አዲስ አበባ ለውጭ አገር ሰራተኞች ለኑሮ ርካሽ ከሆኑት መካከል ናት ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
አዲስ አበባ መቀመጫቸውን በከተማዋ ላደረጉ የውጭ አገር ሰራተኞች ለኑሮ ርካሽ ከሆኑት መካከል አንዷ መሆኗን አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል።
የ209 ከተሞችን የቤት ኪራይ፣ ትራንስፖርትና ምግብ ዋጋ የገመገመው ይህ ጥናት አዲስ አበባን በ194ኛ ደረጃ አስቀምጧታል።
ጥናቱን ያከናወነው መርሰር የተባለ ድርጅት ሲሆን በባለፈው አመት በነበረው የኑሮ ውድነት ግምገማ አዲስ አበባ በ182ኛ ደረጃ አስቀምጧት ነበር።
በዚህ ጥናት መሰረት በአለም ውዷ ከተማ የቱርክሜኒስታን መዲና አሽጋባት ናት። በማዕከላዊ እስያ የምትገኘው የዚህች አገር መዲና ለውጭ አገር ሰራተኞች በውድነት በቁንጮ ስፍራ ተቀምጣለች።
በባለፈው አመት በውድነት ተቀምጣ የነበረችው ሆንክ ኮንግ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን የሊባኖሷ መዲና ቤይሩትና የጃፓን መዲና ቶክዮ ይከተላሉ።
መርሰር የተባለው ድርጅት እንዳስቀመጠው ይህንን ሪፖርት ለማጠናቀር 200 የሚገመቱ እቃዎችን ዋጋ እንዲሁም አገልግሎቶችን ገምግሜያለሁ ብሏል።
ይህም ጥናት ኩባንያዎችና መንግሥታት የውጭ አገር ሰራተኞቻቸውን ምን ያህል መክፈል እንዳለባቸው ጠቋሚ እንደሆነም ተገልጿል።
በመርሰር ከአንድ እስከ አስር ውድ ተብለው የተቀመጡት ከተሞች የቢዝነስ ማዕከላት የተባሉ ሲሆን ካላቸውም የምጣኔ ኃብት እድገት ጋር ተያይዞ በዕቃዎችና በአገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ ያሳዩ ናቸው።
በተለይም ይህ የዋጋ ግሸበት የታየው በቤት ኪራይና ሌሎች መሰረታዊ በሚባሉ ሸቀጦች ነው።
ነገር ግን የአሽጋባት የኑሮ ውድነት ከኢኮኖሚ እድገት ጋር የተያያዘ ሲሆን ካለው ከፍተኛ ግሽበት ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።
በነዳጅ ሃብቷ የምትታወቀው ቱርክሜኒስታን በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እየተናጠችም ሲሆን በርካቶችም ለከፋ ድህነትም ተዳርገዋል።
በቀድሞው የሶቭየት ህብረት አባል የነበረችው ቱርክሜኒስታን በዋናነት ለሩሲያ ነዳጅን በመላክ ነው ምጣኔ ኃብቷ የተመሰረተው። የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታም በማሽቆልቆሉ ነው ምጣኔ ኃብቷ የተጎዳው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












