የቀነኒሳ በቀለ ክብረ ወሰን በኡጋንዳዊው ወጣት ተሰበረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኡጋንዳዲው ጆሹዋ ቼፕቴጌ በፈረንሳይ ሞናኮ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ለ16 ዓመታት በቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የነበረውን የ5000 ሜትር ሩጫ ክብረ ወሰን በሁለት ሰከንድ ማሻሻል ችሏል።
የ23 ዓመቱ ወጣት ባላፈው ዓመት በዶሃ የዓለም ሻምፒዮና ላይ የ10 ሺህ ሜትር አሸናፊ በሆነበት ወቅት የ5 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰንን ለማሻሻል እቅድ እንዳለው ገልጾ የነበረ ሲሆን በቅርብ ዓመታት ያሳካዋል ተብሎ ግን አልተገመተም ነበር።
ነገር ግን በትላንቱ የሞናኮው ውድድር ላይ 5 ሺህ ሜትሩን 12 ደቂቃ 35.36 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመጨረስ ቀነኒሳን ክብረ ወሰን መስበር ችሏል።
ቀነኒሳ በቀለ የዛሬ 16 ዓመት ክብረ ወሰኑን ሲያስመዘግብ ውድድሩን የጨረሰው በ12 ደቂቃ 37 ሰከንድ ከ35 ማይክሮ ሰከንድ ነበር።
በሚያስገርም ሁኔታ ቼፕቴጌ በዚህ ዓመት ክብረ ወሰን ሲሰብር ይሄ ሁለተኛው ነው። ባለፈው የካቲት ወር ላይ ደግሞ በተካሄደ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ ሰዓት ማሻሻል እንደቻለ ተነግሯል።
''ሞናኮ በጣም ልዩ ቦታ ናት፤ የዓለም ክብረ ወሰኖችን ልሰብርባት የምችልባት ከተማ ናት'' ሲል በደስታ ተውጦ ቼፕቴጌ ተናግሯል።
''በዚህ ዓመት በእውነቱ ሞራልን ሰብሰብ አድርጎ ለመስራት ትንሽ ይከብዳል፤ ምክንያቱም በወረርሽኙ ምክንያት ሰዎች ከቤታቸው አይወጡም፤ ብዙ ነገሮችም በፊት እንደነበሩት አይደሉም፤ ተቀይረዋል። ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ በማሸነፌ በጣም ደስተኛ ነኝ።''
በሌሎች ውድድሮች የዓለም ሻምፒዮኑ ኖዋህ ሊይስ የ200 ሜትር ውድድሩን በ19 ሰከንድ ከ72 ማይክሮሰከንድ በሆነ ሰዓት በማሸነፍ አይበገሬነቱን አሳይቷል።
ታናሽ ወንድሙ ጆሴፈስ ደግሞ በመጀመሪያው የዳይመንድ ሊግ ተሳትፎው እሱን ተከትሎ ሁለተኛ ሆኖ መጨረስ ችሏል።
ኖርዌያዊው ዓለም ሻምፒዮን ካርስተን ዋርሆልም ደግሞ በ400 ሜትር መሰናክል ውድድር በአውሮፓውያኑ 1992 በኬቨን ያንግ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበር ችሏል።
ለብቻው ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ሲሮጥ የነበረው ካርስተን ውድድሩን በ47 ሰከንድ ከ10 ማይክሮ ሰከንድ ጨርሷል።
ኬንያዊቷ ሄለን ኦቢሪ ደግሞ የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ውድድሩን በበላይነት ስታጠናቅቅ ሲፋን ሀሰን ደግሞ ጥቂት ዙሮች ሲቀሩት ውድድሩን አቋርጣ ወጥታለች።
5 ሺህ ብቻ ሰዎች እንዲመለከቱት በተፈቀደው የሞናኮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ ተመልካቾች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታቸው ሲሆን አካላዊ ርቀትም መጠበቅ ነበረባቸው።














