ከኑሮ ውድነት ጋር ግብ ግብ የገጠሙት የመንግሥት ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ረድኤት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኝ የሥራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ውስጥ ሠራተኛ ነች። በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱ ሁለቱም የመንግሥት ሠራተኞች ስማቸው ተቀይሯል። ሥራቸውን እንዳያጡ ሰግተዋል።
ትውልድ እና እድገቷ አዲስ አበባ ነው። "ከቤተሰቤ ጋር ባይሆን በ 2700 ብር ደሞዝ ተቀጥሬ እንዴት እኖር ነበር?" ስትል ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት የነበራትን የመነሻ ደመወዝ ትናገራለች። አሁን እንደምንም አምስት ሺህ ብር ይደርሳታል።
በቅርቡ ትዳር ይዛ ከቤተሰቦቿ ቤት የወጣችው ረድኤት የቤት ኪራይ ወጪዋ ሰባት ሺህ ብር ነው። እቁብም ትጥላለች፤ ሦስት ሺህ ብር። ይህ ከምግብ፣ ከጤና ከድንገተኛ ወጪዎች ውጪ ነው።
"ከባለቤቴ ጋር ተጋግዘን ነው እንጂ ብቻዬን ብሆን እንዴት ይቻላል" ትላለች። "ደመወዝ ከተቀበልኩ በኋላ ከ15 ቀን በኋላ እጄ ላይ ገንዘብ አይቀርም" ትላለች።
በምትሰራበት የሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው የገቡ አዲስ ሠራተኞች በተለይም ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ባልደረቦቿ እጅግ ከባድ የሚባል ኑሮ እንደሚገፉ ትናገራለች።
"ለእነሱ ምንም ከምንም አይሆንም። በጣም ያሳዝነኛል። ኪራይ እና ምግብ ችለው ለመኖር በጣም በችግር ነው የሚኖሩት" ስትል ረድኤት ታስረዳለች።
ለመሆኑ ቁጥሮች ምን ይላሉ?
በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛው ቀጣሪ እና የሥራ እድል ምንጭ መንግሥት ነው። የመንግሥት ሠራተኞች ቁጥር አንድ ሚሊዮን ከተሻገረ 10 ዓመት ሊሞላው ነው። እንደ የአለም ባንክ መረጃ ከሆነ የደርግ ስርዓት ሲወድቅ 300 ሺህ የማይሞሉ ከ 200 ሺህ የማያንሱ የመንግሥት ሠራተኞች በኢትዮጵያ ነበሩ።
ታዲያ ይህ ኃይል የዋጋ ግሽበት ወይም በተለምዶ የኑሮ ውድነት በሚባል ቀውስ ምክንያት እየተፈተነ ይገኛል። የዋጋ ግሽበት የገንዘብ የመግዛት አቅም ሲቀንስ የሚከሰት ነው። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው እኤአ ከ 1970 እስከ 2019 ባለው ግዜ ውስጥ ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት የተከሰተው በኢትዮጵያ ሚሌኒየም ወቅት ነበር።
በወቅቱ የዋጋ ግሽበቱ 44 ነጥብ 4 ሆኖ ተመዝግቧል። እንዲሁም ደርግ በወደቀበት ዓመት የዋጋ ግሽበቱ 36 በመቶ ደርሶ እንደነበር የዓለም ባንክ መረጃ ያመላክታል። ከ 2005 ዓም ጀምሮ ለሶስት ዓመታት በአንድ ዲጂት ተወስኖ እና ተረጋግቶ የቆየው የዋጋ ግሽበት በ 2009 ዓ.ም አስር በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
በተለይ በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት የተተኮሰው ግሽበት በተለይም የምግብ ምግብ ነክ ቁሶች ላይ የ 28̌ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ይህንን ጭማሪ በቀላል ቋንቋ የሚያብራሩት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ አብዱልመናን መሃመድ «የመንግሥት ሰራተኞች ባለፈው ሁለት ዓመታት ብቻ የደመወዛቸውን 40 በመቶ ለዋጋ ግሽበት አስረክበዋል» ይላሉ።
ይህ ማለት ከሁለት አመት በፊት 10 ሺህ ብር ደመወዝ የነበረው ሰው አሁን ላይ ባለው ግሽበት ሲሰላ ደመወዙ ወደ ስድስት ሺህ ብር አሽቆልቁሏል ማለት ነው።
መዘዙ ምንድነው?
በመንግሥት መዋቅር "የስራ ሂደት አስተባባሪ" ማለት ዋና አለቃ ማለት ነው። "የእነርሱ ደመወዝ ኪስ የሚሞላ፤ ተለቅ ያለ ነው" ሲሉ ከስራቸው ያሉ ባለሞያዎች ያስባሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ባለ አንድ ተቋም ቡድን መሪ የሆነችው እመቤት ግን "የያዝነው ቦታማ ትልቅ ነው፤ ግን እኛም በችግር ነው የምንኖረው" ትላለች። እሷም የወር ደመወዟ 15 ቀን አይቆይላትም።
እጇ ላይ 7500 ብር ቢደርስም አምስት ሺህ ብር "በጣም ጠባብ" ለምትላት ባለ ሁለት ክፍል ቤቷ ትከፍላለች። ሁለት ልጆች አሏት። "ቀነስ ያለ ትምህርት ቤት" ፈልጋ በወር 750 ብር ለአንድ ልጅ ትከፍላለች። ልጁን የሚያመላልስ ሰርቪስም ከፍያ ይጠይቃል።
"የመንግሥት ሠራተኛ ከሆንሽ ልጅሽን የሚይዝ ሞግዚት ያስፈልጋል። የዘይት፣ የጤፍ ዋጋ ሰማይ ነው። ምን ያልተወደደ ነገር አለ?" በማለት "መኖር አዳግቶኛል" ስትል እመቤት ኑሮዋን ትገልጸዋለች። ከስምንት ዓመት ጀምሮ ቤት ለማግኘት ብትቆጥብም ህልም ሆኖ መቅረቱም ያስቆጫታል። ነገር ግን ደመወዝ ይጨመር ይሆን ብላ ትጠብቃለች።
ረድኤትን እና እመቤትን የሚያስማማቸው አንድ ነገር አለ። በትምህርታቸው ለመግፋት ቢያቅዱም በገቢ እጥረት ምክንያት ትተውታል። ረድኤት እንደውም ጀምራ መክፈል ሲያቅታት ትታዋለች።
እንደ እመቤት ሁሉ ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች የላባቸውን ውጤት ለዋጋ ግሽበት ሲያስረክቡ ውጤቱ አሳሳቢ መሆኑን የኢኮኖሚ ተንታኙ አብዱልመናን ይናገራሉ።
"ይህ በኑሮ ደረጃ ላይ ከፍተኛ ጫና አለው። በተጨማሪም በሥራቸው ላይ ተነሳሽነት እና ደስታ ወይም እርካታ ማጣት ያጋጥማቸዋል። ይህ ለዝቅተኛ አፈጻጸም ብሎም ለሙስና በር ከፋች ነው" ሲሉ ባለሞያው ያብራራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መፍትሄው ምንድን ነው?
ለበርካታ ዓመታት የኑሮ ውድነቱ መሰረት የንግድ ሰንሰለቱ እንደሆነ ባለሞያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። ይህም በተለይ ምርት ከገበሬው እስከ ሸማቹ እስከሚደርስ ባለው ሠንሰለት መሃል ያሉ ደላላዎችን ተወቃሽ ያደረገ ነበር። መንግሥት በተለይም ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች ላይ የሚታየውን ጭማሪ «ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው፣ የጥቂቶች አሻጥር» ሲል በተደጋጋሚ ይሰማል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ በ 2013 የተባባሰው ግሽበት ግን ምክንያቶቹ ከተለመደው የዘለሉ እንደሆኑ የኢኮኖሚ ባለሞያው አብዱል መናን ይናገራሉ።
"አሁን ያጋጠመው የዋጋ ግሽበት ዋና መሰረቱ ብር ከሌሎች የውጪ ገንዘቦች አንጻር ዋጋው እንዲቀንስ በመደረጉ ምክንያት ነው። እንግዲህ ይህ የሆነው ለአስርት ዓመታት በዋጋ ግሽበት ሲናጥ ብሎም በፖለቲካ ያለመረጋጋት ውስጥ ባለ ኢኮኖሚ ላይ ነው" ሲሉ አዲስ ያሉትን ምክንያት ያብራራሉ።
ይህ እንዲቆም ካስፈለገም መንግሥት የብርን ዋጋ የመቀነስ ፖሊሲውን ማቆም አለበት ሲሉም አብዱልመናን ይመክራሉ። እንዲሁም የባንኮችን ተቀማጭ ገንዘብ በመጨመር እና በሂደት የቁጠባ ወለድን ከፍ ማድረግን ጨምሮ የገንዘብ ፖሊሲውን ቆንጠጥ ማድረግ ችግሩን ያቃልለዋልም ይላሉ።
ገንዘብ ዋጋ ለማጣቱ ምክንያት ከሚባሉት ነገሮች መካከል አንዱ መንግሥት እንዳሻው ከብሔራዊ ባንክ በመበደር ፈሰስ ማድረጉ ነው። ይህ ክስም አላግባብ የብር ኖት በማተም ኢኮኖሚው ውስጥ መክተት ሌላው ለዋጋ ግሸበቱ መሰረት እንደሆነ በባለሞያዎች ለአመታት ሲነሳ የቆየ ምክንያት ነው።
አብዱልመናን ይህንን ችግር ለመቆጣጠር ቁልፍ የሚሉት ሌላው መፍትሄም ይሄንን ይመለከታል።
"መንግስት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ መጠን መቀነስ ይገባዋል" ሲሉ ያክላሉ።
















