የዋጋ ንረት ምንድን ነው? እንዴትስ ሊቀረፍ ይችላል?

የዋጋ ንረትን የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ይህ ቃል በእንግሊዝኛው (ኢንፍሌሽን) የሚባለው ነው፡፡ አንዳንድ የምጣኔ ሀብት አዋቂዎች የዋጋ ግሽበት ይሉታል።

ሌሎች ደግሞ የለም "የዋጋ ግሽበት" የሚለው ቃል ይበልጥ የሚወክለው የዋጋ መውረድን (ዲፍሌሽንን) እንጂ የዋጋ ንረትን (ኢንፍሌሽንን) አይደለም ብለው ይከራከራሉ።

ለማንኛውም የአማርኛ ቃሉ የቱን በትክክል ይወክላል የሚለውን ክርክር ገታ አድርገን እንቀጥል።

በዚህ ሐተታ የዋጋ ንረት ወይም የገንዘብ ግሽበትን (ኢንፍሌሽን) ለሚለው ጽንሰ ሐሳብ መጠቀማችንን ልብ ይሏል።

ለመሆኑ የዋጋ ንረት ምንድነው? እንዴትስ ይፈጠራል?

ገንዘቡ ወረቀት ሲሆን

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተመሳሳይ አገልግሎት ብዙ ገንዘብ ከኪስዎ አውጥተው ለረዥም ሰዓት ይቆጥራሉ?

በአንበሳ ድፍረት ገበያ ወጥተው ዋጋ ሲጠራ ግን ነብር እንዳየ ሰው ይበረግጋሉ?

በፊት ሳይጨናነቁ ይገዙት የነበረ ነገር ሁሉ አሁን ደርሶ ከበረብዎ?

ከቀይ ሽንኩርት እስከ ነጭ ሽንኩርት፣ ከቲማቲም እስከ ቃሪያ አልቀመስ አለ?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አካል የሆነው የዓለም ሥራ/ሠራተኞች ድርጅት (ILO) እንደሚለው ከሆነ በዓለም ላይ ዓመታዊ የዋጋ ንረት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል።

ባለፈው መጋቢት 3.7 ከመቶ ነበር። በዚህ ዓመት መጋቢት 9.2 በመቶ ተመዘገበ።

ይህ ማለት የማንኛውም ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች እንዲሁም አገልግሎቶች ዋጋ በምድር ላይ በሚያስደነግጥ ፍጥነት አሻቅቧል።

የዋጋ ንረት ስንል ምን ማለት ነው?

በቀላሉ እናስቀምጠው ካልን የዋጋ ንረት (ኢንፍሌሽን) የሚባለው ለአንድ ሸቀጥ ወይም አገልግሎት የሚከፈለው ዋጋ በጊዜ ሂደት እየተወደደ ሲመጣ ማለት ነው።

በኪስዎ የያዙት ተመሳሳይ ገንዘብ ትናንትና ያገኙትን ተመሳሳይ አገልግሎት ሳይሰጥ ሲቀር ማለት ነው።

የዋጋ ንረት ለምን ይከሰታል? ብለው ይጠይቁ ይሆናል።

ነገሩ ትንሽ እንቆቅልሽ ነው።

ሁለት ቀላል ምክንያቶችን ግን መጥቀስ ይቻላል።

አንዱ የፍላጎት መናር የሚፈጥረው የዋጋ ንረት ነው።

ይህ ሲባል ምን ማለት መሰላችሁ፤ ለአንድ አገልግሎት ብዙ ሰዎች ከፍተኛ ፍላጎት ሲያሳዩ የዋጋ ንረት ይፈጠራል።

ለምሳሌ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው በሬዎች እየታረዱ ነገር ግን በጣም በርካታ ሕዝብ ድንገት በቁርጥ ሥጋ ፍቅር ቢወድቅ የዋጋ ንረት ይፈጠራል።

እንዲህ ዓይነቱ ንረት የሚፈጠረው ለብዙ ጊዜ ሲንኮታኮት የቆየ ምጣኔ ሀብት እያገገመ ሲመጣ ነው።

ሰዎች ኑሯቸው አስተማማኝ ሲሆን፣ ገቢያቸው ሲደረጅ፣ በመንግሥት ሥርዓቱና መዋቅሩ፣ በገበያ መነቃቃቱ እምነት ሲኖራቸው ገንዘብ ከመቆጠብ ይልቅ ገንዘብ ለማጥፋት ይበረታታሉ።

ወደ ገበያ የሚወጣው ሰው ይበረክታል፡፡ ምግብ ቤቶች በበላተኛ ይጥለቀለቃሉ።

በዚህ በፍላጎት መናር የሚከሰተው የዋጋ ንረት (ኢንፍሌሽን) ተገልጋዩ ማኅበረሰብ የሚፈጥረው ነው።

ነጋዴዎች የፍላጎትን መጨመር በበቂ ለማስተናገድ ሲያቅታቸው ዋጋ ንረት ይኖራል።

የነዳጅ ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረትን በማስከተል ከሚጠቀሱት ውስጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የነዳጅ ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረትን በማስከተል ከሚጠቀሱት ውስጥ ነው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነጋዴዎች ዋጋ ቢጨምሩም ተገልጋይ/ሸማች በቀላሉ ስለማይሸሽ አያሳስባቸውም፡፡ ሸማች በፍጹም አልደነግጥ ሲል ደጋግመው ዋጋ ይጨምራሉ።

ይህ ዓይነቱ የዋጋ ንረት በሸማቾች ምቾትና መደላደል የሚፈጠር ሲሆን በእንግሊዝኛው (ፕራይስ ኢንፍሌሽን) ተብሎ ይጠራል።

አዲስ ፍላጎት የፈጠረው አዲስ ዋጋ እንደማለት ነው።

ሁለተኛው የዋጋ ንረት የሚፈጠረው የብዙ ነገሮች ዋጋ መጨመር ነው፡፡ ይህ በእንግዝኛ ኮስት ፑሽ ኢንፍሌሽን (Cost-Push Inflation) ተብሎ ይጠራል።

ይህ ደግሞ እንዴት እንደሚፈጠር እንመልከት።

አንድን አገልግሎት ወይም ምርት ለማሟላት ግብአቶች በየደረጃው ይወደዳሉ።

ይህ በብዙ ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንዱና ዋንኛው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ነው።

ነዳጅ ሲጨምር አብዛኛው አገልግሎትና ሸቀጥ አብሮ ይንራል።

በአጭሩ አንድን ምርት ወደ ገበያ አጠናቆ ለማውጣት በሂደቱ ያሉ ሌሎች ግብአቶች ዋጋ በመጨመራቸው ምክንያት ያንን የዋጋ ጭማሪ ሸማቹ/ተገልጋዩ እንዲከፍለው ሲደረግ ማለት ነው።

ቀድመን ባነሳነው የቁርጥ ሥጋ ምሳሌ እንቀጥል።

በዚህ ሁኔታ የተፈጠረው የዋጋ ንረት የግድ የቁርጥ ሥጋ ተመጋቢው ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ሳይሆን በሂደቱ ላይ የሚከሰት ጭማሪ ያመጣው ነው የሚሆው።

በዚህ ሁኔታ ሥጋ ወዳዱ ማኅበረሰብ ቁጥሩ አልጨመረም እንበል።

ነገር ግን በሬውን ለመቀለብ የወጣ ወጪ፣ በሬውን ከሐረር አዲስ አበባ ጭኖ ለማምጣት የወጣ የአይሱዙ ዋጋ፣ በሬው ቄራ ሲታረድ የተከፈለው ዋጋ፣ የቁርጥ ቤት አስተናጋጆች ደመወዝ መጨመር፣ የአዋዜ መወደድ፣ ስል ቢላዎችን በብዛት ለመግዛት የዋጋ መጨመር ያስከትላል።

በተጨማሪ ደግሞ የሥጋ ቤቱ ባለቤት የተከራየው ቤት መጨመር፣ ለምግብ ቤቱ የሚያወጣው የውሃና መብራት ዋጋ ወጪ ሲጨምር፣ የሥጋ ቤቱ ባለቤት ልጆች የሚማሩበት ውድ ትምህርት ቤት ዋጋ በእጥፍ ሲጨምር ወዘተ. . . የዋጋ ንረቱ እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል ማለት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላው ዓለም እየተከሰተ ያለው የዋጋ ንረት/የገንዘብ ግሽበት ምክንያት ታዲያ ይህ ሰንሰለታማ ጣጣ ያመጣው ነው።

በተለይ የኮቪድ ወረርሽኝ ያቀዛቀዘውን ምጣኔ ሃብት ለማንሰራራት እየደኸ በነበረበት ጊዜ ሩሲያ ዩክሬንን ወረረችና ነገሩ ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ።

ሩሲያና ዩክሬን ደግሞ በዓለም የገበያ ሰንሰለት እጅግ ቁልፍ የሚባሉ መጋቢ አገሮች ነበሩ።

የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ እና በዓለም?

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት አስደንጋጭ ከሚባሉት አገሮች የሚደመር ነው ብንልም፣ ከኢትዮጵያ የባሱ በርካታ አገራት አሉ።

ነገሩ ያልነካው የለም፡፡ በብዙ አገራት የዋጋ ንረቱ በሁለት አሐዝ የሚሰላ መሆኑ ነው ጉድ እያስባለ ያለው።

በቱርክ ለምሳሌ የዋጋ ንረቱ 70 ከመቶ ደርሷል፡፡ በአርጀንቲና 51 በመቶ፣ በስሪላንካ 30 በመቶ ነው።

የስሪላንካ ሕዝብ ነገሩ አንገሽግሾት አደባባይ ወጥቷል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም በሕዝብ ተቃውሞ ሥልጣናቸውን ለቀዋል።

በኢራንም ተመሳሳይ ተቃውሞ ተቀስቅሶ የነበረ ቢሆንም አሁን በረድ ብሏል።

የቴህራን መንግሥት ያመነው ንረቱ 40 በመቶ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን እውነታው ከ50 በመቶ በላይ መድረሱ ነው።

ከፍተኛ የዋጋ ንረት (hyperinflation) ምንድነው?

ለዋጋ ንረትም ሌላ ንረት አለው።

አንዳንድ ጊዜ የዋጋ ንረት በራሱ ሊያብጥ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ ነው።

ከፍተኛ የዋጋ ንረት የምንለው የአንድ አገር የገንዘብ አቅም ጨርሶ ሲንኮታኮት ነው።

ይህ ነገር እዚህ በአህጉራችን ዚምባብዌ ተከስቶ ያውቃል።

በመካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ በሊባኖስ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ በቬንዝዌላ ውስጥ ተከስቶ ነበር።

የአገሬው ገንዘብ ከወረቀት እኩል ወደ መሆን ሲቃረብ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ወይም (ሃይፐር ኢንፍሌሽን) ይባላል።

በተጋነነ ምሳሌ ለማስረዳት የአገሬውን ብር በጆንያ ይዞ ሱቅ ሄዶ አንድ ኪሎ ስኳር ገዝቶ የመመለስ ዓይነት።

ሩሲያና ዩክሬን ለምን ከዋጋ ንረት ጋር ተያያዙ?

ለምሳሌ ስንዴን እንውሰድ። ዩክሬንና ሩሲያ የዓለም ዋነኛ አምራቾችና ሻጮች ናቸው። ዓለምን ስንዴ የሚያበሉት ሁለቱ አገሮች ነበሩ።

ሁለቱ አገሮች ጦርነት ገጠሙ።

ከእነርሱ እየገዙ ሕዝባቸውን የሚቀልቡ አገራት በሙሉ ችግር ውስጥ ገቡ። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ገዝተው ለሌሎች የሚሸጡም ችግር ውስጥ ወደቁ።

ዘይትም ተመሳሳይ ችግር ነው የገጠመው። ዋንኛ አምራቾቹ እነ ኢንዶኔዥያና ማሌዥያ ዘይት ቅድሚያ ለሕዝባችን ብለው የወጪ ንግድ ላይ ዕቀባ አስቀመጡ።

በዚህ የተነሳ ሸማች አገራት ለከፍተኛ ችግር ተዳረጉ።

አሁን የዋጋ ንረቱን ምንድነው የፈጠረው?

ዓለም ከምንገምተው በላይ በንግድ ሰንሰለት የተሳሰረ ነው።

ለምሳሌ ኮቪድ ወረርሽኝና ምጣኔ ሃብትን ምን አገናኛቸው? ልትሉ ትችሉ ይሆናል። ሁሉ ነገር የተሳሰረ ነው ያልነው ለዚህ ነው።

እንዴት?

ለምሳሌ ኮቪድ የእንቅስቃሴ ገደብ አስከተለ፤ ላብ አደር ፋብሪካ አልሄደም፡፡ ምርት አልተመረተም።

ፋብሪካው ገቢ ቀነሰበት፤ ሠራተኛው ሥራውን አጣ፡፡ ሸማች ምርት አልደርስ አለው።

በኮቪድ የተነሳ ዕዳቸውን በቱሪዝም ገቢ የሚከፍሉ አገራት ጭንቅ ውስጥ ገቡ።

አምራች አገራት በበቂ ማምረት አቆሙ።

አንድ ቻይና የምትመረት ብሎን በወቅቱና በጊዜው ተመርታ ወደ አዲስ አበባ አለመድረሷ አንድ ሙሉ ፋብሪካን ልታዘጋ ትችላለች።

የዚያ ፋብሪካ መዘጋት፣ ሺህ ሠራተኛን ሊያፈናቅል ይችላል። የዚያች ብሎን ነገር በቻይናና በአዲስ አበባ ብቻ አያበቃም፡፡ ይህን ሐተታ ያረዝመዋል እንጂ ጉዳዩ ቢጻፍ ዓለምን ያዳርሳል።

የዓለም የንግድ ሰንሰለት እጅግ ከምናስበው በላይ የተሳሰረ ነው የምንለው ለዚህ ነው።

በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በርካታ ቦታዎች በድርቅ ተመተዋል።

በጦርነቱ የተነሳ የነዳጅ ዋጋ ንሯል። ነዳጅ ሲንር የሁሉንም ቁሳቁስ ዋጋ አብሮ ያነዳል፡፡

የኮቪድ ጠባሳ ቀላል አይደለም። የሠራተኞች መመናመን በጋዝ፣ በምግብና በመኪና ዋጋ ላይ ከባድ ምት አሳርፏል።

በዩክሬን ጦርነት የተነሳ በስንዴ፣ በማዳበሪያ፣ በጋዝ እንዲሁም በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቡጢውን አሳርፏል።

ጋዝና ነዳጅ በሳንቲም ሲጨምሩ ፋብሪካዎች ሸብ ረብ ይላሉ።

ወጪያቸውን ለማካካስ በትንንሽ ምርቶቻቸው ላይ ሁሉ ትንንሽ ዋጋ ይጨምራሉ።

ትንንሹ ጭማሪ በየሰንሰለቱ ትንንሽ እየተጨመረበት ይሄዳል።

በመጨረሻ ጭማሪው የእያንዳንዱን ሸማች ቤት ያንኳኳል።

ደግሞ አንርሳ፤ ነጋዴው ሸማች ነው። ሸማችም ነጋዴ ነው። ከዚህ ሰንሰለት የሚወጣ የለም። ሻይ ስንጠጣ ሸማች ነን። ሻይ ቅጠል ስንተክል ነጋዴ ነን።

እሽክርክሪቱ ከምንገምተው በላይ አስገራሚ ነው።

ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የምርት እጥረት ዋጋ ስለሚያንር ሰዎች ፍጆታቸውን ለመግዛት ረጅም ሰልፍ ለመጠበቅ ይገደዳሉ

ዋጋ ንረት አዙሪት የምንወጣው እንዴት ነው?

በየዘመኑ ይህ የዋጋ ንረት ይከሰታል። የዘንድሮስ የከፋ ነው ሲባል ሌላ የከፋ ይመጣል።

አገሮች ይህን የሚቋቋሙበት አንድ ሁነኛ መላ የላቸውም።

ነገሩ ከምንገምተው በላይ ውስብስብ ስለሆነ።

ለዚህም ነው የምጣኔ ሃብታ አዋቂዎች ቀጥተኛ መልስ መስጠት የሚከብዳቸው።

ሆኖም ግን ከችግሩ መውጣት የሚቻለው አንዱ መንገድ ምርትን በመጨመር ነው።

እርግጥ ነው ድሃ አገራት መርፌን ሳይቀር ከውጭ ስለሚያስገቡ፣ ከዚህ የዋጋ ንረት ለመውጣት ፍዳቸውን ማየታቸው የሚጠበቅ ነው።

ትክክለኛ የማክሮና የማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲን በመከተል ህመሙን ማሰታገስ ይችላሉ።

ምጣኔ ሃብት ጽንሰ ሐሳቦች ሙልጭልጭ ናቸው። ሽቅብ የተቆለለ መጽሐፍ ማለት ናቸው።

አንዱ ሲነካ ሌላው ሊፈርስ ይችላል።

የየዋጋ ንረትን ለማስታገስ የሚወሰድ እርምጃ ሥራ አጥነትን ሊፈጥር ይችላል።

የወለድ ምጣኔ መጨመር ወይም መቀነስ፣ አንዳች የጎንዮሽ ጉዳትን ያመጣል።

የምጣኔ ሃብት ሳይንስ እንደ መድኃኒት ነው። ያለ ጎንዮሽ ጉዳት አይፈውስም፣ አይፈወስም ይላሉ ባለሙያዎች።

አንዳንዶቹ ችግሮች የዓለም የገበያ ትስስር የሚፈጥራቸው በመሆናቸው ከአንድ አገር አቅም በላይ ይሆናሉ።

አሁን የተፈጠሩት ሁኔታዎችም በብዛት ዓለም አቀፋዊ መልክ ያላቸው ናቸው።

ይሁንና የዋጋ ንረት ብሔራዊ ባንክና መንግሥታት በሚወስዷቸው የንዑስ እና ጥቅል ምጣኔ ሃብታዊ እርምቶች (Micro/Macroeconomics) ሊሻሻል ይችላል።

ይህም ለምሳሌ በወለድ ምጣኔ ማስተካከያ ሊገለጽ ይችላል።

መንግሥት የሚያካሄዳቸውን መጠነ ሰፊና ግዙፍ መሠረተ ልማቶች ጋብ በማድረግም ሊቃለል ይችላል።

ይህን ማድረግ በሌላ አንጻር ሥራ አጥነትን ሊያባብስ ይችል ይሆናል።

የወለድ ምጣኔ ከፍ መደረግ ደግሞ የገበያ ፍላጎትን ይቀንሳል። ይህም የኢኮኖሚ ዕድገቱን ዘገምተኛ ያደርገዋል፤ ሆኖም የዋጋ ንረትን አደብ ያስገዛዋል ይላሉ አዋቂዎች።

በገበያው ውስጥ እየተሸከረከረ ያለው ገንዘብን መሰብሰብ፣ የትርፍ ግብርን መጨመርም አንዳንድ ጊዜ የዋጋ ንረትን ሊያረግብ ይችላል የሚሉ አሉ።

መፍትሄውን መጠቆም ስለ ጉዳዩ መጣጥፍ እንደመጻፍ ቀላል ስላልሆነ በዚሁ ብንገታውስ?