ሩሲያ ዕድሜያችው ከ18 በላይ የሆኑ በወዶ ዘማችነት እንዲመዘገቡ ቅስቀሳ ጀመረች

የሩሲያ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በርካታ የሩሲያ ወታደሮች በጦርነቱ ተገድለዋል

ከቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ቮሎሶቮ ከተማ በድምጽ ማጉያ ተደበላልቃለች።

እነዚህ በየመንገዱ የተተከሉት ሃሎ ሃሎ ድምጾች ወትሮ የብሔራዊ መዝሙር ነበር የሚያሰሙት።

ወትሮ ‘አትነሳም ወይ!’ የሚሉ ብሔራዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ድምጾችን ነበር የሚያስተጋቡት።

አሁን ግን ቀጥታ ወታደር መመልመል ይዘዋል።

‘ሁለት የወዶ ዘማቾች ባታሊዯን ጦር እየገነባን ነው። ዕድሜያችሁ ከ18 እስከ 60 የሆናችሁ ተመዝገቡ’ የሚል ጥሪን ደጋግሞ እያቀረበ ነው።

ይህ መልእክት ቀኑን ሙሉ ሲያስተጋባ ነው የሚውለው።

በዚህ የጎዳና ላይ ሃሎ ሃሎ ብቻ ሳይሆን መልዕክቱ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች፣ በቴሌቪዥን እና በቢልቦርድ ጭምር እየተላለፈ ነው። ወዳችሁ ዝመቱ እየተባለ ነው። ምልመላው ለአጭር ጊዜ እንደሆነም እየተነገረ ነው።

ሩሲያ በዩክሬን በአጭር ጊዜ ውስጥ እቀዳጀዋለሁ ያለችው የጦር ሜዳ ድል ከዕለት ዕለት እየራቀ መጥቷል።

ሩሲያ በበርካታ የጦር ግንባሮች ከምታስመዘግበው ድል ይልቅ የምታጣቸው ወታደሮች በዝተዋል።

በቮሎሶቮ ከተማ አንድ ሽማግሌን በወዶ ዘማቾች ምልመላ ጥሪ ላይ ስላለቸው ምልከታ የቢቢሲው ዊል ቨተርኖትን ጠይቋቸው ነበር። “ወጣት ብሆን ኖሮ እዘምት ነበር” ይላሉ።

“በቦምብ ነበር ማጥፋት” ሲሉ ዛቱ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይሁንና ጋዜጠኛው በዚህች ከተማ ያነጋገራቸው ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ስሜት አላሳዩም።

“ስለዚህ ጦርነት ለማውራት ራሱ ያማል” አሉት አንዲት ሴት። “ወንድም ወንድሙን መግደል ትክክል ሊሆን አይችልም።”

ከቤተሰቦቿ አንዱ ልዝመት ቢል ምን ሊሰማት እንደሚችል ስትጠየቅ፤ “ሬሳቸው ይመጣላ ” ሰትል ሁለት ጊዜ እንኳ ሳታስብ ምላሽ ሰጥታለች።

የበርካታ ወታደሮች ሬሳ በእርግጥም እየመጣ ነው።

ሩሲያ ቁጥር ይፋ ማድረግ አትወድም። ይሁንና ምዕራባዊያን እያወጡት ባለው አሐዝ ከ70 አስከ 80ሺህ ወታደሮች ወይ ተገድለዋል ወይ ተጎድተዋል። ይህ በስድስት ወራት ውስጥ የሆነ ነው።

አዳዲስ ምልምሎችን ለማባበል የሩሲያ ባለሥልጣናት ገንዘብን እየተጠቀሙ ነው። ረብጣ ሩብል ኑ እና ውሰዱ እየተባሉ ነው ወጣቶች። መሬትም እየተሰጣቸው ነው። ልጆች ካሏችሁ ደግሞ ጥሩ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ይደረጋል እየተባሉም ነው።

በወር 5 ሺ 700 ዶላር የሚሰጣቸው ምልምሎች አሉ።

ይቺ ሴት ግን ነገሩ እንደዚያ እንዳልሆነ ነው የምታወራው።

“ሰዎች አሁን ገንዘቡ ብዙ መሆኑን አይደለም የሚያዩት። ከዩክሬን የሚመለሱ ሰዎች እንዴት እንደተታለሉ ነው የሚናገሩት። መንግሥት ከዚህ ወዲህ በገንዘብ ወጣት አታሎ መመልመሉ የሚሳካለት አይመስለኝም።”

አንዳንድ ሰዎች ግን በቀረበው ገንዘብ ደስተኞች ናቸው። ለመዝመትም ዐይናቸውን አያሹም።

ኒና ቹባሪና እናት ናት። የቭጌኒ ልጇ ነው። ካሬሊያ መንደር ነበር የሚኖሩት። ካልዘመትኩ ብሎ ሄደ። ኒና እንደምትለው ልጇ ምንም አይነት የወታደርነት ልምድ አልነበረውም። መሣሪያ ተሰጥቶት ወደ ዩክሬን አቀና።

በቀናት ውስጥ ተገደለ። “ልጄ በ24 ዓመቱ ተቀጨ” ትላለች ኒና ቹባሪና።

ኒና በሞስኮ በሚገኝ አንድ መናፈሻ ውስጥ እንድንገናኝ ፈቀደች። በአንድ የዳቦ ማጋገሪያ ቤት ውስጥ በትርፍ ሰዓት ሥራ ትሰራለች።

ኒና
የምስሉ መግለጫ, ኒና ቹባሪና

ይህ ፋታ የማይሰጠው ዳቦ የመጋገር ሥራ ሐዘኗን ለመርሳት እንደረዳት ነገረችኝ።

ልጇ ዘመቻ እንዳይሄድ ምንኛ እንደለመነችው አስረዳችኝ። “እባክህን ልጄ ስማኝ እያልኩ ሸኘሁት። ጦርነት አለ። 'ትሞታለህ' አልኩት። 'እማዬ ዝምብለሽ አትጨነቂ፤ ሁሉም መልካም ይሆናል' ብሎኝ ሄደ።”

ኒና የሩሲያ መንግሥት ወጣቶቹን የሚያባብልበት መንገድ ትክከል እንዳልሆነ ትናገራለች።

“ልጆቹ ያለ በቂ ሥልጠና ወደ ግንባር ይወሰዳሉ። ጥይት ማብረጃ ይሆናሉ።”

በሩሲያ ከተሞች መዘዋወር ሕዝቡ በጦርነቱ ላይ ያለውን አመለካከት ለመረዳት ይረዳል። ብዙ ሰው ይህን ጦርነት ከፑቲን ጎን ቆሞ ይደግፋል ለማለት ይከብዳል።

በእንግሊዝኛ የዜድ [Z] ፊደል የተጻፈበት ጦርነቱን የሚደግፈው የተሽከርካሪዎች ምልክት አሁን አሁን በሩሲያ መንገዶች እምብዛምም አይታዩም።

የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፓቬል ሉቪን ከዚህ ወዲያ የሩሲያ ወታደሮች ለፑቲን ዝናና ክብር ሲሉ ለመሞት ፈቀደⶉች አይመስሉኝም ይላሉ።

“ፑቲን ታላቁን የሩሲያ ሥርወ መንግሥት ለመመለስ በማለማቸው ለዚህ ቅዥት የሚሞቱ ከእንግዲህ ብዙ አይደሉም። ይህም የሚሆነው በሩሲያ በጦርነቱ ዙሪያ የሕዝብ ስምምነት ስላለ ነው።”