ኮሮናቫይረስ፡ ባለስልጣኑ ወደ ለይቶ ማቆያ አልገባም በማለታቸው ታሰሩ

ጌዲዮን ሳቡሪ

የፎቶው ባለመብት, Gideon Saburi

አንድ የኬንያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን ከውጭ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ማንኛው ሰው መፈጸም ያለበትን ወደ ለይቶ ማቆያ የመግባት ግዴታን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታሰሩ።

የባሕር ዳርቻ የኬንያ ግዛት ኪሊፊ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ጌዲዮን ሳቡሪ በግድ ወደ ለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት ከገቡ በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸው ህክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ባለስልጣኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከተገኙባት ጀርመን ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ወደ ኬንያ የተመለሱት።

ምክትል አስተዳዳሪው በአሁኑ ወቅት ከበሽታው ሙሉ በሙሉ በመዳናቸው የኬንያ መንግሥት ያወጣውን ደንብ ተላልፈዋል በሚል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ባለስልጣኑ የኮቪድ-19 ቫይረስ ከተገኘባቸው በኋላ ከእርሳቸው ጋር የቅርብ ንክኪ ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ ከ100 በላይ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርገዋል። በዚህም የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ በመጣል ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል ተብሏል።

ምክትል አስተዳዳሪው በግድ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ከተደረጉ በኋላ ለአንድ ጋዜጣ "በሰዎች ላይ ለፈጠርኩት ችግር አዝናለሁ" ሲሉ መጸጸታቸውን ገልጸው ነበር።

በኬንያ ውስጥ እስከ አርብ ድረስ ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል 122ቱ ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ተረጋግጧል።

የሞቱ ሰዎች ቁጥርም አምስት የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም ቀደም ያለ የጤና ችግር የነበረበት አንድ የስድስት ዓመት ታዳጊ ኮሮናቫይረስ የጤንነቱን ሁኔታ አባብሶት ህይወቱ በማለፉ በኬንያ በበሽታው የሞተ በዕድሜ ትንሹ መሆኑ ተነግሯል።

ኬንያ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን ከምሽት አንድ ሰዓት እስከ ንጋት 11 ሰዓት የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ ብትጥልም እስካሁን ግን ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴን አልገደበችም።

ኮሮና
Banner