ተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ መኖር ይዞት የሚመጣው ተስፋና ስጋት

የሞባይል ስልክ ማማ

የጅማ ከተማ ነዋሪና የባንክ ሠራተኛ የሆነው ሞሐመድ አባገሮ የሞባይል ስልኩ ለእሱ ሁሉ ነገሩ እንደሆነ ይናገራል። ሞባይል ለግንኙነት ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ለተለያዩ ግብይቶችና ገንዘብ ለማንቀሳቀስ ያለው ጠቀሜታ ከፍያለ መሆኑንም ይገልጸል።

ለዚህ ደግሞ በዋናነት አስተማማኝ የኢንትርኔት አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ አዲስ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ተቋም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ጥሩ ነገር እንደሆነ ሞሐመድ ያምናል።

"ውድድር ሲኖር ጥራት ይጨምራል ዋጋ ይቀንሳል። እኔም በጥራት ላይ ያተኩራሉ ብዬ አስባለሁ። ጥሩ ቴክኖሎጂ ይመጣል ይህም አገሪቱንና ሕዝቧን የዲጂታል ዘመን ተጠቃሚ ያደርጋሉ። ለምሰራበት የባንኩ ዘርፍም ብዙ ጥሩ ነገሮችን ይዞ ይመጣል።" ይላል።

የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ አገር ተቋማት በሯን ክፍት ያደረገችው ኢትዮጵያ የበርካታ ተቋማት ስብስብ ለሆነው ኩባንያ የመጀመሪያው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነት ፈቃድ በቅርቡ ሰጥታለች።

በዚህም መሠረት 'ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ' የተባለውና የስድስት ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ተቋም አገሪቱ ለጨረታ አቅርባቸው ከነበሩት ሁለት የቴሌኮም ፈቃዶች ውስጥ አንዱን በማሸነፍ በዘርፉ እንዲሰማራ ተመርጧል።

የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የዩናይትድ ኪንግደም ቮዳፎን እና ሲዲሲ ግሩፕ፣ የደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም፣ የጃፓኑ ሱሚቶሞ እንዲሁም ዲኤፍሲ ናቸው፤ በአገሪቱ በኢትዮ ቴሌኮም ከ120 ዓመታት በላይ በብቸኝነት ተይዞ ወደነበረው ዘርፍ ለመግባት ፈቃድ ያገኙት።

ውድድር፡ ቴክኖሎጂ፣ ጥራት፣ ዋጋ

ተቀማጭነቷ ኬንያ መዲና ናይሮቢ የሆነው 'የግሎባል ኢንተርኔት ሸትዳውንስ' የአፍሪካ ፖሊሲ ማኔጀር ብርሃን ታዬ፤ አዳዲሶቹ የኔትዎርክ አቅራቢዎች ሰዎችን ከማገናኘት ባለፈ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያንቀሳቅሳሉ ትላለች።

"ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ራይድና ፈረስ ያሉ የታክሲ አግልግሎት ሰጪዎች ደንበኞቻቸውን የሚያገኙት በስልክና በኢንተርኔት ተጠቅመው ነው። ከዚያ ባለፈ አሁን በኮቪድ-19 ምክንያት ብዙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በበይነ መረብ ታግዘው ነው። እሱም ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻችን ሕይወት በይነ መረብ ላይ ጥገኛ ነው" ትላለች።

ከዚህ በተጨማሪ ብርሃን፤ የአገልግሎት ሰጪ ምርጫና ፉክክር ያለበት ገበያ ለተጠቃሚው መልካም ነው ከሚለውና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ከተሰማራው ከአዲስ አለማየሁ ሐሳብ ጋር ትስማማለች።

"በተለይ ሕግና ፖሊሲው የተስተካከለ ከሆነ ኩባንያዎቹ ተወዳድረው ለተጠቃሚው ጥሩ የሆነ አግልግሎት በጥሩ ዋጋ ያቀርባሉ። ይህ አንደኛው ጥቅም ነው።"

ከመቶ ዓመታት በላይ ዘርፉን በብቸኝነት ተቆጣትሮ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም የሚሰጠውን አገልግሎት ፉክክር ካለባቸው የአፍሪካ አገራት በእጅጉ ዝቅ ያለ መሆኑን የምትጠቅሰው ብርሃን "በአጠቃላይ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ለ100 ሚሊዮን ሰው የሚገባ አይደለም ትላለች። ስለዚህ የአዳዲሶቹ ቴሌኮም ኩባንያዎች መምጣት ብዙ ነገር እንዲቀየር ያስችላል" ስትል ታክላለች።

"በተጨማሪ እኔ ደግሞ ከሰብዓዊ መብት አንፃር ሳየው የተሻለ ኢንተርኔት መኖሩ እንደ የመናገር ነፃነትና መረጃ የማግኘት መብት ያሉ ሰብዓዊ መብቶችን ያስፋፋል።"

ናይሮቢ በሚገኘው የስትራትሞር ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ አጥኚ የሆነችው ብርሃን የአዲሱ የቴሌኮም ኩባንያዎች ጥምረት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሥራ ፈጠራን እንደሚያበረታታ ታምናለች።

"መንግሥት ለሁሉም ዜጋ ሥራ መፍጠር አይችልም። ኢንተርኔትና ስልክ ግን ሥራ ፈጠራን የማበረታት አቅም አላቸው። ለምሳሌ እዚህ ያለንበት ኬንያ ውስጥ ሳፋሪኮም የሚሰጠው አግልግሎት ብዙዎች በሥራ ፈጠራ እንዲሰማሩ የሚያደርግ ነው።"

ነገር ግን ብርሃን፤ አዲሶቹ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያፈሱት ኩባንያዎች ሲመጡ መመሪያ፣ ሕግና ፖሊሲ በአግባቡ ሊተገበር ይገባል የሚለው እንዲሰመርበት ትሻለች።

አዳዲስ'ቢዝነሶች'

አዳዲስ የቢዝነስ ጅማሮዎችን [ስታርትአፕ] በሐሳብ፣ በገንዘብና በተለያዩ ድጋፎች በማበልፀግ ሥራ ላይ የተሠማራው አዲስ አለማየሁ የአዳዲሶቹ ቴሌኮም ኩባንያዎች ወደ አገር ቤት መምጣት ኢትዮጵያን ይቀይራታል ይላል።

"እኔ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገር ኬንያ ጋር እንጂ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ጋር አይደለም የማነጻጽረው። ያለን ክፍተት በጣም ሰፊ ነው።"

አዲስ የቃና ቴሌቪዥን መሥራችና ባለቤት ነው። አዳዲስ የቢዝነስ ሥራዎችን ወደ ማበልፀግ የገባው ከሁለት ዓመት በፊት እንደሆነ ይናገራል። ነገር ግን የቴሌኮም ነገር ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ አይክድም።

ለምሳሌ ይላል አዲስ፤ "ለምሳሌ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው አንድ ሐሳብ በአንድ ወጣትና ጓደኞቹ የበለፀገ ነው። ይህ ቢዝነስ በቴሌኮም አቅርቦት ላይ ጥገኛ ነው። አዲሱ ቢዝነስ ዕቃዎችን ከቦታ ቦታ ያዘዋውራል። ነገር ግን በተለምዶ እንደሚደረገው በደላላ ሳይሆን በአፕሊኬሽን [በስልክ መተግበሪያ] አማካይነት ነው። ይህ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች የሚከፍሉትን ተጨማሪ ገንዘብ ያስቀራል" ይላል።

"በቂ የቴሌኮም አገልግሎት ከሌለ፣ ፈጣን ኢንተርኔት ከሌለ፣ ዋጋው ካልቀነሰ፣ ምንም ሐሳብ ቢኖርህ ወደ ገበያ ለመግባት በጣም አስቸጋሪ ነው።"

ሞባይል

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

አዲስ "እርግጥ ነው ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቸኛው የቴሌኮም አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም ተሻሽሏል" ይላል። "ነገር ግን ፉክክር መኖሩ የበለጠ እንዲሻሻል ያደርገዋል" ብሎ ያምናል።

"አገልግሎት አቅራቢ ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ምርጫ ሲኖር ዋጋው ይወርዳል፤ አግልግሎትም ይሻሻላል ብለን እናስባለን። በዚህ ሂደት ዋናው አሸናፊ የሚሆነው ተጠቃሚው ነው።"

ብርሃን በበኩሏ እነ ኬንያ፣ ኮትዲቯር፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋልና ናይጄሪያን ስታይ የአዳዲሶቹ ኩባንያዎች መምጣት ለጀማሪ ቢዝነሶች በጣም ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው ትላለች።

"ለምሳሌ ኮምፒውተር ሳይንስ ላይ የሚሠሩ 'ፕሮግራመሮችና ኮደሮች' ቁጭ ብለው ኢንተርኔት ላይ ነው ይህን ማድረግ የተማሩት። ሰዎችን አቅም ከመስጠት አልፎ ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ ቢዝነሶች እንዲስፋፉ ያደርጋል ማለት ነው።

"ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች ስለገቡ ብቻ ሕዝቡ ይጠቀማል ማለት አይደለም። የተለያዩ ፖሊሲዎች መስተካከል አለባቸው። ምክንያቱም ሌሎች አገራት ኢንተርኔት ከማስገባት አልፈው ፖሊሲዎችን አስተካክለዋል።"

ባለሙያዋ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ‘ኢንኪዩቤተሮች’ ወይም ጀማሪ ቢዝነስ አብለጻጊዎች በቂ ናቸው ብላ አታምንም። ነገር ግን የቴሌኮም አቅራቢዎቹ አገር ቤት መግባት ሊያነቃቃው ይችላል ትላለች።

የኢንተርኔመቋረጥ

አዲስ፤ ከቡና እና ከወርቅ በላይ ወደፊት የምንሸጠው 'ጭንቅላት ' ነው ይላል።

ይሄን ሲያብራራ "አሁን ባለው ኔትወርክ እንኳ 'ሶፍትዌር ዲቬሎፕ' የሚያደርጉ፣ ዌብሳይት የሚሠሩ፣ የስልክ መተግበሪያዎች የሚፈጥሩ፤ ይሄን ሠርተው ለውጭ ድርጅቶች የሚሸጡ በጣም ብዙ ወጣቶች አሉ።

የኢንተርኔት ጥራት ሲጨምርና ዋጋው ሲቀንስ እንዲሁም መንግሥት እነዚህን ወጣቶች ሲደግፍ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት።"

ውጭ ያሉ ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ የማይልኩበት አንደኛው ምክንያት ያለው ኢንተርኔት አስተማማኝ አለመሆን ነው ይላል አዲስ።

"ለምሳሌ አሁን ያለሁት አሜሪካ ነው። ብዙ ድርጅቶች እያናገርኩ ነውና 'ሞክረነዋል፣ አይተነዋል። ብዙ ብቃት ያላቸው ልጆች እንዳሉ እናውቃለን ግን ኢንተርኔቱ ያስፈራናል' ይላሉ።

"የኢንተርኔቱ መቆራረጥና የፍጥነቱ ዝቅተኛ መሆን ነው አንደኛው ችግር። ሁለተኛው፤ ችግር በተፈጠረ ቁጥር አገልግሎቱእንዲቋረጥ መደረጉ" እንደተግዳሮት ይጠቅሳል።

በእርግጥም በተለያዩ ጊዜያት አለመረጋጋት ሲፈጠር ወይም በሌላ ምክንያት በተደጋጋሚ የኢንተርኔት አገልግሎት ይቋረጣል። በዚህም ኢትዮጵያ ሆን ብለው ኢንተርኔትን ከሚያቋርጡ አፍሪካ አገራት መካከል ትጠቀሳለች። ታድያ ይህ አዲስ ለሚገቡት ኩባንያዎች ስጋት አይሆንም?

"እስካሁን ካለው ልምድ አንፃር የኢንተርኔት መቋረጥ ወደፊትም ይኖራል ብለን ነው የምንገምተው። ይህ የኩባንያዎች ጥምረት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በዚህ ሊጎዳ ይችላል። ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም። ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች ፖሊሲ አላቸው። ለምሳሌ ኢንተርኔት ሲዘጋ ለምንድነው የተዘጋው የሚል መረጃ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው። ቢያንስ ይህንን ግልጽነት ይዘውት ይመጣሉ ብለን ነው የምንገምተው" ትላለች ብርሃን።

የ5ጂ ኢንተርኔት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሉታዊፅዕኖ ይኖር ይሆን?

እነዚህ አዳዲሶቹ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ጥቅማቸውን ፈልገው እንደሚመጡ ብርሃንና አዲስ ይስማማሉ። ኩባንያዎቹ ገበያው ሰፊና ጭንቅላት ያላቸው ወጣቶች የሞሉት ስለሆነ ነው የሚመጡት ይላል።

ብርሃን እንደ ሰብዓዊ መብት ባለሙያ "አደጋ ነው ብዬ የማስበው የግላዊ መረጃ ጥበቃ ጉዳይ ነው" ትላለች።

"ለምሳሌ ኢትዮጵያ 'ፐርሰናል ዳታ ፕሮቴክሽን ሕግ' የላትም። የ100 ሚሊዮን ሕዝብን ኢንፎርሜሽንና ዳታ አሳልፈህ ስትሰጥ በምን ዓይነት መንገድ ነው? በምን ዓይነት ሕግ ነው የሚመራው? የሚለው በጣም ወሳኝ ነው። ለግልና ለውጭ ድርጅት የሰዎችን መረጃ መስጠት በጣም አዳጋች ስለሆነ እሱ እንዴት ነው የሚሆነው የሚለው አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

"ሌላኛው ደግሞ እነዚህ ኩባንያዎች ሲመጡ በጣም ውስብስብ ቴክኖሎጂዎች ነው ይዘው የሚመጡት። ስለዚህ ሕዝቡን አላግባብ ሊጠቀሙበት [አቢዩዝ] ሊያደርጉት ይችላሉ ወይ? የሸማቾች መብት እንዴት ነው ሊጠበቅ የሚችለው መታወቅ አለበት" ትላለች።

ብርሃን ሌላኛው አሳሳቢ ነገር ስለላ [ሰርቬላንስ] ነው ትላለች።

"ሁላችንም ወደድንም ጠላንም ሕይወታችን ኢንተርኔት ላይ ነው። ታክሲ ስንጠራ፣ በስልክ ስንነጋገር፣ መልዕክት ስንላላክ. . . እኔ የአንድን ሰው መረጃ ከፈለግኩ ሳፋሪኮም ከሆነ ኔትዎርክ አቅራቢው እዚያ ሄጄ መረጃ ማግኘት የምችል ከሆነ በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ ይህ እንዴት ነው ቁጥጥር የሚደረግበት? የታክስ ጉዳይ እንዴት ነው የሚሆነው?" የሚሉ ጉዳዮች ሊታሰብበት እንደሚገባ ታሳስባለች።

ብርሃን እነዚህ ጉዳዮች ኩባንያዎቹ ከመግባታቸው በፊት ሊጠኑ እንዲሁም ሕግ ሊወጣላቸው ይገባል ባይ ናት። ይህ ሥራ ደግሞ የተቆጣጣሪው ድርጅትና የመንግሥት ነው መሆን ያለበት ትላለች።

"የትኛውም ኩባንያ ሲመጣ ትርፉን አስቦ እንጂ ሕዝቡን እጠቅማለሁ ብሎ አይደለም። በተለይ መንግሥት ሕጉና ፖሊሲው የሕዝቡን ጥቅም የሚያስጠብቅ ማድረግ ይኖርበታል።"

የኢንተርኔትና የሞባይል አገልግሎት አማራጭ መኖሩ በተለያየ መስክ በርካታ አውንታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ የሕግና የፖሊሲ ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ጥራት ያለው፣ ርካሽና አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ የሥራ መስኮች እንዲጎለብቱና ትርፋማ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ከጥቂት ወራት በፊት የታክሲ ሥራ የጀመረችው ልዩወርቅ ደሳለኝም ይህንን ተስፋ ታደርጋለች።

ከተገልጋዮች ጋር በጥሪ ማዕከል በኩል ነው እና በሞባይል ስልክ ላይ ባለ መተግበሪያ አማካይነት የምትገኛኘው ሲሆን የኢንትርኔት አገልግሎት በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ሰዎች ታክሲ ለማግኘት እየጠሩ መሃል ላይ ይቋረጥባቸዋል።

በተጨማሪም ኢንተርኔት ሲቋረጥ የተጓዙበት የኪሎ ሜትር ርቀትን እንዲሁም የሚጠይቁትን የአገልግሎት ክፍያ ለማወቅ እንደሚቸገሩ ትናገራለች።

"በዋናነት ግን ሥራችን ከሞባይል ኢንተርኔት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ኢንተርኔት ሲቋረጥ ተጠቃሚ ለማግኘት አንችልም።"

አሁን ተጨማሪ አዲስ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ሥራ ይጀምራል መባሉ ለሥራዋ አማራጭና ጥሩ ነገር ይዞ ይጣል ብላ ታስባለች።

"ውድድር ስለሚኖር የተሻለ አማራጭና ጥሩ አገልግሎት እናገኛለን።" ብላ ታምናለች።