ከስልሳ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ በእጅ ጫማ እያመረተ የሚሸጠው ሸዋ ጫማ

ኬጋን አስላንያን ከሸዋ ጫማ ፋብሪካ ሠራተኞች ጋር በፋብሪካው ውስጥ ከማሽኖቹ ጋር የቡድን ፎቶግራፍ 1965

የፎቶው ባለመብት, Aslanian

የምስሉ መግለጫ, ኬጋን አስላንያን (ከመሃል) ከሸዋ ጫማ ፋብሪካ ሠራተኞች ጋር በ1965

ቫርታን አስሌንያን ይባላል፤ ለኢትዮጵያ እንግዳ አይደለም።

እንደውም ቫርታን ሦስተኛው የአርመን ኢትዮጵያዊ ትውልድ ነው።

ወደ ኋላ ሲቆጠር መጀመሪያ ኢትዮጵያ የተወለዱት አያቱ ናቸው።

አሁን በስድሳዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ቫርታን፣ “በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1898 አያቴ ማለትም የእናቴ እናት ነበርች ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ የተወለደችው” ይላል።

የአባቱ ቤተሰቦች ደግሞ ኢትዮጵያ በ1911 እንደገቡ በዚያው መቅረታቸውን ያስረዳል።

“እናቴ የተወለደችው እንጦጦ ነበር። እዚያ ትንሽ ካደገች በኋላ ወደ አዲስ አበባ ወረዱ. . . ከዚያ እናቴ ተወለደች እኔም ደግሞ ቀጠለኩ” ይላል ቫርታን።

እርሱም ሁለት ሴት ልጆችን እዚሁ ኢትዮጵያ ወልዶ፣ የአባቱን የጫማ ፋብሪካ በመረከብ እየሠራ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ የሚናገር የአርመን ዝርያ ነው።

የአስላንያን ቤተሰብ ወደ አዲሰ አበባ ከመጣ በኋላ ለእረፍት ወይም ለጉብኝት ካልሆነ በስተቀር “ከአገራችን [ከኢትዮጵያ] ወጥተን አናውቅም” ይላል ቫርታን።

ቫርታን ለቤቱ የመጨረሻው ልጅ ሲሆን 4 ታላቅ እህቶች አሉት።

እርሱም ’ሸዋ ጫማ’ የተሰኘውን የአባቱን ጫማ ፋብሪካ የተረከበው፣ አባቱ ከ37 ዓመታት በፊት ሲሞቱ ነበር።

“እህቶቼ ወደ ጫማው ሥራ የመግባት ፍላጎት አልነበራቸውም። ለነገሩ እኔም አልነበረኝም፤ ነገር ግን ተስማምተን የአባታችንን ቅርስ ለማቆየት እኔ እንድቀጥልበት በጋራ ወሰንን።”

“. . . ያኔ ጎረምሳ ነበርኩኝ። አባቴ ሲሞት ከልጆቹ መካከል እኔ ነበርኩ የአባቴን መንገድ ለመከተል የወሰንኩት። እስካሁንም እየሠራሁ እገኛለሁ” የሚለው ቫርታን አባቱ ፋብሪካውን ያቋቋሙት እርሱ ሳይወለድ በፊት እንደነበር ይናገራል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሁን ጊዜ የሸዋ ጫማ ፋብሪካ ወደ ሚገኝበት መሐል ፒያሳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ወረድ ብሎ ካለበት ቦታ ከመጣ 67 ዓመታትን አሰቆጥሯል።

ከዚያ ቀደም ደግሞ ፒያሳ ‘ጅማ ባር’ የሚባለው አቡነ ጵጥሮስ አካባቢ ለ15 ዓመታት ሱቅ በመቀያየር ሲሰሩ እንደነበር ቫርታን ያስታውሳል።

በኋላ ግን ሌላ አርመን-ኢትዮጵያዊ የሆነ እና ቦጎሰያን የሚባል የአባቱ ጓደኛ፣ ለአባቱ ንብረቶቹን በቋሚነት እንዲከራዩ ጥያቄ አቀረበላቸው።

የቫርታን አባት፣ ቦታ ከመቀያየር ይሻላል በማለት ቦጎሰያን ያቀረቡትን ጥያቄ በእሺታ ተቀበሉ።

ቫርታን አባቱ አስኪያርፉ ድረስ የጫማ ሥራውን እንደ ኑሮ ማሸነፊያ መንገድ አስቦት እንደማያውቅ ያስታውሳል።

“ጎረምሳ እያለሁ የሙዚቃው ዓለም በስሜት ይገፋፋኝ ነበር። ከእነ ቴዲ ላውንድሪ የማጂክ ፕሬስ ላውንድሪ ባለቤት፣ መንገሻ ወይም ‘ቢቢሻ’ በመባል የሚታወቀው እናም ሌሎችም ጋር በመሆን ሴቫን ባንድ የሚባል አቋቁመን ሙዚቃን ለ22 ዓመታት ሠርቻለሁ” ይላል።

የቫርታን የሙዚቀኛነት ሕይወት በአባቱ ድንገተኛ ሞት ተቋረጠ።

የአባቱን ፋብሪካ ለማስቀጠል ሲል ቫርታን ፊቱን ከሙዚቃ ወደ ጫማ ሥራ አዞረ።

ሙዚቃውን እና የጫማ ሥራውን ጎን ለጎን ለማስኬድ አስቦ እንደሚያውቅ የሚናገረው ቫርታን፣ ነገር ግን ወደ ጫማ ሥራ መግባቱ እና የአባቱን ፈለግ መከትሉ እንደማያስቆጨው ያስረዳል።

አሁንም ቢሆን ግን የግል ስሜቱን ለማርካት አልፎ አልፎም ቢሆን ሙዚቃ ይጫወታል።

ቫርታን የሚያስተዳድረው እና ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በሥራ ላይ የነበረው ፋብሪካ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ከጎረቤት በመጣ እሳት የተነሳ ወደመ።

 ቫርታን ግን እሳት የተጎዳውን የአባቱ ቅርስ የሆነውን ፋብሪካ እንደ አዲስ ለማስጀመር ጥርሱን ነክሶ መታገሉን ይናገራል።

“የእሳት አደጋም በሰዓቱ በመድረሳቸው ቢያንስ ማሽኖቻችንን ማትረፍ ችለናል። ግን የነበሩን የተመረቱ ጫማዎች እና ሌሎች በዋጋ የማይተመኑ ንብረቶችን ያጣን ቢሆንም ሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱ የሚያስመሰግን ነው” ይላል ቫርታን አደጋውን በማስታወስ።

ቫርታን ከአደጋው በኋላ ሸዋ ጫማ ፋብሪካ ሠራተኞች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Aslanian

የምስሉ መግለጫ, ቫርታን ከአደጋው በኋላ ሸዋ ጫማ ፋብሪካ ሠራተኞች ጋር

በእሳት አደጋው የተነሳ ለቅርስነት ብለው ስያስቀመጧቸው የጥንት ጫማ ሞዴሎች ወይንም የመጀመሪያዎቹ ጫማዎቻቸውም ተቃጥለዋል።

ማትረፍ ከቻሏቸው ጫማዎች መካከል የቫርታን አባት የዛሬ 57 ዓመት የሰሩት ጫማ ይገኝበታል።

ሸዋ ጫማ በአጠቃላይ 25 ሞዴሎች እንዳሉት እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ሳፋሪ’ የሚባለው ሞዴል በመሥራት የመጀመሪያው ፋብሪካ መሆኑን ቫርታን ይናገራል።

ሁሉም የፋብሪካው ጫማዎች በእጅ የሚሠሩና ደረጃቸውን የጠበቁ ‘አርቲዛናል’ ሥራ መሆናቸውንም ቫርታን በኩራት ያስረዳል።

ከእሳቱ የተረፈው ከ57 ዓመት በፊት ኬጋን የሠሩት ጫማ

የፎቶው ባለመብት, Aslanian

የምስሉ መግለጫ, ከእሳቱ የተረፈው ከ57 ዓመት በፊት ኬጋን የሠሩት ጫማ

ፋብሪካው በቀን ውስጥ የሚያመርታቸው በእጅ የሚሠሩ ጫማዎች በቁጥር አነስተኞች ናቸው።

ይህ ደግሞ በአገሪቱ ከሚገኙ ትልልቅ የጫማ ፋብሪካዎች ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ቫርታን በቀን በሺህዎች የሚቆጠሩ ጫማዎች የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ባሉበት አገር፣ በእጅ እየሰሩ መቀጠል ትልቅ ስጋት ቢሆንበትም ቤተሰቡ ለስድስት አስርት ዓመታት ይዞት የመጣው ስም ግን በቀላሉ ይጠፋል ብሎ አያስብም።

“በእርግጥ የኑሮ ውድነትና ሌሎችም ነገሮች ተደማምረው ሥራችንን የሚያከብዱብን ነገሮች እየመጡ እንደሆነ ይታወቀኛል። እኛ የምንወዳደረው በምናቀርበው ጥራት፣ እውቀትና ለደንበኞቻችን የቅርብ አገልግሎት በመሆኑ በሺህ ከሚያመርቱ ድርጅቶች ጋር አንወዳደርም።

“ደንበኞቻችንአብረውን ለዓመታት የቆዩ ናቸው። በሥራ ቢሆንም ቤተሰብ ነን ማለት ይቻላል። እርሱም ለእኛ በቂ ነው” ይላል ቫርታን።

ፋብሪካቸውን ምን ልዩ እንደሚያደርገው ሲያብራሩም፣ የጫማዎቹ መልክ አለመቀያየሩ እና እስከ 47 ቁጥር ድረስ ጫማ ማምረታቸው እንደሆነ ይጠቅሳል።

ትልልቅ ቁጥሮችን መሥራት ከባድ የሚያደርገው የጫማው ‘ሞልድ’ [ቅርጽ ማውጫ] አለመገኘቱ ነበር በማለት የሚያስረዳው ቫርታን፣ አሁን ግን ኢትዮጵያ ‘ሞልድ’ መሥራት ስለጀመረች ማንኛውንም ቁጥር ለመሥራት ቀላል ሆኗል ሲል ያክላል።

“ያ ባይሆን ግን ‘ሞልዱን’ ከጣልያን ወይም ከቻይና ማስመጣት ግድ ይሆናል። እንደሱ ማድረግ ደግሞ ከባድ ነው። አንድ ሰው ለአንድ ጫማ ስንት ሺህ ብር ሊከፍል ነው? ለሥራ አይመችም።”

የሸዋ ጫማ ታዋቂው የ50 ዓመት ሞዴል

የፎቶው ባለመብት, Aslanian

የምስሉ መግለጫ, የሸዋ ጫማ ታዋቂው የ50 ዓመት ሞዴል

ቫርታን ወደ ጡረታ እየተጠጋ ሲመጣ ልጆቹ የእርሱን ፈለግ መከተላቸው ወይ አለመከተላቸው ቢያሳስበውም እነርሱ የወደዱትን እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል።

የቫርታን ሚስት የጣልያን እና የአይርላንድ ክልስ ስትሆን የሚስቱም ቤተሰብ ኢትዮጵያ የቆዩና የመኪና መለዋወጫ ንግድ ላይ የተሰማሩ ናቸው።

የቫርታን የመጀመሪያ ልጅ የመኪና መለዋወጫ ድርጅት ውስጥ ትሠራለች።

ሁለተኛዋ ደግሞ “የአይርሽ ደሟ ጠርቷት መሆን አለበት አየርላንድ እየሠራች ነው። ትልቋ ግን አልፎ አልፎ ወደ ጫማውም ሥራ ስለምትመጣ ጊዜው ሲደርስ የፈለገችውን መርጣ መሥራቷ አይቀርም” ይላል ቫርታን።

“ለእኔ ዋናው ነገር ልጆቼ ደስተኛ መሆናቸው ነው። ደግሞም ከሁሉም በላይ ትልቅ፣ ትንሽ፣ ሃብታም ምናምን ሳይሉ ሁሉንም ሰው እንዲያከብሩ አስተምሬአቸዋለሁ።”

በመጨረሻም ልጆቹን ትጉ ሠራተኞች እንዲሆኑ በማስተማሩ ለወደፊቱ ብዙ ስጋት እንደሌለው በእርግጠኝነት ይናገራል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ከስልሳ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ በእጅ ጫማ እያመረተ የሚሸጠው ሸዋ ጫማ