'ገበሬው አምርቶ የማይጠቀምባት ኢትዮጵያ' የኑሮ ውድነቱን እንዴት መቀነስ ትችላለች?

የፎቶው ባለመብት, Louis Dawson
በምጣኔ ሃብታዊ ቋንቋ የአቅርቦት ሰንሰለት ይባላል። በእንግሊዝኛው 'ሰፕላይ ቼይን' የሚባለው ማለት ነው።
የአቅርቦት ሰንሰለት ሸማቹ ወይም ተገልጋዩ የሚፈልገው ነገር ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ ያለው ሂደት ነው።
የምጣኔ ሃብት ሰዎች የአቅርቦት ሰንሰለት የአንዲት ሃገር ዕድገት ምሰሶ ወይም ከምሰሶዎች አንዱ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም ይላሉ።
የአቅርቦት ሰንሰለትን በቀላል ቋንቋ ለማስረዳት ወደ አርባምንጭ እንሂድ። አርባምንጭ የፍራፍሬ ሃገር ናት። በተለይ ደግሞ ሙዝ።
አንድ ፍሬ ሙዝ አርባምንጭ ላይ ያለው ዋጋ እና አዲስ አበባ ተመሳሳይ አይደለም። እንዲሆንም ላይጠበቅ ይችላል። ለምሳሌ አንድ ፍሬ አርባምንጭ ከተማ 20 ሳንቲም ተሸጠ እንበል፤ አዲስ አበባ ሲደርስ ደግሞ 1 ብር [ምሳሌ ነው]።
ሙዝ አርባምንጭ በቅሎና አድጎ አዲስ አበባ አሊያም ሌሎች ከተሞች የሚደርሰው የአቅርቦት ሰንሰለትን ተሳፍሮ ነው።
አምራች አለ። ከአምራች ተቀብሎ የሚያከፋፍል አለ። ከአከፋፋይ ተቀብሎ የሚቸረችር ይኖራል። ከዚያ ገዥ።
ስለ አቅርቦት ሰንሰለት ይህን ካልን ከለት'ተዕለት ኑሯችን ጋር ያለውን ቁርኝት እንይ።
አንድ የኢትዮጵያ ኑሮ ሁኔታ የሚያሳስባቸው ግለሰብ፣ አማራ ክልል ውስጥ ያለች አንድ ሽንኩርት አምራች ሥፍራ ያለው የሽንኩርት ዋጋና ከተማ ሲደርስ ያለው ዋጋ እጅግ የተለያየ መሆኑ ያሳስባል ሲሉ በትዊተር ገፃቸው አሥፍረው ነበር።
ለመሆኑ የአቅርቦት ሰንሰለትና የኑሮ ውድነት ግንኙነት አላቸው? የአቅርቦት ሰንሰለቱ የተቃና ቢሆን ኖሮ ለውጥ ይመጣል?
"እርግጥ ነው ግንኙነት አላቸው። ነገር ግን ሌሎች ምክንያቶች የበለጠ ተፅዕኖ አላቸው" ይላሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ።
"ያለፈውን አሥር ዓመት ብናይ ኢሕአዴግ በገጠርም በከተማም መንገድ ሠርቷል። ግን ከአሥር ዓመት በፊት ያለውን ንረትና አሁን ያለውን ስታየው የዛሬው በጣም ትልቅ ነው። ስለዚህ ሌሎች ገፊ ምክንያቶች ናቸው ለዋጋ ንረቱ ምክንያት የሆኑት እንጂ ሰንሰለቱ ብቻ አይደለም።"
ፕሮፌሰር አለማየሁ እነዚህ 'ገፊ' ያሏቸውን ምክንያቶች ያስረዳሉ። ባደረግኩት ጥናት እነዚህ ምክንያቶች አራት ናቸው ይለሉ።
"አንደኛው ምርታማነት ነው። ምርታማነታችን በሄክታር ሲሰላ በጣም የሞተ ነው። ለምሳሌ በአማካይ የእርሻ ምርታማነቱ የሚያድገው በዓመት በ2.5 ነው። ይህ ከሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ያለ ነው። በእያንዳንዱ የሰብል ዓይነት ሊለያይ ይችላል። ነገር ግን በአጠቃላይ በቂ አይደለም። በጥናቴ መሠረት ቁጥር አንድ ምክንያት ይህ ነው።
"ቁጥር ሁለት ያገኘሁት ምክንያት ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 12/13 ዓመታት ከተገቢው በላይ ብር ይታተም ነበር። ለምሳሌ 2000 ዓ.ም. ላይ የቁጠባ ሒሳብና የቼክ ሒሳብ ውስጥ ያለን ጨምሮ ጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ብር 67 ቢሊየን ነበር። አሁን 870 ቢሊየን ደርሷል። ይህ ማለት በአማካይ በ30 በመቶ ያድግ ነበር ማለት ነው ላለፉት 13 ዓመታት።"
ፕሮፌሰር ዓለማየሁ የብር መጠኑ ከ4 እና 5 በመቶ መብለጥ አልነበረበትም ሲሉ ይሞግታሉ።
ሶስተኛው ምክንያትም ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት ምሁሩ የኢትዮጵያ ብር አቅም ከዓመት ዓመት እየተዳከመ መምጣቱ ሌላኛው ሰበብ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
"በተለይ አዲሱ መንግሥት ከመጣ በኋላ የገንዘባችን አቅም እየወረደ ወይም እየረከሰ መጥቷል። የቀደመው መንግሥት ብዙ ብር ያትም ነበር። አዲሱ መንግሥት ደግሞ ብሩን እያረከሰው ነው። 80 በመቶ የሚሆኑ ከውጭ የምንገዛቸው ነገሮች የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና ነዳጅ የመሳሰሉ ናቸው። ስለዚህ ብሩ በረከሰ ቁጥር እነዚህ ዕቃዎች ይወደዳሉ። በ21 ብር የምትገዛው የነበረው አሁን በ40 ብር ነው የምትገዛው ማለት ነው።"
ፕሮፌሰር አለማየሁ ወደ አራተኛው ምክንያት ሲመጡ ከላይ ካነሳነው የአቅርቦት ሰንሰለት ጋር የተያያዘ ርዕስ ያነሳሉ።
"አራተኛው ምክንያት የነጋዴዎች አለአላግባብ ትርፍ ማጋበስ ነው። ለምሳሌ አንድ ሽንኩርት የሚያመርት ገበሬ የሚያገኘው ገቢና አዲስ አበባ ያንን ሽንኩርት የሚሸጠው ነጋዴ የሚያገኘው ሲነፃፀር ይዘገንናል። ገበሬው ምንም አያገኝም። ባደጉ ሃገራት አንድ ነጋዴ 20 በመቶ ካተረፈ ትልቅ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ መቶ ሁለት መቶ 'ፐርሰንት' ነው የምታተርፈው።
መፍትሄውስ?
ምሁሩ መፍትሄው ችግሮቹን 'መገልበጥ ነው' ይላሉ። እንዴት ማለት? በዝርዝር ያስረዳሉ።
"ለምሳሌ የመጀመሪያው መፍትሄ የሚሆነው ምርታማነትን ማሳደግ ነው። ለምሳሌ ስንዴ ኢትዮጵያ ምን ያክል ታመርታለች? በቆሎስ? ደቡብ አፍሪካ በቆሎ የኛን እጥፍ ነው የምታመርተው። ስለዚህ ምርታማነት ላይ መሥራት ነው አንዱ መፍትሄ።"
የምጣኔ ሃብት አስተማሪው ምርታማነት ማሳደግ ትልቅ 'ኢንቨስትመንት' ይጠይቃል ይላሉ። ነገር ግን በአጭር ጊዜ መፍትሄ ለማምጣት ሊደረግ የሚችለው በትናንሽ መስኖዎች ምርት ማምረት ነው ይላሉ።
"ጠቅላላ ምርታማነት እንኳ ባይጨምር በዓመት ሁለቴ አመርትን ማለት ነው። ለምሳሌ 5 ኩንታል የምታመርት ከሆነ በዓመት፤ በመስኖ ሁለት ጊዜ አመርትክ ማለት 10 ኩንታል ሆነ ማለት ነው። ስለዚህ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ሆኖ የሚታየኝ ይሄ ነው።"
ፕሮፌሰር አለማየሁ ካለው የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር አንፃር ወጣቶች በዚህ መስክ ላይ እንዲሰማሩ ያሻል ይላሉ።
እንደ ምሁሩ ከሆነ ሁለተኛው መፍትሄ ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ ማውጣት ነው። ካልሆነ ደግሞ የሚወሰደውን ብድር ከላይ ለተጠቀሰው መፍትሄ ማዋል ይገባል ይላሉ።
"የሚታተመው ብር ባለፉት ሶስት ዓመታት እየቀነሰ መጥቷል። ይሄ ቆንጆ እርምጃ ነው። ግን ከዚህ በተጓዳኝ የሚታተመው ብር የት ነው የሚገባው የሚለው ነው። የሚታተመው ብር ምርታማነት ላይ ቢጠፋ ችግር አልነበረውም ነበር። የመጀመሪያውን ችግር በፈታ ነበር።"
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ከጠ/ሚ ኃይለማርያም ዘመን ጀምሮ ብር 'ዲቫሉዌት' አልያም አቅሙ መውረድ የለበትም በማለት ሲሞግቱ እንደነበር ይናገራሉ።
"ፈረንጆቹ የሚነግሯቸው 'ኤክስፖርት' [የወጪ ንግድ] ይጨምራል፤ 'ኢምፖርትን' [የገቢ ንግድ] ይቀንሳል እያሉ ነው። ባለፉት ሶስት ዓመታት እኛ ማየት አንደቻልነው ኤክስፖርት አልጨመረም፤ ያው ባለፉት አስር ዓመታት በነበረበት [3 ቢሊዮን ዶላር] እንዳለ ነው። ኢምፖርቱ አይቀንስም [ወደ 17 ቢሊዮን ዶላር ነው]። ብርን የማርከስ ጎንዮሽ ጉዳት ከውጭ የሚመጣ ነገር በሙሉ ድሮ በ20 ብር የነበረው አሁን ወደ 40 ከፍ ማለቱ ነው። ይህ ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል።"
ፕሮፌሰሩ ወደ አራተኛው መፍትሄ ሲመጡ የአቅርቦት ሰንሰለቱ የተስተካከለ ቢሆን ኖሮ የምርት ዋጋ እጅጉን ይቀንስ ነበር ይላሉ።
"ያለው አማራጭ መቆጣጠር ነው። ነገር ግን ነጋዴን ተቆጣጥረህ አትዘልቀውም። አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ነጋዴዎች አሉ። ይሁንና ልቆጣጠር ብትል ችግር ሊፈጠር ይችላል።
"ስለዚህ እኔ የሚታየኝ መፍትሄ ምንድነው፤ በግልና በመንግሥት ትብብር በየቀበሌው ገበያዎችን መመሥረት ነው። በተለይ መሠረታዊ ዕቃዎችን ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ። የአምራቾችና የሸማቾች ማሕበር የሚባሉ አሉ። ነገር ግን በሌብነትና በሙስና የተዘፈቁ ናቸው። ስለዚህ የትርፍ ህዳጉን ወስነህ 'ፕሮፌሽናል' የሆነ በግልና በመንግሥት የሚተዳደር [ፐብሊክ ኤንድ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ] ብትመሠርት አንድ መፍትሄ የሚሆን ይመስለኛል።"
ምሁሩ እነዚህ ገበያዎች መሠረታዊ ለሆኑ ነገሮች ብቻ ነው መሆን ያለባቸው ይላሉ።
"ለዚህ ቆንጆ ምሳሌ 40ና 50 ዓመታት ያገለገሉ ልብ የማንላቸው ተቋማት አሉ። ኢትፍሩትና ከነማ ፋርማሲ የሚባሉ። የእነዚህን ተቋማት 'ስትራክቸር' ማጥናትና በዚያ መሠረት ማቋቋም ይቻላል።"
የአቅርቦት ሰንሰለት በኢትዮጵያና በጎረቤት ሃገራት
ጎረቤት ሃገር ኬንያ ሁለተኛ ሃገሬ ናት የሚሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ የኬንያ መንግሥት ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በገበሬውና በሸማቹ መካከል ያለውን የዋጋ ክፍተት በማጥበብ ትርፉን መልሶ ለገበሬ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት እየዘረጋ እንደሆነ ይናገራሉ።
"ዓላማው ትርፉን ወስዶ ለገበሬው ጥቅም ማዋል ነው። ለምሳሌ የጤና ተቋማትን መገንባት፤ ትምህርት ቤት ማሠራት የመሳሰሉትን ለማቋቋም ነው የሚተልመው ይህ ሥርዓት።"
ይህን እየቀረፁ ያሉት ኬንያዊ ባለሙያ ልክ እንደ ራይድ ወይም ኡበር ያለን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከሩ እንዳሉ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
"ይህ 'ሲስተም' በኤሌክትሮኒክ አማካይነት ምርቶችንና ሸማቹን ማገናኘት ነው ዓላማው።"
ኬንያ ከኛ የሚለያት ቁጥሩ አነስተኛ የሆነና የተደራጀ ነጋዴ መኖሩ ነው ይላሉ ምሁሩ። ስለዚህ ይህ ለቁጥጥር ይመቻል ሲሉ ልዩነቱን ያስረዳሉ።
"እኛ አንድ 15-20 ዓመት አይቀረንም ብለህ ነው ኬንያ አሁን ያለችበት ለመድረስ?" የሚሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ ኢትዮጵያ መወዳደር ያለባት ከነ ሩዋንዳና ማላዊ ጋር ነው ይላሉ።
ምሁሩ ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉ 'ኋላ ቀር መሆናችን ገብቶን ወደ መፍትሄው በፍጥነት ማምራት አለብን' ይላሉ።















