በክሬሚያ የሚገኙ የሩስያ መርከቦች የድሮን ጥቃት ደረሰባቸው

የፎቶው ባለመብት, GOOGLE MAPS
በክሬሚያ የሚገኙ የሩስያ ጦር ኃይሎች የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ዒላማ ሆነዋል።
በሴቫስቶፖል ከተማ በሩሲያ ጥቁር ባህር መርከቦች ላይ ጥቃት ለማድረስ ያነጣጠረ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን ቅዳሜ ተመትቶ መውደቁን በሩሲያ የተሾሙት የየግዛቲቱ መሪ ተናግረዋል።
በኃይል በሩሲያ ግዛትነት ስር በገባችው ክሬሚያ በዚህ ወር በሩሲያ ኃይሎች እና ተተቋማት ላይ ተከታታይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት የተባበሩት መንግስታት ተቆጣጣሪዎች በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኘውን የዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያን እንዲጎበኙ የሚያስችለውን ስምምነት ተቀብለዋል።
ቅዳሜ ማለዳ ላይ በተሰራጨ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል በሴቫስቶፖል የሩስያ ጥቁር ባህር መርከብ በሚገኝበት አካባቢ ጭስ ሲወጣ አሳይቷል። ቢቢሲ ምስሉን ማረጋገጥ አልቻለም።
በሩሲያ የተሾሙት አስተዳዳሪው ሚካሂል ራዝቮዛይቭ የችግሩን አሳሳቢነት አሳንሰውታል።
የመርከቦቹ የአየር መከላከያ ምላሽ በመስጠት የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን ማውደሙን ተናግረዋል። "በዋናው መሥሪያ ቤት ጣሪያ ላይ ወድቋል። ምንም ጉልህ ጉዳት አልደረሰም። ማንም አልተጎዳም" ብለዋል።
ራዝቮዝሃይቭ ቅዳሙ ዕለትም የፀረ-አውሮፕላን ስርዓቶች በሴቫስቶፖል እንደገና ሥራ ላይ እንደዋሉ ተናግረዋል። ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ በክሬሚያ በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃቶች ደርሰዋል።
ከእነዚህም መካከል አንዱ በሴቫስቶፖል አቅራቢያ በሚገኝ የአየር ማረፊያ ሲሆን አርብ ዕለት ደግሞ በአካባቢው ወደብ ላይ ተፈጽሟል።
በወሩ መጀመሪያ ላይ በክሬሚያ ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ በምትገኘው ሳኪ የሩሲያ ጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ዘጠኝ የሩስያ ጄቶች ወድመዋል።
በወቅቱ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ብዙ የሩሲያ ቱሪስቶች በአቅራቢያው ካለ ሪዞርት ሲሸሹ ታይቷል።
ክሬሚያ እአአ በ2014 በሩስያ የተወረረች እና በኃይል የተወሰደች ሲሆን ዩክሬን ልታስመልሳት ቃል ገብታለች።
የኪዬቭ መንግስት በቅርብ ጊዜ በተፈፀሙ ጥቃቶች እጁ ስለመኖሩ ከማረጋገጥም ሆነ ከመካድ ተቆጥቧል።
የምዕራባውያን ባለስልጣናት እነዚህ ጥቃቶች በሩሲያ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ የሥራ እና የስነ-ልቦና ተፅእኖ እያሳደሩ ነው ይላሉ።

በሌላ ዜና የዛፖሪዝሂሂያ የኑክሌር ጣቢያ ደህንነት በዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች መጎብኘቱ ወደነበረበት ሊመልሰው ይችላል ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ገልጸዋል።
የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቆጣጣሪዎች ወደ ተቋሙ እንዲገቡ ፈቃድ ትሰጣለች ካሉ በኋላ ነው ይህንን ያሉት።
ባለፈው ሳምንት ክሬምሊን እና ኪዬቭ በኒውክሌር ጣቢያው ጥቃት በማድረስ የኒውክለር አደጋ ስጋት ተደቅኗል በማለት እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ ነበር።
ሩሲያ ካርኪቭን፣ ዲኒፕሮን እና ማይኮላይቭን እና ሌሎችንም ከተሞች ዒላማ በማድረግ በለሊት የማጥቃት ስልቷን ቀጥላለች።
በሩሲያ የተሾሙት የማሪዎፖል ከንቲባ ከግድያ ሙከራ ተርፈዋል ተብሏል።
የሩስያ የመንግስት ቲቪ ጋዜጠኛ እንዳለው ከንቲባው ኮስትያንቲን ኢቫሽቼንኮ በመኪና ውስጥ እያሉ በአቅራቢያቸው ፍንዳታ መድረሱን ተናግሯል።
ቅዳሜ ዕለት ሌሎች ሁለት የእህል መርከቦች ከዩክሬን ከተነሱ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቱርክ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
መርከቦቹ እህል ጭነው ወደ አፍሪካ ቀንድ ማምራታቸውን መመልከት “በጣም ልብ የሚነካ” ነው በማለት ተናግረዋል። እነዚህ መርከቦች “በአስቸኳይ ረሃብ ለሚሰቃዩት እርዳታ” ለማድረስ ይረዳሉ ብለዋል።
ጉቴሬዝ አክለውም ከሩሲያ የምግብ እና ማዳበሪያ ማጓጓዝ መቻሉ እየናረ ከመጣውን የኑሮ ውድነት አንጻር ወሳኝ ነው ብለዋል።












