የወቅቱ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ተግዳሮቶች

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) ባለፉት 10 ዓመታት በየዓመቱ በአማካኝ 9.4 በመቶ እያደገ መሆኑን ይናገራል።
ኢትዮጵያ ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ በትግራይ ክልል የቀሰቀሰው ጦርነት፣ በቅርቡ የተከሰተው ከፍተኛ ሆነ የምንዛሬ እጥረት እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት ኢኮኖሚውን እየተፈታተነው ይገኛል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያው ከ64 እስከ 68 ብር ድረስ በመመንዘር ላይ እንደሚገኝ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ይህ ዋጋ እስከ 72 ብር ድረስ ከፍ እንደሚል ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በመደበኛው የምንዛሬ ገበያ አንድ ዶላር በ45 ብር እየተመነዘረ ይገኛል።
የአገሪቱ የዋጋ ግሽበትም ቢሆን ከእለት ወደ እለት እየጨመረ እንደሚሄድ ያሳያል።
ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኮቪድ-19 ምክንያት ተጽዕኖ እንደደረሰበት እና 2 በመቶ ገደማ ዕድገት እንደሚያስመዘገብ ጠቅሰው ነበር።
ወርቅነሽ ሲማ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። ከምታገኘው ገቢ በላይ ወጪዋ ሰማይ መንካቱን በመግለጽ የኑሮ ውድነት እንዳማረራት ትናገራለች።
"የቤት ኪራይ፣ በርበሬ፣ ዘይት እና ጤፍ ዋጋቸው ሰማይ የነካ ነው" የምትለው ወርቅነሽ በአሁኑ ጊዜ ገቢያችን እና ወጪያችን የተመጣጠነ አይደለም ስትል ለቢቢሲ አስረድታለች።
ወርቅነሽ መንግሥት ለኑሮ ውድነቱ መፍትሄ ያበጅለታል ብላ ተስፋ ብትጥልም "ለእኛ ግን በጣም ፈታኝ ነው" ስትል ኑሮ እንደከበዳት ትገልጻለች።

በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ለማ አበበ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ስላለው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ሲናገር "እያደገ ነው" በማለት ነው።
አክሎም "የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነቱም በዚያው መጠን እያደገ ነው። ይህ ደግሞ ገበሬውን ሳይሆን ኑሮውን በየወሩ በሚያገኘው ደሞዝ ላይ ያደረገውን መካከለኛ ገቢ የሚያገኝ ነዋሪ እየጎዳው ነው። ገበሬው ግን ያመረተውን በገበያው ዋጋ ስለሚሸጥ አትራፊ ነው" ሲል ያስረዳል።
አቶ ለማ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር የአገር ውስጥ ምርትን መጠቀምን ማበረታታ እና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስ መፍትሄ ይሆናል ብሎ ያምናል።
የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች
ባለፉት አሥር ዓመታት መንግሥት በከፍተኛ መጠን ከተፈተነባቸው ችግሮች መካከል አንዱ የዋጋ ንረት ነው።
መንግሥት የዋጋ ንረትን መቆጣጠር አቅቶታል ብለው የሚተቹ ወገኖች በርካታ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥታቸው የዋጋ ንረት ለመከላከል እንደ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ያሉ ተቋማትን እያቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ኢኮኖሚውን ነፃ ለማድረግ በሚል በመንግሥት ይዞታ ስር የሆኑትን ቴሌኮምዩኒኬሽንን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊል ወደግል ለማዘዋወር ተወስኖ ነበር።
ከእነዚህ ድርጅቶች በተጨማሪም የኢንደስትሪ መንደሮችን፣ የስኳር ፋብሪካዎችን፣ ሆቴሎችን እና ሌሎች አምራች ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር ተወስኗል።
ይህ ውሳኔ የተወሰነው የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱንና የዋጋ ግሽበቱን ለመቋቋም፣ የገቢ ማመንጨት አቅምን ለማጠናከርና የወጪ ንግዱን ለማቀላጠፍ በሚል ነው።
ለዚህ ውሳኔ ሌላኛው ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ የብድር መጠን ከፍ ማለቱ እንደሆነም ይነገራል።
ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ተቋማት ክፍት እንደምታደርግ ያስታወቀችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ይፋ በተደረጉ የለውጥ እርምጃዎች ነው።
በቅርቡም ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፍ ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ ለተሰኘው ጥምረት ፍቃድ መስጠቷ ይታወሳል።
በዚህም የተነሳ ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ነዋይ ወደ አገሪቱ እንዲገባ እና በርካታ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ተነግሯል።
እንደ ማዕከላዊ ስታትስቲክ ባለስልጣን መረጃ ከሆነ በኢትዮጵያ ያለው የኑሮ ውድነት በሰኔ ወር ብቻ 24.5 በመቶ ደርሷል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ የውጭ አገራት የተበደረችው 42.8 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ይነገራል።
ኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብቷን ለማሳደግ ከወሰደቻቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ የተለያዩ ኢንደስትሪ ፓርኮችን ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱና እንዲልኩ ማበረታታት ነው።
ማርታ ገላነው በአገሪቱ ካሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል በአንዱ ተቀጥራ ትሰራለች።
የአውቶሜሽን ኢንጂነር ባለሙያ የሆነችው ማርታ በአገሪቱ እየተስፋፉ ያሉ የኢንደስትሪ መንደሮች የወደፊት ተስፋዋን ብሩህ ማድረጋቸውን ትናገራለች።
በአሁኑ ጊዜ ገና በመቋቋም ባለ ፋብሪካ ውስጥ እየሰራች ቢሆንም ለወደፊት ግን "እንደ አውቶሜሽን ኢንጂነርነቴ በየትኛውም ትልልቅ ፋብሪካዎች ውስጥ ያሉ ማሽኖችን ማንቀሳቀስ እችላለሁ" ስትል ታስረዳለች።
በደብረብርሃን የኢንደስትሪ ፓርክ የእንስሳት መኖ ለማምረት በማሰብ ግንባታ እያካሄዱ መሆኑን የሚናገሩት የባጃኢ ኢትዮ ኢንደስትሪያል ሶሉሽን ባለቤት ባጃኢ ናይከር ናቸው።
በደብረብርሃን ኢንደስትሪያል ፓርክ ውስጥ እያስገነቡት ባለው የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ድብልቅ የእንስሳት መኖ ለኢትዮጵያውያን እንስሳት አርቢዎች ለማምረት እየሰሩ ነው።
ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ከውጭ እየመጣ የነበረውን የእንስሳት ቫይታሚንና ሚነራሎችን ለማስቀረት የሚያስችል እቅድ አለው።
ፋብሪካው የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያም የማቅረብ ሃሳብ እንዳለው ባለቤቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እንደ ሚስተር ባጃኢ ከሆነ መንግሥት በዚህ የኢንደስትሪ መንደር ፋብሪካቸውን እንዲገነቡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን አድርጎላቸዋል።
በኢንደስትሪ ፓርክ ውስጥ ሲሰሩ ለተወሰነ ዓመታት ከታክስ ነጻ እንደሚሆኑ፣ ከውጭ የተወሰኑ እቃዎችን ከቀረጥ ነጻ የማስገባት እድል እንደተመቻቸላቸው፣ መሬት በርካሽ ማግኘታቸውን እንዲሁም በዚህ ኢንደስትሪ መንደር ለእንስሳት አምራቾች የተለየ ትኩረት መሰጠቱ እርሳቸውን ከሳቧቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በመላ አገሪቱ 15 የኢንደስትሪ ፓርኮች እንዳሉና ተጨማሪ 20 ደግሞ የመገንባት እቅድ እንዳለው ያስረዳል።

የትግራይ ጦርነት እና የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት እያሳየ ቢሆንም በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ጦርነት ግን የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ፈተና ላይ ጥሎታል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት እና የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ የበላይ ኃላፊ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ባለሀብቶች የረዥም ዓመት እቅድ ይዘው መሆኑን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ያለው ግጭት የአጭር ጊዜ መሆኑን እና አገሪቱም እንደምትወጣው ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
ለኢትዮጵያውን ዋነኛ የምጣኔ ሀብት ስጋት የዋጋ ግሽበት መሆኑን የሚያብራሩት አቶ ዘመዴነህ፣ ባለፉት 10 ዓመታት የግሽበት መጠኑ በእጥፍ መጨመሩን በመግለጽ ይህም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ተግዳሮት ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ለዋጋ ግሽበቱ መናር ምክንያት ነው ብለው ከጠቀሷቸው መካከል ከፍተኛ የሆነ የፍላጎት መጨመር ሲኖር የአቅርቦት መጠን በዚያው ልክ ማደግ አለመቻሉን ነው።
በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለ ከፍተኛ አለመመጣጠን በተለይ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርቶች ከፍላጎት ጋር በተመጣጠነ መልኩ አለማደጋቸውን ያነሳሉ።
ሌላው የጅምላ፣ የችርቻሮ እና የማከፋፈል ስርዓት በአገሪቱ ውስጥ አሁንም ኋላ ቀርነት እንዳለው አንስተዋል። ለዚህም መዋቅራዊ ለውጥ መካሄድ አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።
ኢትዮጵያ ከ126 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌኮምዩኒኬሽኑን ዘርፍ ለግል ባለሀብቶች መስጠቷን የሳፋሪኮም ስምምነትን በመጥቀስ የገለፁት አቶ ዘመዴነህ፤ "ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ለተለያዩ ቢዝነሶች በሯን መክፈቷን ያሳያል" ሲሉ ተናግረዋል።
በቴሌኮም ዘርፉ የውጭ ባለሀብቶች መምጣታቸው የአገልግሎት ጥራት፣ የዋጋ ውድድር በመፍጠር ለቴሌኮሙም ሆነ ለፋይናንስ ዘርፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያብራራሉ።
አቶ ዘመዴነህ ኢትዮጵያ በግብርና፣ በአምራች እንዲሁም በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች በቀጣዩቹ ሦስትና አምስት ዓመታት እድገት እንደምታሳይ ያላቸውን ተስፋም ገልፀዋል።














