ኮሮናቫይረስ፡ ወሲብና ኮቪድ-19ን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች

ስዕል

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

'ወሲብ ብፈጽም ኮሮናቫይረስ ሊይዘኝ ይችላል?' በእርግጠኝነት ይህ ጥያቄ በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ቢያቃጭልም ለመጠየቅ ግን እንሸማቀቃለን።

ሃቅንና ብዥታን ለመለየት ጥያቄዎን ለጤና ሙያዎች በማቅረብ ቢቢሲ ተገቢውን ምለሽ አግኝቷል። የቀድሞው የላቭ አይላንድ አወዳዳሪ ዶ/ር አሌክስ ጆርጅ እና የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ አሊክስ ፎክስ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል። በጥያቄዎቹ ዙሪያ ሁለቱም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ወሲብ መፈጸም ችግር ያመጣል?

ዶ/ር አሌክስ ጆርጅ፡ ግንኙነት ውስጥ ከሆናችሁ.… አብራችሁ የምትኖሩ ከሆነና ተመሳሳይ አካባቢ ውስጥ ካላችሁ የሚቀየር ነገር አይኖርም። ነገር ግን አንደኛችሁ ብቻ የኮሮናቫይረስ ምልክት ካሳያችሁ፤ ማኅበራዊ እርቀታችሁን መጠበቅና እራስን መለይት ያስፈልጋል። ኑሯችሁ አንድ ቤት ውስጥ ቢሆንም እንኳ ማለት ነው። እንደ ዓለም አቀፍ መስፈርት ቤት ውስጥ እንኳ ቢሆን ማንም ሰው ሁለት ሜትር መራራቅ እንዳለበት ይመከራል። በእርግጥ በአብዛኛው ይሄ ሲተገበር አይታይም።

አሊክስ ፎክስ፡ አንዳንድ ጊዜም እርሰዎ የሚሰማዎት ቀላል የኮሮናቫይረስ ምልክት ከታያብዎት የፍቅር አጋርዎም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ብለው ማሰቡ መልካም ነው። በመሆኑም ምንም ዓይነት ምልክት ካሳዩ ምልክቱ ምንም ይሁን ምን እራስዎን ከፍቅረኛዎ መለየት አለብዎት።

ከአዳዲስ ሰዎች ጋር የሚፈጸም ወሲብስ?

ዶ/ር አሌክስ፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በእርግጠኝነት መምከር የምችለው ባለንበት አስቸጋሪ ወቅት ከአዳዲስ ሰዎች ጋር ምንም አይነት ወሲብ መፈጸም የለብዎትም ነው። ምክንያቱም መዘዙ ቫይረሱን ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ወይም ደግሞ መቀበል ነውና።

አሊክስ ፎክስ፡ ደግሞም መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር፤ አንዳንድ ሰዎች ቫይረሱ ኖሮባቸው ነገር ግን ምንም የኮሮናቫይረስ ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። ስለዚህ ፍጹም ደኅንነት ቢሰማዎትም ወሲብ በሚፈጽሙበት ወቅት በሚፈጠረው መጠጋጋትና መሳሳም ምክንያት ቫይረሱ ከአንዱ ወደ ሌላው ይተላለፋል።

የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ አሊክስ ፎክስ እና ዶ/ር አሌክስ ጆርጅ

የፎቶው ባለመብት, PAUL COCHRANE/JESSIE WHEALEY

የምስሉ መግለጫ, የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ አሊክስ ፎክስ እና ዶ/ር አሌክስ ጆርጅ

በቅርቡ ተሳስሜያለሁ፤ ከቀናት በኋላ ያ ሰው የቫይረሱን ምልክት ማሳየት ጀምሯል። ምን ማድረግ አለብኝ?

ዶ/ር አሌክስ፡ በቅርቡ የሳሙት ግለሰብ ቫይረሱ እንዳለበት ካወቁ በፍጥነት እራስዎን ለይተው ያቆዩ። ምልክቶቹን በደንብ ይከታተሉ። ምልክት ማሳየት ከጀመሩ ተጨማሪ ጥንቃቄዎችን ያድርጉ። ህመሙ ከጠናብዎ ግን ለተጨማሪ ሕክምና ሐኪሞችን ማማከር ይኖርብዎታል።

አሊክስ ፎክስ፡ በግንኙነታችን ወቅት አንዳችን ለሌላኛችን ኃላፊነት ሊሰማን ይገባል። ለምሳሌ ከተሳሳሙ በኋላ ምልክቶቹን ቀድመው ማሳየት የጀመሩት እርሰዎ ከሆኑ ምልክት ማሳየት መጀመርዎን ለፍቅር አጋርዎ ቶሎ መንገር ይኖርብዎታል። በዚህ ሂደት ከሁለታችሁ መካከል ምልክት ያላሳዩት እርሰዎ እንደሆኑ ካወቁም በፍጥነት እራስዎን ይለዩ።

ኤች አይ ቪ አለብኝ፤ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭነቴ የሰፋ ነውን?

አሊክስ ፎክስ፡ በዚህ ጉዳይ ዶ/ር ሚካኤል ብራዲ ትልቅ ምክረ አስቀምጠዋል። በተከታታይ የኤችአይቪ መድኃኒት የሚወስዱ ከሆነና ጥሩ በሽታን የሚከላከሉ የነጭ ሕዋሳት ብዛት [የሲዲ4] ካለዎና በደምዎ ውስጥ ያለው የቫይረሱ መጠን ሊለይ በማይችል ደረጃ ከሆነ እርሰዎ በሽታውን የመቋቋም አቅምዎ ዝቅተኛ ነው ከሚባሉት መካከል አይደሉም። ይህ ማለት ኮሮናቫይረስ ቢይዝዎ ሕመምዎን የሚያፋፍም ተጨማሪ በሽታ የለብዎትም ማለት ነው። ነገር ግን ከኤችአይቪ ነጻ ነዎት ማለት ግን አይደለም።

ስለዚህ የኤችአይቪ በደምዎ ውስጥ ካለ የተለመደ መድኃኒትዎን የመውሰድ ተግባርዎን ሳያስተጓጉሉ ይቀጥሉ። የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ጨምሮ እራስን ለይቶ ማቆየትን የመሳሰሉ ትዕዛዞች ሲሰጡ ይፈጽሙ። ለሌሎች ሰዎች የሚሰጡ ማንኛቸውንም ትዕዛዞች ማክበርዎንም አይዘንጉ።

ኮሮና
Banner