ኦሎምፒክ፡ አትሌት ቀነኒሳ ሰሚ ካጣሁ የዓለም አቀፉን የኦሎምፒክ ባንዲራ ወክዬ ልወዳደር እችላለሁ አለ

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Pool

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አገሬን ወክዬ እንዳልሳተፍ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተደጋጋሚ ክልከላ ይደረግብኛል አለ።

አትሌት ቀነኒሳ በቅርቡ ለቶኪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ምርጫ ጋር በተያያዘ ላቀረብኩት ቅሬታ በቂ ምላሽ የማይሰጠኝ ከሆነ በግል የዓለም አቀፉን የኦሎምፒክ ባንዲራ ወክዬ ልወዳደር እችላለሁ ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

line

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ሚያዝያ 19/2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በመጪው የቶክዮ ኦሊምፒክ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ተወዳድረው እንደ አዲስ እንዲመረጡ ወስኖ ነበር።

ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን አወዳድሮ መምረጥ አስፈላጊ መሆኑ በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ፣ በአሰልጣኞች እና በአትሌቶች ጭምር በጋራ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም መሰረተ ፌዴሬሽኑ ሚያዚያ 28 በሰበታ ከተማ ለሚካሄደው ወድድር አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ ለ12 ወንድ እና ለ8 ሴት አትሌቶች ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ውድድሩም በታቀደለት ቀን ተካሂዶ በሁለቱም ጾታ ከ1-5ኛ የወጡ አትሌቶችን ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል።

line

የቀነኒሳ ቅሬታ ምንድነው?

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2020 ሊካሄድ ታቅዶ በነበረው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ለመወዳደር በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ተመርጦ እንደነበረ ያስታውሳል።

ይሁን እንጂ ፌዴሬሽኑ በቅርብ ጊዜያት ውድድር ስላልተካሄዱ የአትሌቶችን ብቃት ለመለየት የአገር ውስጥ ውድድር በማካሄድ ለመምረጥ ማሰቡ በአትሌት ቀነኒሳ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።

አትሌት ቀነኒሳ ለቢቢሲ ሲናገር፤ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የነበረው ሕግ በመቀየር በአገር ውስጥ ውድድር የማራቶን ተወዳዳሪዎችን ለመመርጥ መወሰኑ አግባብ አይደለም።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አትሌት ቀነኒሳ ከእርሱ በተጨማሪ ሌሎች አትሌቶችም በዚህ የፌዴሬሽኑ ወሳኔ ላይ ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል ይላል።

"ሌሎች አትሌቶችም ቅሬታ አቅርበዋል። ስብሰባውን ረግጠው የወጡ ልጆችም ነበሩ። ነገር ግን የእነርሱ ቅሬታ አልተሰማም። ለምንድ ነው በምርጫ የምታደርጉት ብለው ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረው ነበር። ለኦሊምፒኩ ቀጥታ የምትመርጡን ከሆነ እንመጣለን፤ አሁን የማጣሪያ ውድድር ለማድረግ ስላልተዘጋጀን ማጣሪያው ላይ መሳተፍ አንፈልግም ብለው የወጡ ልጆች አሉ" በማለት ያስረዳል።

አትሌት ቀነኒሳ በዓለም አቀፍ መድረክ በማራቶን ውድድር ያስመዘገበው ሰዓት የዓለማችን ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት መሆኑን ያስታውሳል። በጥሩ ጤንነት እና አቋም ላይም እንደሚገኝ ጨምሮ ተናግሯል።

አትሌት ቀነኒሳ በጥሩ ብቃት እንደምትገኝ ካመንክ ለምን ፌዴሬሸኑ ባዘጋጀው የማጣሪያ ውድድር ላይ አልተሳተፍክም ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፤

"ሲጀመር ውድድሩ መደረጉ በራሱ ፍትሃዊ አይደለም። እኔ የተወዳደሩት አትሌቶች ውጤት ያልተገባ ነው ማለቴ አይደለም። ውድድሩን ላደረጉትም ላላደረጉትም ክብር አለኝ። ነገር ግን እንደሚታወቀው ባለፈው ዓመት በሰዓታችን መሠረት ስድስት አትሌቶች ተመርጠናል። አሁን አዳዲስ አትሌቶች ተጨምረው ነው ውድድሩ የተደረገው። ይህ ራሱ ፍትሃዊ አይደለም" ይላል።

አትሌት ቀነኒሳ፤ በኢትዮጵያ ለማራቶን ውድድር የአገር ውስጥ ማጣሪያ ከተደረገ በርካታ አስርት ዓመታት ማለፋቸውን ገልጾ፤ ይህ ውድድር የ2020 ኦለምፒክ ነው። ውድድሩ ወደ 2021 ስለተዘዋወረ እንደ አዲስ ውድድር ሊታይ አይገባም ይላል።

በተጨማሪም "ውድድሩ ሶስት ወራት ቀርተውት እያለ ለምን ማጣሪያ ማድረግ አስፈለገ? ሕጉ ለምን ተቀየረ? ይህን የማድረግ ሐሳብ ካላቸው ለምን ከዓመት በፊት አላደረጉትም። ይህ ማራቶን ነው። 10 ሺህ ወይም 5 ሺህ አይደለም። የትራክ ሩጫ አይደለም" ብሏል።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Ian MacNicol

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

የዓለም ሻምፒዮናው አትሌት ቀነኒሳ ጥቂት ወራት ለቀሩት ወድድር አሁን ላይ ሌላ የማራቶን ማጣሪያ ማድረግ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ያስረዳል።

"እንደ አትሌት ይሄ ይጎዳል። ቶሎ 'ሪከቨር' [ሊያገግም] የሚችል አትሌት አለ፤ ቶሎ የማያደርግ አለ። ከሶስት ወራት በላይ የሪከቨሪ ጊዜ የሚወስድበት አትሌትም ይኖራል። በትንሹ አንድ አትሌት ሁለት ሳምንት የማገገሚያ ጊዜ ያስፈልገዋል። እስከዚያው ቀላል ልምምድ ነው የሚያደርገው። ስለዚህ ይህን ውድድር ከአራት ወራት በፊት ሊያደርጉ ይችላሉ። ደግሞ ማጣሪያውን እንደሚያደርጉ ከዓመት በፊት አስቀድመው ማሳወቅና ሕጋቸው ላይ ማስቀመጥ ነበረባቸው" በማለት ይገልጻል።

'ግላዊ ጥቃት አለ'

በኦሊምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ በሪዮ ኦለምፒክ ተሳታፊ ሳይሆን መቅረቱን አስታውሶ፤ "ፐርሰናል [ግላዊ] ነው፤ አዎ። ፌዴሬሽን ውስጥ ያሉት ሁሉም ናቸው ባይባልም ከአብዛኛዎቻቸው ግላዊ ጥቃት አለ" በማለት ተናግሯል።

አትሌት ቀነኒሳ አትሌቲክ ፌዴሬሽን ውስጥ ተደጋጋሚ የሆኑ የአሰራር ለውጦች አሉ በማለት ይከስሳል።

"ፌዴሬሽን ውስጥ አዲስ ሰው በተቀጠረ ቁጥር አዳዲስ ሕጎች የሚያወጣ ከሆነ፤ ወጥ የሆነ ሕግ ከሌለ ከቴክኒክ ጀምሮ እስከ አሰልጣኝ ድረስ ሁሉም የግል ፍላጎት እንዳለው እንደሚያሳይ አትጠራጠር። ሁሉም አትሌቶች የተለያየ 'ማኔጅመንት' አላቸው። ሁሉም የራሱን አትሌት ነው የሚደግፈው፤ የራሱ አትሌት ነው ኦሊምፒክ ላይ እንዲሰለፍለት የሚፈልገው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች እንደየቅርበታቸው ፌዴሬሽን ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ ጫና በመፍጠር የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሟላ መንገድ ነው የሚፈጥሩት። አዲስ የሚመጣው አመራር ከዚህ በፊት የነበረውን ሕገ ደንብ ተከትሎ ነው ምርጫ ማካሄድ የሚገባው እንጂ እንደ ወዳጅነትህ ሌላውን የምታጠቃበት አሠራር መዘርጋት የለብህም" ይላል።

'በግል ልወዳደር እችላለሁ'

አትሌት ቀነኒሳ ቅሬታውን በደብዳቤ ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማቅረቡን ገልጾ፤ ለቅሬታው ምላሽ የማይሰጠው ከሆነ በግል የዓለም አቀፉን የኦሎምፒክ ባንዲራ ወክዬ ልወዳደር እችላለሁ ብሏል።

"እንደሚታወቀው የሩስያ አትሌቶች በአበረታች መድኃኒት ምክንያት መወዳደር ሳይችሉ ቀርተው ነበር። በዚህን ጊዜ ግን በግላቸው መወዳደር ችለው ነበር። ውድድሩን ሲያሸንፉ የዓለም አቀፉን የአትሌቲክስ ባንዲራ ያነሳሉ። ይህን ማድረግ ልቻል አልቻል የማውቀው ነገር ስለሌለ ከማናጀሬ ጋር በመነጋገር ያንን ዕድል የማገኝበት ሁኔታ አመቻቻለሁ ለማለት ነው።"

አትሌት ቀነኒሳ ከዚህ ውሳኔ መድረስ ቀላል አለመሆኑን እና የአገርን ባንዲራ ማንሳት ሳይቻል በኦሎምፒክ ኮሚቴ ባንዲራ መወዳደር ስሜት እንደሚጎዳ ገልጿል።

"እርግጥ ነው ስሜት ይጎዳል። ነገር ግን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከዚህ በፊትም የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ሪዮ ላይ በተደረገው ኦሊምፒክ እንዲሁ ውድድር ሲደርስ ነው አዲስ ሕግ ያስቀመጡት። እና ይህ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ስምንትና ዘጠኝ ዓመት ሙሉ እሰለፋለሁ ብዬ ስጠብቅ አሁንም ደርሶ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ምን ታደርገዋለህ? አማራጭ ስላጣሁ ነው እንጂ ሳይሰማኝ ቀርቶ አይደለም።"

line

በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ለተነሱ ቅሬታዎች የኤትሌቲክ ፌዴሬሽን አስተያየት ለማካተት ያደረገውነው ጥረት አልተሳካም።