ኮሮናቫይረስ፡ "መኖር የሚፈልግ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት" ቀነኒሳ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኦሎምፒክ አሸናፊውና የአምስት ሺህና የአስር ሺህ ክብረወሰን ባለቤት የሆነው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ማኅበረሰቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክሮች በሥራ ላይ እያዋለ አይደለም ሲል ስጋቱን ለቢቢሲ ተናገረ።
የዓለም ሕዝብ እንደ ቅጠል እየረገፈ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እራሱን ከወረርሽኙ መጠበቅ ቢኖርበትም ይህ እየተተገበረ አለመሆኑ እንዳሳሰበው አትሌት ቀነኒሳ ገልጿል።
ጨምሮም "ሕዝቡ በባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ተቀብሎ ራሱን የማይጠብቅ ከሆነ አገሪቱ ትልቅ ፈተና ሊገጥማት ይችላል" በማለት አሳስቧል።
ቀነኒሳ እንዳለው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጤና መሰረተ ልማት እምብዛም ጠንካራ አለመሆኑን በመገንዘብ ሕዝቡ የሚሰጠውን ምክር በተግባር መተርጎም ይጠበቅበታል ሊል መክሯል።
"ነገን በማሰብ መኖርን ያለመ ሰው፤ በዚህ ወቅት ለራሱና ለቤተሰቡ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል" በማለት ጤንነት ካለ ወደ ፊት ብዙ ነገር መሥራት ይቻላል ሲል ቀነኒሳ ለጥንቃቄ ትኩርት እንዲሰጥ መክሯል።


የበሽታው መስፋፋት ያሳሰበው ቀነኒሳ የግል ንብረቱ የሆነውንና በሱሉልታ የሚገኘውን የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ መንደር በኮሮናቫይረስ ለተጠረጠሩ ሰዎች ለይቶ ማቆያነት እንዲውል መስጠቱንም ገልጿል።
ቀነኒሳ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከመምከር ባሻገር እሱም ድሃን ከሃብታም ከማይለየው በሽታ እራሱንና ቤተሰቡን ለመጠበቅ ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በዚህም መሰረት ኮሮናቫይረስ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ከሰማ ጀምሮ ልምምድ የሚያደርገው ብቻውን እንደሆነ በመግለጽ "እያንዳንዱ ሠው የሚጠበቅበትን ጥንቃቄ ካደረገ ይህንን በሽታው መቆጣጠር ይቻላል" ብሏል።
ነገር ግን "ብዙ ሰው እየተነገረ ያለውን እየሰማ አይመስልም፤ ይህንን ጉዳይ እንደ ቀላል የሚመለከተው ይመስለኛል" በማለት ቀነኒሳ ያጋጠመውን ይናገራል።
በዚህ ወቅት "ለመጨበጥና አብሮ ፎቶ ለመነሳት የሚጠጉ ሰዎች ያገጥማሉ።. . . አይሆንም ስትላቸው ደግሞ የሚናደዱ ሰዎች አሉ" በማለት የዓለም ጤና ድርጀት የኮቪድ-19 ወረርሽን ስርጭትን ለመከላከል ይረዳሉ በማለት ያስቀመጣቸውን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስታውሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከኮረናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በጃፓን ሊካሄድ የነበረው የኦሊምፒክ ውድድርን አስመልክቶ የተጠየቀው ቀነኒሳ በአሁኑ ወቅት 38 ዓመት ሊሞላው እንደሆነ በመናገር፤ ውድድሩ በአንድ ዓመት መራዘሙ ምንም ተጽዕኖ እንደማያመጣበት ገልጿል።
"አንድ እና ሁለት ዓመት ምንም ለውጥ አያመጣም። እደርሳለሁ፤ እሄዳለሁ እቅዴንም በተግባር ለማዋል እችላለሁ" ብሏል።
በተጨማሪም ውድድሩ ቢሳተፍ ደስተኛ እንደሚሆን ገልጾ "ሁልጊዜም ፈጣሪ ያለው እንጂ ሠው ያለው አይሆንም" በማለት ዓለምን እያስጨነቀ ያለው በሽታ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ሕዝቡ የሚነገረውን ተግባራዊ እያደረገ መፀለይ እንዳለበት መክሯል።












