በዶሃ የሴቶች ማራቶን 28 ሯጮች አቋርጠው ወጡ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ትናንት እኩለ ለሊት በኳታር፣ ዶሃ በተጀመረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካሄደው የማራቶን ሩጫ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ማቋረጣቸው ተሰማ።
ሩጫውን በበላይነት ኬኒያዊቷ ሩት ቼፔንጌቲች ያሸነፈች ሲሆን፤ ከ68 ተወዳዳሪዎች 28ቱ በሙቀቱ ከባድነት ምክንያት አቋርጠው መውጣታቸው ተዘግቧል።
እኩለ ለሊት ላይ የተደረገውን ይህ የሴቶች የማራቶን ውድድር ካቋረጡ ተወዳዳሪዎች መካከል ኢትዮጵያዊቷ ሩቲ አጋ አንዷ ነች።
የውድድሩ አዘጋጆች ከዋናው ውድድር ቀድመው የማራቶን ውድድሩ እንዲካሄድ ያደረጉት የአየር ጠባዩ ለማራቶን ምቹ ላይሆን ይችላል በሚል እንደሆነ ተነግሯል።
የሴቶች ማራቶን ሲካሄድ፤ የሙቀት መጠኑ 32 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን፤ ወበቁ ደግሞ ከ70 በመቶ በላይ ነበር ተብሏል።
የኢትዮጵያ ማራቶን አሰልጣኝ ሀጂ አዲሎ ሮባ፤ የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊዋ ሩቲ ነጋን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ተወዳዳሪዎች ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።
"በአገራችን ማራቶንን በዚህ የአየር ጠባይ መሮጥ የሚታሰብ አይደለም" ካሉ በኋላ "ምን ያህሎቹ እንደሚጨርሱ ለማየት ጓጉቻለሁ" ብለዋል።
የ23 ዓመቷ ቼፔንጌቲች ሩጫውን በ2 ሰዓት ከ32 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ በማጠናቀቅ ወርቅ ስታገኝ፤ የባህሬን ዜግነት ያላት ሯጭ ሁለተኛ፣ ናሚቢያዊቷ ሯጭ ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።
ቼፔንጌቲች፤ "በእንዲህ አይነት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ አሸንፋለሁ ብዬ አልጠበቅኩም" በማለት ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ተናግራለች።
የብሪታኒያ ፈጣን የማራቶን ሯጭ ቻርሎቴ ፑርዱኤ እና ሌሎች ታዋቂ ሯጮችም አቋርጠው ከወጡት መካከል ናቸው።












