በትግራይ የወሲባዊ ጥቃት ተጎጂዎችን የሚያክሙ ባለሙያዎች ትግል

አይናቸውን የሸፈኑ ግለሰብ

ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ ወታደራዊ ግጭቶች በተካሄደባት በትግራይ ክልል ዕዳጋ ሓሙስ አንዲት ሴት ልጅ ረዘም ለቀናት ወሲባዊ ጥቃት ከተፈፀመባት በኋላ ማህጸንዋ ባእድ ነገሮች ገብቶበት ተጥላ መገኘቷ ተሰማ።

ይህች ተጠቂ ቁጥራቸው በርከት ያለ የኤርትራ ወታደሮች አካባቢው ወደሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ በመውሰድ ለቀናት እንደደፈሯት በአዲግራት ሆስፒታል የሚገኘው የህክምና ታሪኳ ያስረዳል።

በመጋቢት ወር ወደ አዲግራት ሆስፒታል ስትመጣ "ማህጸንዋ ውስጥ የነበሩ ባእድ ነገሮች ለማስወጣት ስሞክር ከአቅሜ በላይ ሆነ" የሚለው መጀመሪያ ያያት ዶክተር አታኽልቲ ስዩም ነው።

በመሆኑም ሌላ ሐኪም እንዲያያት ግድ ሆነ፤ አንድ የማህፀንና ጽንስ ሐኪም ተጠርቶም በቀዶ ጥገና እንዲወገዱ አደረገ።

ዶክተር አታኽልቲ "ይህ አሰቃቂ ክስተት መቼ ከአእምሮዬ እንደሚወጣ አላውቅም" በማለት እያለፈበት ያለውን ሥነ ልቦናዊ ጫና ያስረዳል።

እሷም የነርቭ ችግር አጋጥሟት በመቀለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የጤና ክትትል እየተደረገላት ይገኛል።

"...ብዙ ተደራራቢ ወሲባዊ ጥቃት የደረሳቸው ሴቶች ታሪክ ስሰማ ውዬ ወደ ቤት ስሄድ፤ ምን እንደምረግጥና ምን እንደምናገር አላውቅም" ትላለች በአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ስር በሚገኘው የዋንስቶፕ ሴንተር የምትሰራው ነርስ ሙሉ።

እነዚህ የህክምና ባለሙያዎች በየቀኑ የሚያስተናግዷቸው ተደፍረው የመጡ ሴቶች ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው።

የተመድ ሰብዓዊ ዕርዳታ ሃላፊ ማርክ ሎውኮክ ለፀጥታው ምክር ቤት ወሲባዊ ጥቃት በትግራዩ ግጭት እንደ ጦርነት መሳሪያ አገልግሏል ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካው አምባሳደር ዋሺንግተን "በመድፈር እና ጭካኔ በተመላባቸው ወሲባዊ ጥቃቶች ደንግጣለች" ሲሉ ተናግረው ነበር።

የደረሰባቸው ስቃይ ከብዶባቸው መፈጠራቸውን የጠሉ፣ ጥቃቱ ባሳደረባቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና ተረብሸው "ሰው አይፈልገኝም፣ በህይወት መኖር የለብኝም፣ ሞት ይሻለኛል" የሚሉ ተጠቂዎች ቁጥራቸው ቀላል አለመሆኑን የሕክምና ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

የታካሚዎቻቸው ቀልብ አረጋግተው፣ ታካሚዎቻቸው አዲስ ህይወት እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ ጥረት ማድረግ የሐኪሞቹ ኃላፊነት ከሆነ ወራቶች መቆጠር ጀመረዋል።

እነዚህ የሕክምና ባለሙያዎች በቂ የህክምና መሳሪያና መድኃኒት በሌለበት፣ የሰው ኃይል እጥረት ባለበት ሁኔታ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተደፈሩ ሴቶችና እናቶች ሲያስተናግዱ ይውላሉ።

በአዲግራት ሆስፒታል ከአንድ ዓመት በላይ ሲያገለግል የቆየው ዶክተር አታኽልቲ እስከ አሁን ድረስ ከ140 በላይ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ማከሙን ይናገራል።

ይሁን እንጂ ይህ ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ስለሚመጣ በዚያው ልክ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ጫናውን እየበረታበት እንደመጣ ያስረዳል።

"በየቀኑ የምሰማውና የማየው ጉዳይ ስለሆነ፣ በየቀኑ ራሴን ያመኛል፣ ጭንቀት አለብኝ፣ ምግብ አልበላም፣ ራስን የመጣልና በሆነ ነገር ያለመደሰት ሁኔታ ይታይብኛል" ይላል።

እንደ ዶክተር አታኽልቲ ከሆነ እስከ አሁን ድረስ ከ258 በላይ ሴቶች ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው በመግለጽ አዲግራት ሆስፒታል ለሕክምና መጥተዋል።

ዶ/ር አታኽልቲ ካስተናገዳቸው ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች መካከል በእድሜ ትንሿ 12 ዓመት ሲሆናት፣ ትልቋ እድሜ ደግሞ የ89 ዓመት አዛውንት ይገኙባቸዋል ይላል።

"አብዛኛዎቹ እናቶች ናቸው፤ የ70 ዓመት የካህናት ባለቤቶች፣ ቆራቢ እናቶች አሉ። የደረሰባቸው ሲናገሩ እንባቸው ይቀድማቸዋል። ይህን ሳይ ሁሉም ነገር ያስጠላኛል" ሲል ይናገራል።

በትግራይ ካሉ ከተሞች ሁሉ መቀለ ከተለያዩ አካባቢዎች በተሻለ የህክምና አገልግሎት የሚገኝባት ከተማ ናት።

በአይደር ሪፈራል ሆስፒታልና በመቀለ ሆስፒታል የሚታከሙ ከመቀለና ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች የመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠቂዎች ይገኛሉ።

እስከ አሁን በአይደር ሆስፒታል ወደሚገኘው የጾታዊ ጥቃት ሰለባ ማዕከል (ዋን ስቶፕ ሴንተር) ከ335 በላይ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች መምጣታቸውን የምትናገረው ነርስ ሙሉ፣ ከእነዚህ መካከል ከ140 በላይ ሴቶች በመደፈራቸው ያረገዙትን ጽንስ እንዲቋረጥ የሚፈልጉ ናቸው ትላለች።

በተጨማሪም ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የተጠቁ፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት የደረሰባቸው፣ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የማይችሉ ሆነው ሲመጡ የዚህ ማዕከል ነርስ ሙሉ፣ ቀድሞ የማግኘት ኃላፊነቱ በእሷ ጀርባ ላይ ወድቋል።

"ሰው መቅረብ አይፈልጉም፤ በደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት ራሳቸውን ከመጥላታቸው የተነሳ የአእምሮ መድኃኒት መውሰድ የጀመሩ አሉ" የምትለው ነርሷ፤ በዚህ ሁኔታ የተሳካ ሥራ መስራት ከባድ እንደሆነ ትናገራለች።

"በቀን እስከ 15 ታካሚ የምናይበት ሁኔታ አለ። በርካታ የጤና ተቋማት ስለ ተዘረፉና ስለወደሙ ፅንስ የሚያቋርጡበት አልያም መድኃኒት የሚያገኙበት ሁኔታ የለም። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሕዝቡም እኛም በጣሙን ተቸግረናል" ትላለች።

በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግችቱ ከተከሰተ በኋላ የሚያጋጥሙ ጾታዊ ጥቃቶችን በተመለከተ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል።

በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በግጭት ወቅት የሚከሰት ወሲባዊ ጥቃት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ቡድን ልዩ ተወካይ ፕራምሊያ ፓተን በትግራይ የሚስተዋለው ጾታዊ ጥቃት እንዲገታ ቀደም ሲል ጥሪ አቅርበው ነበር።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በማዕከላዊው መንግሥትና በህወሓት በሚመራው የትግራይ ክልላዊ መስተዳደር መካከል የነበሩ ፖለቲካዊ ልዩነቶች እየተካረሩ መጥተው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ላይ ወደ ወታደራዊ ግጭት መከሰቱ አይዘነጋም።

በዚህ ምክንያት በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ሱዳን ሲሰደዱ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ወደ ተለያዩ የክልሉ ከተሞች ተፈናቅለዋል።

የዓለም የምግብ ድርጅት 91 በመቶ የክልሉ ሕዝብ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሲገልጽ፤ መንግሥትና ሌሎች ድርጅቶች የተለያዩ የእርዳታ ቁሳቁሶች እያቀረቡ መሆናቸውን አስታውቋል።

ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ ኃይሎች ፈጽመዋቸዋል ከተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል ጾታዊ ጥቃቶችን በተመለከተ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው እንደተናገሩት በክልሉ ውስጥ የመብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙና ምርመራ ተደርጎ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

"በትግራይ ወሲባዊ ጥቃትና ዘረፋ እንደተፈጸመ የሚያሳዩ ሪፖርቶች አሉ። የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ የትግራይ ሴቶች የደፈረና ንብረት የዘረፈ ወታደር በሕግ ይጠየቃል" ብለዋል።

የኤርትራ መንግሥትም የሚቀርብበትን ክስ ውድቅ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት ሶፊያ ተስፋማሪያም ለድርጅትቱ የጸጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ የኤርትራ ወታደሮች አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ፈጽመዋል መባሉ "የሚያስቆጣ ብቻ ሳይሆን በሕዝባችን ባህልና ታሪክ ላይ የተሰነዘረ የከፋ ጥቃት ነው" ሲሉ ተቃውመውታል።

ሁለት ጀርባቸውን ሰጥተው የቆሙ ግለሰቦች

"ትንሽ መድሃኒት እንቁ ሆናብናለች"

የጤና ተቋማት በትግራይ ከባድ ውድመት ከደረሰባቸው ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች አንዱ ናቸው።

ከታህሳስ ወር አጋማሽ እስከ መጀመርያ የመጋቢት ወር ባለው ጊዜ ድንበር የለሹ የሐኪሞች ማኅበር በ106 የጤና ተቋማት ላይ ባካሄደው ዳሰሳ፤ 70 በመቶ የሚጠጉ ተዘርፈዋል፤ 30 በመቶ ደግሞ ወድመዋል ብሏል።

እነዚህ "ሆን ተብሎ የወደሙና የተዘረፉ" ናቸው ሲል የክልሉ ሕዝብ ጥቂት የህክምና አማራጮች ብቻ እንደቀሩት ገልጿል።

"የሽንትና ደም መርመራ ማድረግ የምንችልበት ሆነ መድኃኒት የምናገኝበት ደረጃ ላይ አይደለንም። ታካሚዎች ለተከታታይ አራት ቀናት ወረፋ ይዘው ይውላሉ። ትንሽ መድኃኒት እንቁ ሆናብናለች" የሚለው ዶክተር አታኽልቲ የባለሞያ እጥረት ባለበት ሁኔታ የጾታዊ ጥቃት ታካሚዎች ቁጥር መብዛቱ ሥራውን እንዳከበደው ይናገራል።

ተጎጂዎቹ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ፣ በጦርነቱ ምክንያት አባት ወይም ወንድማቸው የተገደሉባቸው ሲሆኑ፣ ሌሎች የቆዳና የሥነ አእምሮ ችግሮች ይታይባቸዋል።

"አብዛኛውን ጊዜ ጠዋት ገብተን ምግብ ሳንበላ የምናድርበት ሁኔታ ስላለ ውሎ አዳሬ ሆስፒታል ውስጥ ሆኗል። ከሩቅ አካባቢ ስለሚመጡ ትተናቸው መሄድ ይከብደናል፤ ደግሞም ያለቅሳሉ። ወደ ቤት ስገባ ሁሉም ነገር ስለሚረብሸኝ አልተኛም" ይላል።

የመቀለ ዋን ስቶፕ ሴንተር ማኅበራዊ ሠራጠኛ፣ ዐቃቢ ሕግ፣ ሐኪምና ፖሊስ ያለው የተደራጀ አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል በመሆኑ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑት ሴቶች ከመጠቋቆም ገለል ብለው እንዲታከሙ ረድቷቸዋል።

ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ሴቶች የኅብረሰተቡ አመለካከትና ባህል ጫና ስለሚያሳድርባቸው ወደ ህክምና ለመምጣት አይደፍሩም፤ የደረሰባቸውን ጉዳት የሚናገሩትም ጥቂት ናቸው።

ነርስ ሙሉ ማዕከሉ ከአቅሙ በላይ የሆነ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ትናገራለች።

"በህይወቴ ሙሉ እንደዚህ ሥነ ልቦናዬን የገደለው አጋጣሚ የለም። ድንጋጤውን ቤታችን ድረስ ይዘነው እንሄዳለን፣ ምግብ አይበላልንም። ሰው ስለሚበዛም ሰዓት እላፊውን አናከብርም። ህይወትን ሽጦ ነው እየተሰራ ያለው" ብላለች።

በተጨማሪም "ወደ ቤት ስሄድ እያንዳንዱ ሳክማቸው የዋልኳቸውን ሴቶች ስም፣ የሰውነታቸው ሁኔታና ስቃያቸው በፍጹም አይረሳኝም። ቀንና ሌሊት ከእኔ ጋር ናቸው። ስቃያቸው የእነሱ ቢብስም ሁላችንንም የጎዳ ሆኗል" በማለት ቤተሰቦችዋ ፊት ስለ ሥራዋ እንደማታወራ ገልጻለች።

"ድሮ በትንሽ ነገር እደሰት የነበርኩ ሰው አሁን ቤተሰቦቼም ሆነ ጓደኞቼን ሳገኝ እንኳ አልደሰትም" የሚለው ዶክተር አታኽልቲ በበኩሉ "ሁሌም ለመጪው ትውልድ ምንድን ነው የምንነግረው? በሚል እጨነቃለሁ" ይላል።

"ከዚህ በፊት ሻይ እየጠጣሁ ስለ አንድ የዳነልኝ ታካሚዬ ሳወራ እውል ነበር፤ አሁን ግን ስደክም ባድርም ለሰው አላወራውም። የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነው የሚሰማኝ። በዚህ ወቅት አገልግሎት መስጠት ስላለብኝ እንጂ፤ ዘወትር ዛሬም ላያቸው ነው? እያልኩ እየተጨነቅኩ ነው የምሄደው" በማለት ያለበት ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራል።

"ሁሉም ህልም ይመስለኛል"

የህክምና ባለሞያዎች ስለ ግል ስሜታቸውና ድካማቸው ለማሰብም ሆነ ለማዘን ብዙም ጊዜ የላቸውም።

ነርስ ሙሉ እንደምትለው "አሁን እንደልብ ተናግሮ መሄድም አይቻልም። ብንናገርም የሚያግዘን የለም፤ እየሆነ ያለውን ነገር ከሆነ በኋላ ላግዝህ የሚለው ደግሞ ስቃይን ነው የሚጨምረው" ትላለች።

የአዲግራት ሆስፒታል ዶክተር አታኽልቲ በበኩሉ የመብራትና ስልክ አገልግሎት በተደጋጋሚ እንደሚቋረጥና ከሁሉም በላይ ውሃ አለመኖሩ ትልቅ ችግር እንደሆነባቸው ያነሳል።

"ሕዝቤና አገሬ ነው በሚል ወኔ ነው የምንሰራው እንጂ፤ ሰርተን እጃችን የምንታጠብበት ውሃ እንኳ የለም። መብራት ስለሚጠፋ ዳቦና እንጀራ የማይገኝበት ቀን ብዙ ነው። ለስላሳ ጠጥተን የምንሰራበት ሁኔታ ነው ያለው" ሲል ያስረዳል።

ከሁሉም በላይ ግን "ህይወታችን ሁሉ ህልም ሆኗል። ትንሽ መድኃኒት ማግኘት፣ መብራትና ሌሎች ነገሮች እንደልብ ማግኘት ህልም ነው" ብሏል።

ከ10 ዓመታት በላይ በነርስነት ያገለገለችው ሲስተር ሙሉ በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታ አንድ ተስፋ የሚሰጣት ነገር አለ።

እሱም "ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴቶች እዚህ በመምጣት አእምሯቸውን ሰቅዞ ይዞት የነበረው ችግር በትንሽ ቃላት ቀለል ሲልልቸው ደስ ይለኛል። ቀልባቸውን ስተው መጥተው አሁን በእግራቸው ሲሄዱ ሳይ እደሰታለሁ" ትላለች።

ይህች መቅለል ግን ጊዜያዊ ናት። ሐኪሞቹ ትንሽ ቀለል ያላቸው ሸክም መልሶ የሚቆለልባቸው እንደገና አዲስ የጥቃት ሰለባዎች ሲመጡ ወደነበረው የጭንቀት አዙሪት መልሰው እንደሚገቡ ይናገራሉ።