የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ለምን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ አያገኝም?

ዶላር እና ብር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለመሆኑ ከኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ጀርባ ያለው ምንድን ነው?

ኢትዮጵያውያንን እየፈተነ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደማያገኝ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በመጋቢት ወር የኑሮ ውድነትን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በ34.7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጾ ነበር።

የዋጋ ንረቱ ለምግብነት በሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ እና እህሎች፣ ቅመማ ቅመም እና ዘይት፣ ቅቤ እና ቡና እንደሚጨምር ገልጾ ነበር።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ከኑሮ ውድነቱ የተነሳ በሚያገኙት ደመወዝ ኑሮን መምራት አዳጋች እንዳደረባቸው ይናገራሉ።

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአገሪቱ ውስጥ ለሚታየው የኑሮ ውድነት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቁልፍ መፍትሔ ነው ቢሉም፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ግን ከፍተኛ አምራች በሆኑ አካባቢዎች በሰላም እጦት መታመሳቸው አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ይላሉ።

አሁን ያጋጠመው የዋጋ ንረት በቅርብ ጊዜ በተፈጠሩ ምክንያቶች የተከሰተ እንዳልሆነ የሚታመን ሲሆን ለዚህም ለሁለት ዓመታት ያህል የመላውን ዓለም ምጣኔ ሀብት ያቀዛቀዘውን የኮሮናቫይረስወረርሽኝን ተከትሎ መሆኑን ጫናውን አጉልቶታል።

ከዚህ ባሻገር ግን በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት፣ በተለያዩ ስፍራዎች ያጋጠሙ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እንዲሁም የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በነዳጅ፣ በስንዴ እና በምግብ ዘይት ላይ ያስከተኩት ከፍተኛ ጭማሪ ችግሩን አባብሰውታል።

ይህ በተደራራቢ ምክንያቶች እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለው የዋጋ ንረት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚስተካከል እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳም እንዲሁ በአንድ ውይይት ላይ የዋጋ ንረቱ እንዲሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ የሚያገኝ ችግር እንዳልሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ልክ እንደ አቶ ሽመልስ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ያገኛል ማለት “ማታለል ይሆናል” ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ መንግሥት ወሳኝ የሆኑ አፋጣኝ እርምጃዎችን ከወሰደ በፍጥነት መፍትሔ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው።

ይህ የሃሳብ ልዩነት የሚመነጨው የዋጋ ንረቱ ዋነኛ ምክንያቶች ምንድን ናቸው ከሚለው ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) የግብርና ምርት የሆኑት ፍራፍሬ እና ጥራጥሬ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ አንዳንዶቹ እስከ 100 ፐርሰንት ጭማሪ አሳይተዋል ይላሉ።

እናም “በዚህ አገር ውስጥ ኑሮ ያልከበደው ከ5 በመቶ አይበልጥም” በማለት ተናግረዋል።

እነርሱም ይላሉ ምሁሩ “በሙስና የከበሩ እና በንግድ ውስጥ በአቋራጭ የበለፀጉ ናቸው” በማለት የችግሩን አስከፊነት ያብራራሉ።

ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጀምሮ በኑሮ ዝቅተኛው ወለል ላይ ከሚገኘው ላብ አደሩ ድረስ ለመኖር ከብዶታል ሲሉ የሚያስረዱት ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)፣ የዋጋ ግሽበቱ ዋነኛ ምክንያት ምርታማ የሆኑ አካባቢዎች ሰላም ማጣታቸው መሆኑን ይገልጻሉ።

አክለውም የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት ፈተና ውስጥ መግባቱ ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጽኦ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ዶ/ር ጉቱ፣ ልክ እንደ አቶ ሽመልስ ምርት እና ምርታማነት ቀንሷል የሚል አቋም አላቸው። ለዚህም ምክንያት ያሉትን ሲያስቀምጡ፣ በአምራች አካባቢዎች የጦርነት እንቅስቃሴ መኖሩ ነው።

ሁለተኛው የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት በተለይ የኢኮኖሚ ደጋፊ የሚባሉ ምዕራባውያን አገራት ጋር ያለው ግንኙነት ጥሩ አለመሆን፣ አገሪቱን የምታገኛውን የኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲሁም ከንግድ ጋር የተያያዘ የውጪ ምንዛሬ አሳጥቷታል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በመጻፍ እና ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት አብዱልመናን መሐመድ በበኩላቸው “መንግሥት በተደጋጋሚ የዋጋ ግሽበቱ ብሎ የሚጠቅሰው ዋናውን ምክንያት ወደ ኋላ ሸሽጎ ነው” ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ምርት ደብቆ ዋጋ ጨምሮ ለመክበር የሚደረግ የነጋዴዎች እንቅስቃሴ መንግሥት የሚያነሳው ምክንያት ሲሆን፣ ይህ ግን ዋነኛው ምክንያት ግን አይደለም ይላሉ።

“አሁን ላለው የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ተጠያቂ መንግሥት ራሱ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ገንዘብ ማተም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ባንኮች ደግሞ ይህንን ገንዘብ ሲያበድሩ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው የብር መጠን ጨምሯል።”

ይህ በጦርነት እና በፖለቲካ አለመረጋጋት ምጣኔ ሀብቷ የደከመባት አገር ውስጥ ገንዘብ በገበያ ውስጥ መብዛቱ ኑሮ ያስወድዳል ይላሉ።

አብዱልመናን እንደሚሉት አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት መነሻ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የተለቀቀው ገንዘብ ከአገሪቱ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ያልተመጣጠ መሆኑ ነው።

“መንግሥት ይህንን ማመን አይፈልግም። መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ብዙ ተበድሯል” የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አብዱልመናን ይህ በአፋጣኝ መስተካከል እንዳለበት ይመክራሉ።

አብዱልመናን ምርታማ የሆኑ አካባቢዎች ሰላም ማጣታቸው ለምርት መቀነስ ምክንያት መሆኑን ቢስማሙም፣ ኢኮኖሚው ሲቀዛቀዝ በገበያው ውስጥ ያለውን የገንዘብ ፍሰት መቀነስ ሲገባ መንግሥት ተቃራኒውን በማድረግ እንዳባባሰው ያምናሉ።

የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ለምን በአጭር ጊዜ መፍትሔ አያገኝም?

ዶ/ር ጉቱ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት “አሁን ባለው ሁኔታ መፍትሔ የለውም። ይህ ተሰምሮበት በግልጽ ልንነጋገርበት ይገባል” ይላሉ።

አክለውም “አሁን ባለው ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታ በስድስትም ሆነ በዘጠኝ ወር ውስጥ ለሕዝቡ እፎይታ የሚሰጥ ነገር ማድረግ ይቻላል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።”

አገሪቱን ላጋጠማት የዋጋ ግሽበት በአጭር ጊዜ መፍትሔ የሚሆን ተስፋ የለም እንዲሉ ያደረጋቸውም “ችግሩ በጣም ውስብስብ” በመሆኑ የተነሳ እንደሆነ ይናገራሉ።

ዶ/ር ጉቱ “የምርታማነት እጥረት ምክንያቱ ፖለቲካ ነው” ብለው “ነገሩ አሁን በተያዘበት መንገድ ደግሞ በአንድ እና በሁለት ዓመት ውስጥ እንኳን ወደ ቦታው የሚመለስ አይደለም” ይላሉ።

ምርቶቻቸውን የሚሸጡልን እና የእኛን ከሚገዙ የውጪ አገራት ጋር ያለን ጥሩ ግንኙነት ሻክሯል፤ ይህንንም ወደ ቦታው መመለስ በሁለት እና ሦስት ወር የሚሆን አይደለም ይላሉ።

አብዱልመናን በበኩላቸው መንግሥት ይህንን ችግር በሚገባ ተረድቶ በስድስት ወር እና በአንድ ዓመት ውስጥ የከሰተውን የዋጋ ግሽበት ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ ቁርጠኝነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

“የዚህ ችግር መንስዔ ከአቅርቦት ጋር ብቻ የተያያዘ እንደሆነ የሚያስቡ ከሆነ ችግሩ መፍትሔ አያገኝም” የሚሉት አብዱልመናን መንግሥት በራሱ በኩል ጠንከር ያሉ ቁርጠኛ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈለገው ይመክራሉ።

ለዚህም መንግሥት በአፋጣኝ ማድረግ ያለበት “ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ መቀነስ ነው፤ ይህ ደግሞ ወገብን ማሰር ይጠይቃል። በተጨማሪ መንግሥት አስፈላጊነታቸው ጥያቄ ውስጥ ያሉ ፕሮጀክቶችን ማስቆም፣ አስፈላጊ የሚባሉ ፕሮጀክቶችንም ቢሆን ለጊዜው መፍትሔ እስኪገኝ ማዘግየት አለበት” ሲሉ ይመክራሉ።

እንዲሁም “የኢትዮጵያን ብር የመግዛት አቅም ከውጪ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ የማውረድ እንቅስቃሴ ወደ አገር ቤት የሚገቡ እቃዎችን ስለሚያንር በአስቸኳይ መቆም አለበት፤ መንግሥት እነዚህን እርምጃዎች የሚወስድ ከሆነ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ውጤት ማየት ይቻላል” ይላሉ አብዱልመናን።