የዋጋ ግሽበት እጅግ የሚያሰጋቸው አገራት የትኞቹ ናቸው?

ቱርክ ውስጥ ዳቦ ለመግዛት ተሰለፉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቱርክ ውስጥ ዳቦ ለመግዛት ተሰለፉ ሰዎች

የዋጋ ግሽበት ዓለምን ከጥግ ጥግ አስግቷል።

ከኢትዮጵያ እስከ ሲሪ ላንካ ከብራዚል እስከ ደቡብ አፍሪካ።

ምግብ ተወዷል። ነዳጅ ተወዷል። ምን ያልተወደደ አለ?

የተለይ የመሠረታዊ አቅርቦቶች ዋጋ መናር ዓለምን አስጨንቋል።

በእርግጥ የዋጋ ግሽበት ከሌላው የዓለም ክፍል በላይ የሚያንገዳግዳቸው አገሮች አሉ። ለዚህ ምክንያቱ ሰብል አለመሰብሰቡ፣ ወረርሽኙ መክፋቱ እና የተፈጥሮ ጋዝ መጥፋቱ ነው።

በዚህ ደግሞ በአፍሪካ ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት ዋነኛ ተጎጂ ናቸው። ቱርክ፣ ብራዚል እና ሲሪ ላንካም ይጠቀሳሉ።

ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት

አብዛኞቹ ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት ምግብ ለማብሰል የተጣራ ፈሳሽ ጋዝ (በሲሊንደር የሚታሸግ ቡታ ጋዝ) ይጠቀማሉ።

የጋዝ ዋጋ ደግሞ እያሻቀበ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት በአንዳንድ የናይጄሪያ ግዛቶች ጋዝ በእጥፍ ጨምሯል። ብዙዎች ወደ ማገዶ እንጨት፣ ከሰል እና ኬሮሲን ፊታቸውን ለማዞር ተገደዋል።

እነዚህ አማራጭ ኃይል ምንጮች ደግሞ አካባቢን ይበክላሉ። የተጠቃሚዎቹን ሳምባም ይጎዳሉ።

የነዳጅ ዋጋ መጨመር፤ የማዳበሪያ ዋጋ እንዲሁም ምግብ ከእርሻ ወደ መደብር የሚጓጓዝበት ዋጋም እንዲንር ምክንያት ሆኗል።

የናሳ የመሬት ምልከታ እንደሚጠቁመው በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ዝናብ ከጠፋ ሰነባብቷል። ይህም የዋጋ ግሽበት አስከትሏል።

በአንጎላ ባለፈው ዓመት የምግብ ዋጋ 36.4 በመቶ መጨመሩን የአገሪቱ የስታትስቲክስ ተቋም ይፋ አድርጓል።

በማላዊ የኑሮ ውድነት ፀረ መንግሥት ሰልፎችን አስከትሏል።

በአፍሪካ 282 ሚሊዮን ሰዎች ተመጣጣኝ ምግብ እንደማያገኙ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።

ቱርክ

ጥቅምት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በኢስታንቡል እና ዲያርባሪክ ከተሞች ሰልፍ መውጣታቸው ይታወሳል።

አምና የዋጋ ግሽበት በ36 በመቶ ከፍ ብሏል። የአገሪቱ የስታትስቲክስ ተቋም እንዳለው የምግብ ዋጋ በዓመት 44 በመቶ ጨምሯል።

በኢስታንቡል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመንግሥት ሱቆች ለዳቦ ሰልፍ ይዘው ማየት ተለምዷል። የግል ዳቦ ቤቶች ዋጋ ስለማይቀመስ ከእነሱ መግዛት አይታሰብም።

ነዳጅና ማዳበሪያ ከመወደዱ ባሻገር የቱርክ መንግሥት የስንዴ ዋጋን መጨመሩ ዳቦ እንዲወደድ አድርጓል።

የአውቶብስና ባቡር ክፍያም በእጥፍ ጨምሯል።

የመብራት ክፍያ 50 በመቶ፣ የጋዝ ክፍያ 25 በመቶ ከፍ ብሏል።

ብራዚል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty

የምስሉ መግለጫ, ብራዚል በቀንድ ከብት ከዓለም አንደኛ ብትሆንም የሥጋ ዋጋ እጅግ ከፍ ብሏል። ሥጋ የሚገዙ ዜጎች ቁጥርም በ67% አሽቆልቁሏል።

መንግሥታት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የወለድ መጠንን የሚጨምሩበት አሠራር አለ። ይህም ገንዘብን ለማግኘት አስቸጋሪ ያደርጋል።

ፕሬዘዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን "ወለድን መጨመር ሀብታምን የበለጠ ሀብታም የሚያደርግ፣ ድሃን የባሰ የሚያደኸይ ሰይጣናዊ አካሄድ ነው" ብለዋል።

የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ የወለድ መጠንን እንዲቀንስም አዘዋል።

ይህ ውሳኔ የቱርክ መገበያያ ሊራ ከዶላር አንጻር ዋጋው በ45 በመቶ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል።

መንግሥት ለዋጋ ግሽበት መፍትሔ ያለው የደመወዝ መጠንን በ50 በመቶ ማሳደግ ነው።

የምጣኔ ሀብት ተንታኞች የቱርክ የዋጋ ግሽበት በመጪው ፀደይ 50 በመቶ ይደርሳል ብለው ተንብየዋል።

ብራዚል

የብራዚል የስታትስቲክስ ተቋም እንደሚለው የሸቀጥ ዋጋ በ10 በመቶ፣ የነዳጅ ዋጋ በ50 በመቶ ጨምሯል።

አምና በድርቅ ሳቢያ መሠረታዊ ሰብል የሆኑት ሩዝ እና ባቄላ ጠፍተው ነበር። የምግብ ዋጋም በ14 በመቶ አሻቅቧል።

ብራዚል በቀንድ ከብት ከዓለም አንደኛ ብትሆንም የሥጋ ዋጋ እጅግ ከፍ ብሏል። ሥጋ የሚገዙ ዜጎች ቁጥርም በ67 በመቶ አሽቆልቁሏል።

በድርቁ ሳቢያ ኃይል አመንጪዎችም እየተንገዳገዱ ነው። ለምሳሌ የአገሪቱ ከውሃ ኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ ተቋም ተዘግቷል። በዚህ ምክንያት የመብራት ክፍያ በአንድ አምስተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

ከ213 ሚሊዮን ብራዚላውያን 27 ሚሊዮኑ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖሩ ጉቴሮ ቫርጋስ የተባለ ድርጅት ገልጿል። እነዚህ ሰዎች በወር በ49 ዶላር ይኖራሉ።

ሲሪ ላንካ
የምስሉ መግለጫ, በተለይም ሩዝ፣ ስንዴ እና የዱቄት ወተት ዋጋቸው አይቀመስም። ነዳጅም በ85% ጨምሯል።

ሲሪ ላንካ

አምና ከነበረው የምግብ ዋጋ አንጻር የዘንድሮው 20 በመቶ ንሯል።

ደሴቷ ሲሪ ላንካ አምና መሠረታዊ የምግብ አቅርቦትን ከውጭ ለማስገባት ስትሞክር የምግብ ዋጋ በጣም ተወዶባታል።

ዋነኛ ገቢዋን ከቱሪዝም ታገኝ ነበር። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግን ለሁለት ዓመታት የአገሪቱን የእንጀራ ገመድ በጥሷል።

በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት ተመናምኗል።

ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ስለሌላቸው መንግሥት ምግብ ጫኝ መርከቦች እንዳይገቡ አግዷል።

ይህም በመደብሮች የምግብ አቅርቦት ውስን እንዲሆን፣ የሸቀጥ ዋጋም እንዲንር አድርጓል።

በተለይም ሩዝ፣ ስንዴ እና የዱቄት ወተት ዋጋቸው አይቀመስም። ነዳጅም በ85 በመቶ ጨምሯል።

የተቆጣውን ሕዝብ ለማረጋጋት መንግሥት 1 ቢሊዮን ዶላር መድቦ፤ በሠራተኞችን ደመወዝ እና ጡረታ ላይ ማሻሻያ አድርጓል።

ከአንዳንድ የምግብ ዓይነቶች እና መድኃኒት ላይም ቀረጥ ተነስቷል።