ቀነኒሳ 'ከሞት እንደመነሳት' ነው ባለው ሁኔታ ማራቶንን አሸነፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሩጫው መድረክ ጠፍቶ የከረመው የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለ ዛሬ በተካሄደው የበርሊን ማራቶን ላይ ለውድድሩ ክብረወሰን ሁለት ሰከንዶች የቀሩት ውጤት በማስመዝገብ አሸነፈ።
ቀነኒሳ በቀለ ከማራቶን ክብረ ወሰን ቀጥሎ ሁለተኛው ምርጥ ሰዓት ነው በተባለ 2 ሰዓት ከአንድ ደቂቃ ከአርባ አንድ ሰከንድ በማስመዝገብ ነው የበርሊን ማራቶንን ማሸነፍ የቻለው።
ቀነኒሳ ከውድድሩ በኋላ ለቢቢሲ እንደተናገረው የዚህን ውድድር ውጤት "ከሞት እንደመነሳት ነው የምመለከተው" ሲል ጠቅሶ ምክንያቱንም ሲያስረዳ ለረጅም ጊዜ በህመም ምክንያት ከሩጫ ውድድር እርቆ መቆየቱን ይገልጻል።
በቀጣይ በጤናው ላይ ምንም ችግር ካላጋጠመው የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰንን ለመስበር እንደሚሰራ ተናግሯል።
"ህመም ላይ ስለነበርኩ ክብረወሰኑን ለመስበር የሚያስችል በቂ ልምምድ አላደረግኩም" የሚለው ቀነኒሳ ለዚህ ውጤት ያልተቋረጠ የወራት ልምምድ እንደሚያስፈልግ ጠቅሶ "በቅርቡ የማራቶን ክብረ ወሰን ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል" ሲል ተናግሯል።
በሴቶቹ የማራቶን ውድድር አንደኛና ሁለተኛ በመውጣት ኢትዮጵያዊያን ያሸነፉ ሲሆን አንደኛ አሸቴ በከሬ ሁለተኛ ማሬ ዲባባ በመሆን ተከታትለው አሸናፊነቱን ተቆጣጥረውታል።
በወንዶቹ ውድድር በአንደኛነት ካሸነፈው ቀነኒሳ በቀለ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያኑ ብርሐኑ ለገሰ ሁለተኛ እንዲሁም ሲሳይ ለማ ሦስተኛ በመውጣት በሁለቱም ጾታዎች የበርሊን ማራቶን ውድድር በኢትዮጵያዊያን የበላይነት ተጠናቋል።
የ37 ዓመቱ ቀነኒሳ በቀለ ከዚህ በፊት በተካሄዱ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን ክብረ ወሰኖችንም ያሻሻለ ኮከብ አትሌት ነው።
በኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ የተያዘው የማራቶን ክብረወሰን ላይ ለመድረስ ሁለት ሰከንዶችን ዘግይቶ ውድድሩን የጨረሰው ቀነኒሳ "አዝናለሁ፤ እድለኛ አልነበርኩም። ነገር ግን ተስፋ አልቆርጥም፤ ክብረ ወሰኑንም ለመስበር እችላለሁ" ሲል ከበርሊኑ ድሉ በኋላ ተናግሯል።












