በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ የደኅንነት ማረጋገጫ መሰጠቱ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, DW
የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በሚመለከት ለፌደራል መንግሥት የደኅንነት ዋስትና ደብዳቤ መላካቸው ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኞች እና ከምዕራባውያን አምባሳደሮች ጋር በመቀለ ከተገናኙ በኋላ ነው።
የምዕራባውያኑን ጉብኝት ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው መግለጫ፤ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ለሠራተኞች የሚሰጠውን የደኅንነት ማረጋገጫ በተመለከተ ለፌደራሉ መንግሥት ደብዳቤ ልከዋል ብሏል።
በዚህም መሠረታዊ አገልግሎቶቹን መልሰው ሥራ ለማስጀመር ለጥገና ወደ ትግራይ ክልል ለሚሰማሩ ሠራተኞች የደኅንነት ዋስትና እንደሚሰጥ የሚገልጽ ደብዳቤ በዲፕሎማቶቹ በኩል መላኩን የአውሮፓ ኅብረት አመልክቷል።
ዛሬ ሐምሌ 26/2014 ዓ.ም. የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር እንዲሁም በኢትዮጵያ የካናዳ እና የጣሊያን አምባሳደሮች ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመቀለ ተገናኝተዋል።
ልዩ መልዕክተኞቹ እና አምባሳደሮቹ ወደ መቀለ ሄደው ከህወሓት አመራሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ለፌደራል መንግሥቱ የሚሰጥ ደብዳቤ ከደብረጺዮን መቀበላቸውን የአውሮፓ ኅብረት አስታውቋል።
ኅብረቱ እንዳለው ቀደም ሲል ከፌደራል መንግሥት ጋር በተደረጉ ውይይቶች የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ስምምነት እንዳለ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ የተቋረጡትም መሠረታዊ አግልግሎቶች መልሶ ለማስጀመር ዋነኛው እንቅፋት ለጥገና የሚሰማሩ ሠራተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው በማለት ሲገልጽ ቆይቷል።
ወደ መቀለ አቅንቶ በነበረው የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ የጋራ ዲፕሎማሲያዊ ቡድን በኩል ከትግራይ አመራሮች በኩል የተሰጠው ዋስትና አገልግሎቶቹ በአስቸኳይ መልሰው እንዲጀመሩ በር ይከፍታል ተብሏል።
ይህ ደብዳቤ በክልሉ ተቋርጠው የሚገኙ እንደ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎቶችን ለመጠገን ወደ ክልሉ ለሚጓዙ ሠራተኞች ደኅንነት ማረጋገጫ ነው ተብሏል።
የምዕራባውያኑ የመቀለ ጉብኝት የተሰማው ባለፈው ሳምንት የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ልዩ መልዕክተኞቹ እና አምባሳደሮቹ ወደ መቀለ እንዲጓዝ የፌደራሉ መንግሥት መፍቀዱን ከተናገሩ በኋላ ነው።
የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይም የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛዋ አኔት ዌበር ኢትዮጵያ መግባታቸውና በአዲስ አበባ እና በመቀለ ቆይታ እንደሚኖራቸው ሰኞ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈው ነበር።
አምባሳደር ሬድዋን የምዕራባውያን አገራት ተወካዮቹ ወደ መቀለ እንዲሄዱ ተፈቅዷል ያሉት፤ ሐሙስ ሐምሌ 21/2014 ዓ.ም መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በየትኛውም ስፍራ፣ በማንኛውም ጊዜ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን በገለጹበት ወቅት ነው።
አምባሳደር ሬድዋን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ስለሚደረገው ንግግር የፌደራል መንግሥት አቋም በየትኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ቦታ ንግግር ማድረግ መሆኑን ለምዕራባውያኑ መናገራቸውን ገልጸዋል።
"ፖለቲካዊ ውይይት አስፈላጊ ነው"
ምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶች ወደ መቀለ ተጉዘው ከትግራይ ኃይሎች ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረቱ ባውጣው መግለጫ ላይ፤ “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመቋጨት ፖለቲካዊ ውይይት አስፈላጊ ነው” ብሏል።
ምዕራባውያኑ ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት ያሳዩት ጥረት የሚደነቅ ነው ያለ ሲሆን፤ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚካሄደውን ንግግር ለመደገፍ ዝግጁ ነን ብለዋል።
ልዑኩ በጦርነቱ ለተጎዱት በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ እርዳታ ማቅረቡ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ምዕራባውያኑ በነዳጅ፣ በጥሬ ገንዘብ እና በማዳበሪያ ላይ ተጥሎ ያለው ክልከላ መነሳት አለበት ያለ ሲሆን፤ ሁለቱም ወገኖች ከጥላቻ እና ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
ሁለት ዓመት ሊሆነው የተቃረበውን ጦርነት ለማብቃት በመንግሥትም ሆነ በህወሓት በኩል ድርድር ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ ካሳወቁ ወራት ተቆጥረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም “ከህወሓትም ይሁን ከማንኛውም ሰላም ፈላጊ ጋር የምንፈልገው ሰላም ነው፤ የሚቻል ከሆነ ለሰላም መቆም ችግር የለውም” ሲሉ ተናግረው ነበር።
የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደረገውን ውይይት የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ አዋቅሮ ሥራ መጀመሩን ኣሰውቋል።
ይህንንም ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ጋር በኬንያ መንግሥት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ኃይሎችን የሚወክል በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ የሚገኙ አባላት ያሉት ልዑክ መዘጋጀቱንና ለድርድር ለመላክ ዝግጁ እንደሆኑ ቢገልጹም ወኪሎቹ እነማን መሆናቸውን አላሳወቁም።
ከፍላጎት ባሻገር የተጀመረ ነገር ስለመኖሩ አስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የሌለ ሲሆን፣ የማደራደሩን ኃላፊነት በተመለከተ ሁለቱም ወገኖች የተለያየ ፍላጎት እንዳላቸው ከዚህ በፊት ማሳወቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳለው የገለጸ ሲሆን፣ የህወሓት መሪዎች ደግሞ በኅብረቱ ላይ ጥያቄ እንዳለቸው በመጥቀስ በኬንያ መንግሥት በአደራዳሪነት እንዲሳተፍ ይፈልጋሉ።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ዲፕሎማት ሞሊ ፊ ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም የታቀደው ድርድር በኬንያ ምርጫ መጓተቱን መናገራቸው ይታወሳል።
ዲፕሎማቷ በቀጣይ ሳምንት በኬንያ የሚካሄደው ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ድርድሩ ይጀመራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቦ ነበር።












