ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማጠናከር ቆርጫለሁ አለች

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ-ኡን እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ መቁረጧን አስታወቀች። ግንኙነቱ ሁሉን አቀፍ ነውም ብላለች።

ቪላድሚር ፑቲን ለአቻቸው ኪም ጆንግ ኡን በላኩት ደብዳቤ የግንኙነታቸው መዳበር ሁለቱንም አገራት እንደሚጠቅም አስገንዝበዋል።

ፑቲን ይህን ደብዳቤ የላኩት የፒዮንግያንግን የነጻነት ቀን አስመልክተው ነው።

ለዚህ የፑቲን ደብዳቤ ምላሽ የሰጡት አቻቸው ኪም ሁለቱ አገራት ጥብቅ ግንኙነታቸው የጀመረው በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጃፓንን ከረቱ በኋላ እንደሆነ አውስተዋል።

አክለውም፣ “ይህ ግንኙነታችን ገና ይጎመራል” ብለዋል።

ግንኙነቱ ስትራቴጂክና ታክቲካዊ ሆኖ ከጠላት አገር የሚመጣን ያልተጠበቀ ጥቃት ለመመከት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።

ይሁንና ፒዮንግያንግ ጠላት ያለችውን አገር በስም አልጠቀሰችም። ብዙውን ጊዜ የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ሚዲያ ጠላት ብሎ የሚጠቅሳት የዓለም ልዕለ ኃያሏን አሜሪካንን ነው።

የሶቭየት ኀብረት በአንድ ወቅት ጥብቅ የሰሜን ኮሪያ ወዳጅ አገር የነበረች ሲሆን፣ የባሕል እና የኢኮኖሚ ትብብታቸውም የላቀ ነበር።

ይሁንና የሶቭየት ኅብረትን መፍረስን ተከትሎ ይህ ግንኙነት ተቀዛቅዞ ቆይቶ ማንሰራራት የጀመረው ሩሲያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሆድና ጀርባ መሆን በጀመረችበት በፈረንጆቹ 2020 መባቻ ነው።

በሐምሌ ወር ሩሲያ ሁለቱን በዩክሬን ተገንጣይ ግዛቶች ራስ ገዝ መሆናቸውን ሩሲያ ካስታወቀች ወዲህ ለእነዚህ አወዛጋቢ ግዛቶች እውቅና በመስጠት ሰሜን ኮሪያን የቀደማት የለም።