የቴሌኮምን ጨረታ ያሸነፈው ጥምረትና የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈራረሙ

ፕሬዝደንት ኡሁሩ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ

በኢትዮጵያ መንግሥት እና የቴሌኮም አገልግሎት ለማቅረብ ፍቃድ ባገኘው ጥምረት መካከል የፍቃድ ስምምነት ፊርማ ተካሄደ።

ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፍ ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ ለተሰኘ ጥምረት ፍቃድ መስጠቷ ይታወሳል።

ይህን ጥምረት የኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ሲሆን፤ የዩናይትድ ኪንግደም ቮዳፎን እና ሲዲሲ ግሩፕ፣ የደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም፣ የጃፓኑ ሱሚቶሞ እንዲሁም ዲኤፍሲ በጥምረቱ ተካተዋል።

የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተከናወነው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ እና የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በተገኙበት መድረክ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጀነራል ኢንጂነር ባልቻ ሬባ፤ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጥምረቱ የአሥርት ዓመታት አገልግሎት እና ልምድን ወደ ኢትዮጵያ ያመጣል ብለዋል።

የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ ፒተር እንዴንግዋ በበኩላቸው ጥምረቱ መሠረታዊ የተግባር ሥራዎችን በቀጣይ ወራት ይጀምራል ብለዋል።

የጥምረቱ አካል የሆነው የቮዳኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻሜል ጆሱባ፤ ጥምረቱ ለኢትዮጵያ አዎንታዊ ለውጦችን ይዞ ይመጣል ሲሉ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ የሥራ እድል መፍጠር፣ የጤና እና የግብርና ዘረፎችን ማሻሻል ፍላጎታቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለጥምረቱ ፍቃድ መስጠቷ ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ነዋይ ወደ አገሪቱ እንዲገባ እና በርካታ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ሲነገር ቆይቷል።

ጥምረቱም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት ጨረታ ያሸነፈበትን 850 ሚሊዮን ዶላር ለመንግሥት ገቢ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ይፋ አድርጓል።

ጥምረቱ እአአ በ2022 አጋማሽ የቴሌኮም አገልግሎቶችን መስጠት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በቀጣይ 10 ዓመታት 8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደርጋል ተብሏል።

በተመሳሳይ ዓመት 1.5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል የተባለለት ጥምረቱ፤ የአገሪቱን የቴሌኮም ዘርፍ ያዘምናል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስተዳደር የቴሌኮም ዘርፉን ለውጪ ተቋማት ለመጀመሪያ ጊዜ ክፍት ያደረገ ሲሆን፤ መንግሥት የኢትዮቴሌኮምን ድርሻ የመሸጥ ሐሳብ አለው።