የፑቲን አጋር የሆኑ ግለሰብ ሴት ልጅ ሞስኮ ውስጥ ተገደለች

የሩሲያውፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ አጋር የሆኑ ግለሰብ ሴት ልጅ ሞስኮ አቅራቢያ መገደሏ ተሰማ።
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ዳርያ ዱጊና ወደ ቤት ስታቀና እየነዳች የነበረው መኪናዋ በእሳት ተያይዞ ፈንድቶ ህይወቷ አልፏል።
"የፑቲን አንጎል" በመባል የሚታወቁት ሩሲያዊው ፈላስፋ አባቷ አሌክሳንደር ዱጊን የጥቃቱ ዓላማ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል።
ዱጊን የሩሲያው ፕሬዝዳንት የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑ የሚታመን ታዋቂ ጽንፈኛ ብሔርተኛ አስተሳሰብ አራማጅ ናቸው።
የሩስያ ሚዲያ 112 እንደዘገበው ዱጊን ባለቀ ሰዓት ከልጃቸው ተነጥለው ለመጓዝ ከመወሰናቸው በፊት ጥንዶቹ ቅዳሜ ምሽት ከተካሄደው ዝግጅት መገባደድ በኋላ አብረው ሊመለሱ አቅደው ነበር።
በቴሌግራም ላይ የተለቀቀ ያልተረጋገጠ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ሲረባረቡ ዱጊን በድንጋጤ የሚቃጠለውን ተሽከርካሪ ሲመለከቱ ይታያል።
ቢቢሲ ተተንቀሳቃሽ ምስሉን ማረጋገጥ አልቻለም።
የህግ አስከባሪ አካላት ታስ ለተሰኘው የዜና ወኪል እንዳረጋገጡት አንዲት ሴት አሽከርካሪ በቦልሺዬ ቪያዚሚ መንደር መኪናዋ ፈንድቶ ህይወቷ ማለፉን ተናግረዋል። ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም።
ከሩሲያ ባለስልጣናት እስካሁን ምንም አይነት ይፋዊ አስተያየት አልተሰጠም።
በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ይፋዊ ወንበር ባይኖራቸውም የዱጊና አባት የሩሲያው ፕሬዝዳንት የቅርብ አጋር ሲሆኑ “የፑቲን ተጽዕኖ ፈጣሪም” ይባላሉ።
የፈላስፋው ልጅ ዳሪያ ዱጊና ታዋቂ ጋዜጠኛ ስትሆን የዩክሬንን ወረራንም በግልጽ የምትደግፍ ነበረች።
የ30 ዓመቷ ጋዜጠኛ ከሩሲያ ወረራ ጋር በተያያዘ "ሐሰት መረጃ" ላይ ትሳተፋለች በሚል በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ማዕቀብ ተጥሎባታል።
በግንቦት ወር ጦርነቱን "የሥልጣኔ ግጭት" ስትል በቃለ መጠይቅ ወቅት ገልጻለች። እሷም ሆነች አባቷ በምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ ስለተጣለባቸው እንደሚኮሩ ተናግራለች።
አሌክሳንደር ዱጊን እአአ በ 2015 ሩሲያ ክሬሚያን በኃይል ወደ ግዛቷ እንድትቀላቀል ሲደረግ ተሳትፈዋል በሚል በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
ጽሑፎቻቸው የቭላድሚር ፑቲን የዓለም ዕይታ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ይነገርላቸዋል።
ዱጊን ለዓመታት ሞስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ራሷን በኃይል እንድታሳይ የጠየቁ ሲሆን በዩክሬን የሚካሄደውን የሩሲያ ወታደራዊ እርምጃንም ይደግፋሉ።












