ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል ስለተባለው ሠራዊቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ምላሽ ሰጠች

የፎቶው ባለመብት, @stesfamariam
ኤርትራ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብቷል የተባለውን ሠራዊቷን በተመለከተ በይፋ ምላሽ ሰጠች።
በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ አምባሳደርና ቋሚ ተወካይ የሆኑት ሶፊያ ተስፋማሪያም ሐሙስ እለት የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ላይ በተነሱ ጉዳዮች ላይ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ነው ስለኤርትራ ወታደሮች የገለጹት።
ትግራይ ውስጥ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱን ተከትሎ የኤርትራ ኃይሎች ድንበር ተሻግረው ወደ ትግራይ ክልል ገብተዋል የሚሉ ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ሲወጡ የቆዩ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የኤርትራ መንግሥት ለወራት ሲያስተባብሉ መቆየታቸው ይታወሳል።
በመጨረሻም ባለፈው መጋቢት ወር የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት የህወሓት ኃይሎች በሰነዘሩት የጠብ አጫሪነት ጥቃት ተገፍቶ የኤርትራ ሠራዊት ድንበር አልፎ መግባቱን ገልጸው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ወደ አሥመራ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በመነጋገር የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አሳውቀዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ በኩል የተገለጸውን የኤርትራ ወታደሮች መኖር ያላስተባበለ ከመሆኑም በላይ አንድም ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው ስለመግባታቸው ያለው ነገር አልነበረም።
አሁን ግን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ባካሄደው ውይይት ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ባለስልጣን የሆኑት ማርክ ሎውኮክ እና በምክር ቤቱ የአሜሪካ መልዕክተኛ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ላደረጉት ንግግር ኤርትራ በሰጠችው የደብዳቤ ምላሽ ላይ ስለወታደሮቿ ተገልጿል።
አምባሳደር ሶፊያ ተስፋማሪያም ለጸጥታው ጥባቃ ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ ላይ በዚያ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ገልጸዋል።
በዚህም ወደ ኢትዮጵያ የኤርትራ ሠራዊትን በሚመለከት "አንዣቦ የነበረው ስጋት በአብዛኛው በመወገዱ ኤርትራና ኢትዮጵያ የኤርትራ ኃይሎችን ለማስወጣትና የኢትዮጵያ ሠራዊት በድንበር ላይ እንዲሰማራ ለማድረግ በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው አማካይነት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል" በማለት አረጋግጠዋል።
አምባሳደሯ ለምክር ቤቱ በጻፉት ደብዳቤ ላይ የኤርትራ መንግሥት በዝግ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የአሜሪካዋ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በሰነዘሩት "ተገቢ ያልሆነ" መግለጫ ላይ ተቃውሞ እንዳለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ዘርፍም ላይ ቅሬታቸውን በደብዳቤው ላይ ተቋሙ "በተደጋጋሚ ከተሰጠው ድርሻ ባሻገር በመሄድ ተቀባይነት የሌለው ገንቢ ያልሆነ ተግባራት ውስጥ ገብቷል" ሲሉ ከሰዋል።
በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የአሜሪካ መልዕክተኛ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድም በዚሁ ጊዜ የአስገድዶ መድፈርና ጾታዊ ጥቃቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶችን ተከትሎ የኤርትራ ወታደሮች "በአስቸኳይ" ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ጠይቀው ነበር።
አምባሳደር ሶፊያ በደብዳቤያቸው ላይ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በግጭቱ ወቅት "ወሲባዊ ጥቃትና ረሃብ እንደ መሳሪያ ጥቅም ላይ ውሏል" በሚል የቀረበውን ክስ ሐሰተኛ ሲሉ በደብዳቤያቸው የተቃወሙት ሲሆን፤ የኤርትራ ወታደሮች አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ፈጽመዋል መባሉ "የሚያስቆጣ ብቻ ሳይሆን በሕዝባችን ባህልና ታሪክ ላይ የተሰነዘረ የከፋ ጥቃት ነው" ሲሉ ተቃውመውታል።
ህወሓት በፈጸመው ጥፋት በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ንጹሃን በምንም መልኩ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደማይገባ የገለጸው የኤርትራዋ አምባሳደር ደብዳቤ የሰብአዊ እርዳታን ማቅረብ የወቅቱ አንገብጋቢ ሥራ መሆን ይገባዋል ብሏል።
በትግራይ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ሐሙስ ዕለት ለአምስተኛ ጊዜ በተወያየው የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በግጭት ከተጎዳው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል "የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያመለክት ነገር የተባበሩት መንግሥታት ተቋማትም ሆኑ ሌሎች አብረውት የሚሰሩ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች እንዳላዩ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ባለስልጣን የሆኑት ማርክ ሎውኮክ ተናግረው ነበር።
ትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ድንበር ተሻግረው ገብተዋል የተባሉት የኤርትራ ወታደሮች የተለያዩ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን በተመለከተ ክስ ሲቀርብባቸው ቆይተዋል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ግን ለወራት ወታደሮቹ ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን በተመለከተ ይወጡ የነበሩትን ሪፖርቶች ሲያስተባብሉ የቆዩ ሲሆን፤ በመጨረሻም በመጋቢት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች መኖራቸውን ለአገሪቱ ፓርላማ ተናግረው ነበር።
ከቀናት በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከተነጋገሩ በኋላ ወታደሮቹ ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች ለቀው በመውጣት የኢትዮጵያ ሠራዊት ስፍራዎቹን እንዲቆጣጠር ከስምምነት መድረሳቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ አምስት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን በዚህ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ላይ ለመምከርና መግለጫ ለመውጣት ምክር ቤቱ የሐሙስ ዕለቱን ጨምሮ ለአምስት ጊዜ ተሰብስቦ ተወያይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ማርክ ሎውኮክ ግጭቱ እንዲቆምና የበለጠ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር እንዲመቻች ጥያቄ አቅርበዋል።
ትግራይ ውስጥ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ጦር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር።
በትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አሃዙ በበርካታ ሺዎች ሊሆን እንደሚችል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይናገራሉ።
ከዚህ ባሻገርም በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች ግድያዎች፣ ጾታዊ ጥቃቶች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ዘረፋና የንብረት ውድመቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ አመልክተዋል።
በተጨማሪም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዳለው በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
















