ከእንጦጦ ፓርክ እስከ ጂቡቲ መንገድ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየከወነ ያለው ተቋም
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተገኙበት ወቅት በኢትዮጵያ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ድክመት የአገር ንብረትን እያባከነ እንደሆነና የአገር ምጣኔ ሀብት እድገት ሲፈተን ከቆየባቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረው ነበር።
የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ድክመት በብዙ ዘርፎች ቢታይም የተሻሉ የሚባሉም አሉ። በጠንካራ የፕሮጀክቶች ክትትል እና አፈጻጸም ለውጥ እያመጣ ነው የተባለው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋነኛ ተጠቃሽ ነው።
ኮርፖሬሽኑ ሀብት እና ቴክኖሎጂን በማጣመር ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገር እድገት የበኩላችንን እየተወጣን ነው ይላል።
"እኛ ጋር 24 ሰዓት 1 ሰዓት ነው" የሚሉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው፤ ኮርፖሬሽኑ በኮንስትራክሽን እና ማኑፋክቸሪንግ ሥራዎች (በግንባታና ምርት ዘርፍ) ግንባር ቀደም ኩባንያ የመሆን ራዕይ መሰነቁን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ማን ነው?
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮሥኮ) በመንገድ፣ በሕንጻ እና በውሃ ሥራዎች ተሰማርተው የነበሩ የሦስት ድርጅቶች ጥምረት ነው።
በፕሮጀክቶች አፈጻጸሙ መልካም ስምን መገንባት የቻለው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፤ 2008 ዓ.ም. ላይ የኢትዮጵያ መንገድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የውሃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና ሕንጻ ቴክኖሎጂን በማጣመር ተመስርቷል።
ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በመንገድ፣ በመስኖ እና የውሃ መስመር ዝርጋታ እና በሕንጻ ግንባታ ዘርፎች ተሰማርቶ ይገኛል።
በቅርቡ ከውሃ ኃይል የሚያመነጩ (ኃይድሮ ፓዎር) ግድቦች እና የባቡር መስመር ግንባታ ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢ/ር ዮናስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከውሃ ኃይል የሚያመነጩ ግድቦች ግንባታቸው የሚከናወነው በውጪ ተቋራጮች መሆኑን ጠቅሰው፤ ኮርፖሬሽኑ ወደዚህ ዘርፍ መግባቱ የውጪ ምንዛሬ ወጪን እንደሚቀንስ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, ECWC
ኮርፖሬሽኑ በመንገድ ግንባታ ብዙ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች እንዳሉት የሚናገሩት ኢ/ር ዮናስ፤ የጂቡቲን ወደብ ከኢትዮጵያ የሚያገናኘውን መንገድ ለመገንባት ኮርፖሬሽኑ ሥራ መጀመሩን ይናገራሉ።
"ከተማን ከከተማ፣ ክልልን ከክልል የሚያገናኙ የመንገድ ግንባታዎችን ከመገንባት አልፈን አገርን ከአገር የሚያገናኝ የመንገድ ግንባታ ማከናወን ጀምረናል" ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ የአየር ማረፊያ ግንባታዎችን እንደሚያከናውን ጠቁመው በቅርቡም ሦስት አየር ማረፊያዎችን ለመገንባት ውል መግባታቸውን ያስረዳሉ።
ኢ/ር ዮናስ የሚመሩት ኮርፖሬሽን በቅርቡ የባቡር መስመር ግንባታ ማከናወን እንደሚጀምር ይናገራሉ። "ልክ እንደ ኃይድሮ ፓዎር ግንባታው የባቡር ዲፓርትመንት ከፍተን ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት አጠናቀናል" ብለዋል።
የሕንጻ ግንባታን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ እስከ 21 ፎቅ ርዝመት ያላቸውን ሕንጻዎች እንደሚገነባ በመግለጽ፤ የመኖሪያ ቤቶች ዋጋን ለማረጋጋት ኮርፖሬሽኑ ወደ ሪል ስቴት ልማት እንደሚሸጋገርም አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, ECWC
የኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶች
የእንጦጦ ፓርክ እና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው የአዲስ አበባ ከተማ አትክልት ገበያ በቅርቡ ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ያከናወናቸው ፕሮጀክቶች ናቸው። የአንድነት ፓርክ ዋሻ ግንባታም በፕሮጀክት አስተዳደር ተሳታፊ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይናገራሉ።
በቅርቡ በአዲስ አበባ የእናቶች እና ሕጻናት ሆስፒታል ገንብቶ ያስመረቀው ኮርፖሬሽኑ፤ ግንባታቸው በአንድ ዓመት ተኩል ሁስጥ የሚጠናቀቁ ሁለት አጠቃላይ ሆስፒታሎችን ለመማከናወን ከከተማ መስተዳደሩ ጋር ውል ገብቷል።
ኮርፖሬሽኑ ከጎንደር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ መገጭ የተሰኘ የግድብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በዚህ ዓመት ላይ ውሃ መያዝ እንደሚችል የተነገረለት ግድብ ግንባታው ሲጠናቀቅ 77 ሜትር ቁመት እና ከ800 ሜትር በላይ ርዝመት ይኖረዋል። ግድቡ ከ45 ሺህ በላይ ቤተሰቦች በዓመት ሦስት ጊዜ እንዲያመርቱ ከማስቻሉም በላይ ለጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ግብዓት ይሆናል።
በኦሮሚያ ክልል የጉደር-ሸነን-ሰዮ 91.8 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዲሁም በደቡብ ክልል የዱራሜ-ዳንቦያ፣ አንጋጫ-ሀላባ 64 ኪ.ሜ አስፋልት መንገድ ግንባታ አስጀምሯል።
ከአገር ውጪም በጂቡቲ 80 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን መንገድ ለመሥራት ውል ፈርሞ የመንገድ ግንባታ ሥራ ጀምሯል።
የለውጥ ሥራዎች
ይህ ኮርፖሬሽን ወደ ስኬት ከመምጣቱ በፊት ብዙ ፈተናዎችን አልፏል ይላሉ ኢ/ር ዮናስ።
ኢኮሥኮ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካም የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች መሠራታቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ።
ኮርፖሬሽኑ 2008 ዓ. ም. ላይ ሲቋቋም 3 የተለያየ የሥራ ባህል ያላቸው ተቋማት ተቀላቅለው የተቋቋመ ስለሆነ ኮርፖሬሽኑ በተመሠረተ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም ነበር ይላሉ ኢ/ር ዮናስ።
ሰኔ ወር 2011 ዓ. ም. ላይ ወደ ተቋሙ ሲመጡ ይህ 12 ሺህ ሠራተኞችን የያዘው ተቋም ሊፈርስ ተቃርቦ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
ኢ/ር ዮናስ ኮርፖሬሽኑን ለመታደግ በሦስት ምዕራፎች የተከፋፈለ የለውጥ ሥራ መከናወኑን እንዲህ ያስረዳሉ።
"የመጀመሪው ምዕራፍ ተቋሙን ከችግር እንዴት እናውጣው ብለን ሮድ ማፕ [ፍኖተ ካርታ] ቀረጽን። በዚህ ፍኖተ ካርታ ተቋሙ በወቅቱ ከነበሩበት መሠረታዊ ችግሮች የሚያላቅቀው ሥራ ነው ያከናወነው። የተለያየ የነበረውን የሥራ ባህል አንድ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል።"

በአንድ ዓመት ውስጥ አሠራሩን ወጥ ማድረግ እና ሠራተኛው ጋር የነበረውን ቅሬታ ለመቅረፍ መሞከሩን ይናገራሉ።
በኮርፖሬሽኑ ውስጥ የመንገድ ሥራዎች፣ ማሽኖች ባለ ቢጫ ቀለም እንዲሁም በውሃ ሥራዎች የተሰማሩ ማሺነሪዎች ቀለም ደግሞ ሰማያዊ እንደነበሩ በማስታወስ፤ "የአንድ ኮርፖሬሽን አካል ሆነው የውሃ ሥራዎች ማሽነሪዎች የመንገድ ሥራ ውስጥ ገብተው አይሠሩም፤ የመንገድ ማሽነሪዎችም እንዲሁ የውሃ ሥራ አይሠሩም በሚል 'የውሃ ዘረፍ፣ የመንገድ ዘረፍ' ተብለው ተከፋፍለው ተቋሙ ውጤታማ እንዳይሆን ተደርጎ ነበር" በማለት ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል የሠራተኞች ደሞዝ እና ደረጃ የተለያየ መሆኑ ከሠራተኛው ዘንድ የተለያዩ ቅሬታዎች ሲያስነሳ መቆየቱን ይገልጻሉ።
2012 ዓ.ም. ላይ ግን የተቋሙን አደረጃጀት እና የአሠራር ሥርዓት ወጥ በማድረግ አዲስ ሥርዓት መዘርጋታቸውን ገልጸዋል።
በውሃ ወይም በመንገድ ሥራ ላይ ብቻ ተሰማርተው የነበሩ ሠራተኞች የውሃ እና የመንገድ ሥራ ጥምር ክህሎት እንዲኖራቸው መደረጉን እንዲሁም የቀለም ጉዳይ ወሳኝ ስለነበረ ሰሚያዊ እና ቢጫ ቀለሞችን በመቀላቀል የኮርፖሬሽኑን ማሽነሪዎች ቀለም ወደ አረንጓዴ እንዲቀየር መደረጉን ያስረዳሉ።
"ይህ ሲሆን [የለውጥ ሥራ ሲከናወን] 90 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች እንዲቀየሩ ተደርጓል። ሰዉ ደስተኛ ነበር። በሚመጥናቸው ቦታ የተመደቡም አሉ። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ። ተልዕኮ ሰጥተን እየፈተንን ምደባ ሰጥተናል። ይህን ስናደርግ አንድም ቅሬታ አልቀረበብንም" በማለት ኢ/ር ዮናስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶችን ሲቀበል ትርፋማ እንደማያደርጉ እየታወቀ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ውል ይገባ ነበር ይላሉ።
ኮርፖሬሽኑ ለማከናወን የሚቀበላቸውንም ሆነ የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በዝርዝር እንደሚገመግም የሚናገሩት ኢ/ር ዮናስ "በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ መዘግየት ካጋጠመ ምክንያቱ ተለይቶ አፈጻጸሙ ላይ ማስተካከያ እየተደረገ ከ2012 ዓ. ም. ጀምሮ ትርፋማ ወደ መሆን ተሸጋግረናል" ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተሰማራባቸው ዘርፎች በአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር፣ በጥራት ጥበቃ ሥርዓት እና በሥራ ቦታ ጤና እና ደኅንነት አስተዳደር ሥርዓት የኢኤስ አይሶ ሰርተፊኬቶችን ማግኘት ችሏል።

የኮርፖሬሽኑ ሁለተኛው የለውጥ ምዕራፍ የፕሮጀክት አስተዳደር ሪፎርም መሆኑን ይናገራሉ። የዚህ ሪፎርም ዓላማዎች መካከል ኮርፖሬሽኑ በተሰማራባቸው ዘርፎች ወጥ የሆነ የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እና የተቋሙን አትራፊነት ማረጋገጥ ተጠቃሽ ናቸው።
ይህ ሪፎርም የሰው ሃብት፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የመሳሪያዎችና ማሽነሪዎች ሥራ አመራር ማሻሻያዎችን ያካትታል።
ኮርፖሬሽኑ ይህ ሪፎርም የሚቀበላቸው ፕሮጀክቶች በተገባላቸው የውለታ ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቁ ያረጋግጣል፤ እንዲሁም ውጤታማ የአሰራር ስርዓት በማስፈን የትርፍ መጠንን ከፍ ማድረግ ይቻላል ይላል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢ/ር ዮናስ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ የዲጂታይዝድ ኤንድ ኢንደስትራላይዝድ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ለውጦችን እንደሚያካሂድ ያስረዳሉ።
ይህ የለውጥ ሥራ ከሚፈጥራቸው እድሎች መካከል በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በዋና መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በሚተከሉ የቴሌቪዥን መስኮቶች በቀጥታ ያሉበትን ሁኔታ መከታተል ማስቻል አንዱ ነው።
አሁን በሙከራ ላይ በሚገኘው የዚህ የለውጥ ሥራ፤ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከቢሯቸው ሆነው፤ ገልባጭ ተሽከርካሪዎች አሸዋ ሲገለብጡ እና ኮንክሪት ሲሞላ በቀጥታ ላፕቶፕ ኮምፒውተራቸው ላይ ይከታተላሉ።
ይህ አሠራር ሠራተኛው ወደ ፕሮጀክት ሳይቶች ሳይጓዝ በአነስተኛ ወጪ ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ እና አስፈላጊውን ፈጣን ማስተካከያ ለማድረግ እንደሚያስችል ኢ/ር ዮናስ ይናገራሉ።













