ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጠበቆች ማኅበር ቦርድ የሰጡት ሹመት ተቃውሞ ገጠመው

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Justice
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የቦርድ አባላት ውስጥ ሴት ባለሙያዎች አለመካተታቸው ተቃውሞ ገጠመው።
ከቀናት በፊት ሥራቸውን ከጀመሩት የቦርድ አባላት መካከል ሴት የሕግ ባለሙያዎች አለመካተታቸውን በተመለከተ ተቃውሞውን ያሰማው የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የሕግ ሙያ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትን የጠበቆች ማኅበር ማቋቋም ሳይቻል ቀርቶ በዚህ ዓመት ነበር በከፊል ዘርፉን የማስተዳደር ሥልጣን ይዞ ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገው።
ይህ ማኅበር በተቋቋመበት አዋጅ መሠረትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበሩን የቦርድ አባላት የሚሾሙ ሲሆን በዚህ መሠረት አባላቱ ተሹመዋል።
በዚህም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቅራቢነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰባት አባላት ያሉት ቦርድ የተሾመ ሲሆን፣ ከቦርድ አባላቱ መካከል አንዲት ሴት እንኳን አለማካተቱ ቅሬታ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።
ሳባት አባላት ባሉት ቦርድ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ አለመኖሩ ላይ ቅሬታ ያቀረበው እና ውሳኔው እንዳሳሳበው የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ገልጿል።
ማኅበሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባለው መረጃም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 3089 የፌደራል ጠበቆች ውስጥ 362ቱ ብቻ ሴቶች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።
በሙያው ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ በሚታመነው የዚህ ቦርድ የአመራር ቦታ ላይ ታዲያ ሴቶች አለመካተታቸው በሙያው ውስጥ ያሉ ሴቶችን ያላሳተፈ መሆኑ ጫናው ቀላል አይሆንምም ብሏል - ማኅበሩ።
የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ከዚህ ቀደም በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን ድርድር ሁለቱም ተደራዳሪ አባላትን በሚያዋቅሩበት ወቅት የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑትን ሴቶችን አላሳተፉም ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
የጠበቆች ማኅበር ቦርድ የማኅበሩን የሥራ ሂደት መከታተልን ጨምሮ በርካታ ቁልፍ ኃላፊነቶች አሉት።
ከእነዚህም መካከል የዲሲፕሊን ጉባዔ፣ የጥብቅና ሙያ መግቢያ ፈተና ኮሚቴ እና የጥብቅና ፈቃድ ገምጋሚ ኮሚቴዎች በሚወስኑት ውሳኔዎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ተቀብሎ መመርመር ብሎም በማኅበሩ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን መመልከት ይገኙበታል።
ሌላው የቦርዱ ቁልፍ ሥልጣን የጥብቅና ድርጅቶች የመድህን መጠን እና የ የጥብቅና አገልግሎት ክፍያ መጠንን እና የአከፋፈል ሥርዓትን በተመለከተ በመመሪያ የመወሰን ሥልጣን በአዋጁ ተሰጥቶታል፡፡
የጠበቆች ማኅበሩ ካሉት የአስተዳደር እና የአመራር መዋቅሮች መካከል ከፍተኛውን ሥልጣን የሚይዘው ሰባት አባላት ያሉት የሥራ አስፈጻሚው ክፍል ሲሆን ይህም በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጠ ነው።
ባለፈው ጥር 15/2014 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤም ማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚውን ሲመርጥ ከሰባቱ አባላት ፕሬዝዳንቷን ስንዱ አለሙን ጨምሮ ሦስቱ ሴቶች ነበሩ።
የሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበሩ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የፌደራል የጠበቆች ማኅበርን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ቦርዱ የሴቶችን ተሳታፊነት ያማከለ እንዲሆን ጠይቋል።
“የቦርዱ አባለት 50 በመቶ ብቃት ያላቸው ሴቶች እንዲሆኑ፣ በተደረገው ሹመት ላይ ማስተካከያ ተደርጎ የሴቶችን እኩልነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር የበኩልዎን ጥረት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን” ሲልም ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የቦርድ አባላት ሰባት ሲሆኑ፣ በሕጉ መሠረት የተሾሙትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።
መሾማቸው ከቀናት በፊት ይፋ የተደረገው ሰባቱ የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የቦርድ አባላት ፡-
1. አቶ ዓለምአንተ አግደዉ (ከፍትሕ ሚኒስቴር)…. ሰብሳቢ
2. አቶ ወንድሙ ግዛዉ (ከጠበቆች ማኅበር)……..ፀሐፊ
3. አቶ ብርሃኑ አመነዉ (ከጠቅላይ ፍ/ቤት) …......አባል
4. አቶ ታምሩ ወንድማገኝ (ከጠበቆች ማኅበር)….አባል
5. አቶ አብደላ አሊ (ከጠበቆች ማኅበር)….............አባል
6. ዶ/ር ብሩክ ኃይሌ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) .….አባል
7. አቶ ምህረቱ ቁምላቸዉ (ከፍትሕ ሚኒስቴር)….አባል ናቸዉ፡፡












