የአውሮፓና የኢትዮጵያን ግንኙነት ወደ ቀደመው ለመመለስ በቂ መሻሻል አለመታየቱን የአውሮፓ ኅብረት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም፣ የኤርትራ ወታደሮች መውጣት እንዲሁም ያልተቋረጠ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና የተቋረጡ መሰረተ ልማቶች በትግራይ መመለስ የአውሮፓንና የኢትዮጵያን አጋርነት ለመመለስ ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸው ተገለጸ።
ከእነዚህም በተጨማሪ በሁሉም አካላት ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት ማስፈን ተገቢነትን በተመለከተ የአውሮፓ ኅብረት መሠረታዊ የሚላቸውን ጉዳዮች ለኢትዮጵያ መንግሥት በግልጽ ማቅረቡን ኅብረቱ ገልጿል።
ከዚህ ቀደምም መጨረሻ ላይ በተካሄደው የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት እነዚህ ሁኔታዎች መነሳታቸውን የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል በጻፉት ጽሑፍ ላይ አስፍረዋል።
ጆሴፍ ቦሬል ‘ታይም ቱ ስቶፕ ዘ ፎርጋትን ዋር ኢን ትግራይ’ (የተረሳውን የትግራይ ጦርነት ማቆሚያ አሁን ነው) በሚል በጻፉትና በአውሮፓ ኅብረት ይፋዊ ድረ-ገጽ ላይ ነሐሴ 05/2014 ዓ.ም በወጣው ጽሁፋቸው አውሮፓ ያላትን አቋም አንጸባርቀዋል።
በመጋቢት ወር ላይ የታወጀው የተኩስ አቁም እንዲሁም ፖለቲካው ውይይቶችን አስመልክቶ አንዳንድ መሻሻሎች ቢታዩም የአውሮፓ ኅብረትና የኢትዮጵያን ግንኙነት ወደቀደመው ለመመለስ በቂ መሻሻሎች አይደሉም ተብሏል።
በባለፈው የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ጉባዔም የአውሮፓ ኅብረት አገራት ይህንኑ መናገራቸውም ሰፍሯል።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በተፈጸሙ ጥሰቶች ምክንያት ግንኙነታቸው መሻከሩ ጋር ተያይዞ ኅብረቱ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚደርገውን የበጀት ድጋፍ ማገዱ ይታወሳል።
ሆኖም ኅብረቱ "ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ አላቆመም" ያሉት ጆሴፍ ቦሬል፣ ለዚህም እንደ ማሳያነት የጠቀሱት በቅርቡ በግጭቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በጤና እና በትምህርት ዘርፎች የተደረገውን የ80 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ነው።
ለሁለት ዓመታት ያህል የትግራይ ክልል ረሃብ እና ወሲባዊ ጥቃት እንደ መሳሪያ በሆኑበት አስከፊ ጦርነት ውስጥ ናት ሲሉ የኅብረቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን አስፍረዋል።
ምንም እንኳን የሰላም ውይይቶች በተፋላሚ ወገኖች ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ ቢነገርም "ምግብ፣ መድኃኒት፣ መብራት፣ ቴሌኮምና የባንክ አገልግሎት እንደ መሳሪያ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው" ብለዋል።
በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ እና የአውሮፓ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች በአዲስ አበባ ካሉ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከትግራይ አመራሮች ጋር መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚመለሱበትን ሁኔታ መነጋገራቸውንም ጠቅሰዋል።
እነዚህም ልዑካን ስለ ሰላም ሲወራ ቢሰሙም አሁንም ፀጥ ያለው ጦርነት እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
በቅርቡ ልዑካኑ ትግራይ ደርሰው ከመጡ በኋላ በነዳጅ፣ በጥሬ ገንዘብ እና በማዳበሪያ ላይ ተጥሎ ያለው ክልከላ መነሳት አለበት ያሉ ሲሆን፤ በክልሉ ተቋርጠው የሚገኙ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሰው ለሚጠግኑ ባለሙያዎች ደኅንነት የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከትግራይ አመራር ለፌደራል መንግሥት ይዘው መመለሳቸውም ተመልክቷል።
ይህንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ልዑካኑ ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ላይ አተኩረዋል ብሏል።
ተቋርጠው የሚገኙ መሠረታዊ አገልግሎቶች በተመለከተ የመንግሥት አቋም ግልጽ ነው ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ አገልግሎት ማስጀመር የሚቻልባቸው ሁኔታ መፍጠር እና የሰላም ንግግር መጀመር ቀዳሚ መሆን አለበት ብለዋል።
ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው ባለፈው ሰኔ ኢትዮጵያን ጎብኝተው የነበሩት የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነሩ ሌናርሲችንም ዋቢ በማድረግ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ እንዲሁም የሰዎች፣ የእቃዎችና የአገልግሎት እንቅስቃሴ ክርክርም ሆነ ድርድር የሚደረግበት አይደለም ብለዋል።
"ምክንያቱም ይህ ሕይወትን የማዳን ጥያቄ ስለሆነ ነው" ብለዋል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ እና ከዚያም በላይ ያለውን ግዴታ ያለ ምንም መዘግየት እንዲወጣ እንጠብቃለን። ይህ የፖለቲካ ሂደቱ እንዲጀመር በአንድ ወገን ቅድመ ሁኔታዎችን መቀበል ማለት አይደለም። ይህ አንድ መንግሥት ለሕዝቡ ያለውን ግዴታዎች ማክበር ነው” ሲሉ አስፍረዋል።
በትግራይ 4.8 ሚሊዮን፣ በአፋር 1.2 ሚሊዮን እንዲሁም በአማራ ክልል ከሰባት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በአጠቃላይ 13 ሚሊዮን ሕዝብ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚሹ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።
ምንም እንኳን ለእነዚህ ሕዝቦች ተደራሽነት መጠነኛ መሻሻል ቢኖርም በተለይም በትግራይ አሁንም ከፍተኛ ችግር እንደሆነም ተጠቅሷል።
በአገሪቱ ውስጥ በሌሎችም ክልሎች ውጥረቱ እየታየ ሲሆን የተለያዩ አገራዊ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች የአገሪቱን እና አልፎም የፀጥታ ሁኔታን እያባባሱ ይገኛሉ ተብሏል።
በቅርቡ የአል ሻባብ ታጣቂዎች ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ድንበር ላይ ሰርገው መግባታቸው ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ቀውስ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አጉልቶ የሚያሳይ እንደሆነም ጆሴፍ ቦሬል ጠቅሰዋል።
"መላውን የአፍሪካ ቀንድ የሚጎዳውን ይህንን ደም አፋሳሽ ጦርነት ማቆሚያው አሁን ነው" በማለት ኅብረቱ ሁሉም ወገኖች ውይይት እንዲያደርጉ እና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ተማጽኗል።
"ተፋላሚ ወገኖች ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት ጊዜው አሁን ነው" ያሉት ጆሴፍ ቦሬል ይህንንም ለሕዝባቸው ለአገራቸው እንዲሁም አገሪቷ ያለባት ተጋላጭነት በመላው ቀጣናው ላይ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ምክንያት ሊሆናቸው ይገባል በማለትም አስምረዋል።
"ለሰላም መስማማት ድፍረትን ይጠይቃል። ወደ ውይይት እና ስምምነት መምጣት ጦርነቱን ከመቀጠል የበለጠ ድፍረትን ይጠይቃል" ብለዋል።
አክለውም “በሰላም ሂደት መሳተፍ አንድ ፓርቲ ማሸነፍ፣ ሌላው ደግሞ መሸነፍ አይደለም።በጥልቅ ትርጉሙ የፖለቲካ አመራርን መለማመድ ነው። ትንሽ የዕድል መስኮት ቢኖርም ጊዜው አሁን ነው፤ ሁሉም ተፋላሚ አካላት ይህንን ዕድል እንዲጠቀሙ እንጠይቃለን” ብለዋል በጽሁፋቸው ጆሴፍ ቦሬል።












