አትሌቲክስ፡ ቀነኒሳ በቀለ በጉዳት ምክንያት ከለንደን ማራቶን ራሱን አገለለ

የፎቶው ባለመብት, Pool
በረዥም ርቀት ሩጫ ከፍተኛ ዝናን የተጎናፀፈው ቀነኒሳ በቀለ ባቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ከለንደን ማራቶን ራሱን አግልሏል።
በመጪው እሁድ በሚካሄደው የለንደን ማራቶን ውድድርም እንደማይሳተፍ አዘጋጁ፣ ቨርጂን መኒ ለንደን ማራቶን በድረገፁ አስታውቋል።
በባለፈው አመት መስከረም ላይ በርሊን በተካሄደው ማራቶን በ2፡01፡41 ሰዓት ውድድሩን አሸንፎ የነበረው ቀነኒሳ የለንደኑ ከዚያ በኋላ ሁለተኛ ውድድሩ ቢሆንም በዚህ ውድድር ላይ አለመሳተፉ እንዳሳዘነው ገልጿል።
"በእሁዱ ውድድር ላይ ባለመሳተፌ በጣም አዝኛለሁ" በማለት የገለፀው አትሌቱ
"በወረርሽኙ ምክንያት የቡድኑን አባላት ሳላገኝ መዘጋጀቱ ፈታኝ ነበር። ሆኖም በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ የነበርኩ ቢሆንም በግራ ባቴ በኩል የሚነዘንዝ ህመም በባለፉት ሳምንታት እየተሰማኝ ነው።
ሁለት ፈጣን ስልጠናዎች ካደረግኩ በኋላም ነው የህመሙ ስሜት እየተሰማኝ ያለው" ብሏል።
አክሎም "ህመሙ ከተሰማኝ ጀምሮም ህክምና እያደረግኩ የነበረና ለውድድሩም ዝግጁ እሆናለሁ ብዬ በሙሉ ልቤም አስቤ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ግን በጣም ከፍቶ በዚህ ሁኔታ መወዳደር እንደማልችል አወቅኩ" በማለት አስታውቋል።
"የለንደኑ ማራቶን ለኔ በጣም ጠቃሚ ነበር። ባለፈው አመት በበርሊን ያደረግኩት ውድድር ከፍተኛ በራሰ መተማመኔን ጨምሮልኛል፤ መነቃቃትም ፈጥሮልኛል። እናም ያንን ለማሳየት በከፍተኛ ሁኔታ ጠንክሬ ዝግቴን እያደረግኩ ነበር።
በአለማችን ያሉ በርካታ ሰዎች ይህንን ውድድር በጉጉት እየጠበቁት እንደነበር አውቃለሁ። አድናቂዎቼን፣ አዘጋጆቹንና ተወዳዳሪዎቹን ቅር በማሰኘቴ አዝናለሁ። ለማገገምና እንደገና ዝግጁ ለመሆን ጊዜዬንም እወስዳለሁ። በሚቀጥለው አመትም ለንደን እንደምመለስ ተስፋ አደርጋለሁ" ብሏል።
የቨርጂን መኒ ለንደን ማራቶን የዝግጅት ዳይሬክተር በበኩላቸው "አለም የቀነኒሳ በቀለንና የኢሉይድ ኪፕቾጌን ውድድር በጉጉት እየተጠበቀ ነበር። ቀነኒሳ ምን ያህል ቅር እንደተሰኘና እንዳዘነ እናውቃለን። በፍጥነትም እንዲያገግም እንመኝለታለን"ብለዋል።
ሆኖም ይሄ ውድድር የሁለት ሰዎች ብቻ ሳይሆን በማራቶን ውድድር አስሩ ፈጣን ከሚባሉት አራቱ የሚሳተፉበትና ስድስቱ ደግሞ የ2፡05 ሬኮርድን የሰበሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ከነዚህም መካከል በባለፈው አመት ሁለተኛና ሶስተኛ የወጡት ሞስነት ገረመውና ሙሌ ዋሲሁን ይሳተፋሉ ማለታቸውንም በድረገፁ ላይ ሰፍሯል።
በመጪው እሁድ በበይነ መረብ በሚካሄደው የለንደን ማራቶንም ከ109 አገራት የተውጣጡ 45 ሺህ ያህል ሰዎች በውድድሩ ለመሳተፍ ተመዝግበዋል። ይህ አርባኛው ውድድርም ከቤታቸው ወይም ካሉበት ሆነው በኢንተርኔት አማካኝነት ተሳታፊ ይሆናሉ።












