ እርምጃ የሚባል አይደለም።

እንዲያውም ከሚያመጣው ጣጣ ይልቅ በጎ ጎኑ ይታያቸዋል፡፡ በዚህ ወቅት የሕዝብ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡

ይህን የሚሉት በምክንያት ነው። ዋናው ምክንያታቸው በመንግሥት ላይ ጫናው መበርታቱን ከመገንዘብ ይመነጫል፡፡

አንደኛ ረጂዎች በዩክሬን ጉዳይ ተጠምደዋል። የረጂዎች መታከት (donors fatigue) እየታየ ነው።

ሁለተኛ በጦርነት የወደመው መሠረተ ልማት ቁጥር ሥፍር የለውም።

መንግሥት ይህን ክፍተት በሌላ በየትኛውም መንገድ ሊሸፍነው አይቻለውም ባይ ናቸው።

መንግሥት ይህን ገንዘብ በዌልፌር መልክ ከመሰብሰብ ሌላ አማራጭ አልነበረውም ወይ ተብለው ሲጠየቁም፣ “ይህን ሐሳብ ያመጡ ሰዎች መቼስ ብዙ አማራጮችን እንዳዩ እገምታለሁ” ይላሉ፡፡

ምናልባት ሌላው አማራጭ በሕዝብ ፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ ተሳትፎ ገንዘቡን መሰብሰብ ሊሆን ይችል ነበር ብለውም ይገምታሉ፡፡

ይሁንና ይህም ፈተናው ቀላል እንዳልሆነ ይረዳሉ፡፡

“ሕዝቡ ለግደቡ፣ ብሎም ለተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች፣ ለመፈናቀሎች በየጊዜው ገንዘብ አዋጣ እየተባለ ተዳክሟል” ይላሉ፡፡

ሌላው መንገድ ለአቶ አብነት ከነጋዴዎች በቀጥታና በፈቃድ ገንዘብ ማሰባሰብ ነው፡፡

ይሁንና “ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር፤ መንግሥት የነጋዴውን ፊት ለማየት የፈራ ይመስለኛል” ይላሉ፡፡

ከሕዝብም ከነጋዴም ዐይን እየሸሸ ያለው መንግሥት ታድያ ይህን ገንዘብ በእጅ አዙር ለመሰብሰብ የመረጠ ይመስላል፡፡

እነዚህ ሁሉ ከግምት ሲገቡ መንግሥት ለመልሶ ማልማት ገንዘብ ለማምጣት ያሰበበት መንገድ ተገቢነቱ ይጎላባቸዋል፤ ለአቶ አብነት በላይ፡፡

ይልቅ እርሳቸውን የሚያሰጋቸው የ3 በመቶ ቀረጥ መጣል አይደለም። ከዚያ ይልቅ የሚያሳስባቸው ሁለት ነገር ነው፡፡

ይህ ገንዘብ ከተሰበሰበ በኋላ ለታለመለት ዓላማ ይውላል ወይ? የሚለው አንዱ ነው፡፡

ሌላኛው ደግሞ፣ “በመልሶ ማልማት የገነባነውን መልሰን እንዳናወድመው ነው፡፡”

ከፍርሃቶቻቸው የሚልቀው ግን ይህ ነው፡፡

“ከፊት ለፊታችንስ ሌላ አውዳሚ ጦርነት እንደሌለ በምን እርግጠኛ እንሆናለን?”