አሜሪካ የአል ቃኢዳን መሪ ካቡል ውስጥ ገደለች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ የአል ቃኢዳውን መሪ አይማን አል-ዛዋሂሪን በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ውስጥ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት መግደሏን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስታወቁ።
የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሲአይኤ ባለፈው ዕሁድ ካቡል ውስጥ ባካሄደው የፀረ-ሽብር ዘመቻ ላይ ነው ዛዋሂሪን መግደል የቻለው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ባይደን አይማን አል-ዛዋሂሪ “በአሜሪካ ዜጎች ላይ ግድያ እና ጥቃትን የቀረጸ ሰው ነው’’ ብለዋል።
አክለውም “አሁን ፍትህ ተሰጥቷል ፤ ይህ የአሸባሪ ቡድን መሪ ከዚህ በኋላ በሕይወት የለም” ሲሉም ግድያውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ዛዋሃሪ ከቀድሞው የአል-ቃኢዳ መሪ ቢን ላደን ጋር በመሆን ከ20 ዓመታት በፊት የተፈጸመውን የ9/11 ጥቃትን የመራ ሲሆን፣ አሜሪካ ለረጅም ዓመታት ስታፈላልገው የቆየችው የሽብር ቡድኑ መሪ ነው።
አይማን አል-ዛዋሂሪ የኦሳማ ቢን-ላደን ሕልፈትን ተከትሎም አል-ቃኢዳን ሲመራ ቆይቷል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ዛዋሂሪ በአንድ በጥብቅ በሚጠበቅ ቤት በረንዳ ላይ ተቀምጦ ባለበት ወቅት ነው የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ሁለት ሚሳኤሎችን ተኩሶ የገደለው።
እንዲሁም በቤቱ ውስጥ የነበሩ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው እና በጥቃቱ ዛዋሂሪ ብቻ ተነጥሎ መገደሉንም አክለው ተናግረዋል።
ባይደን በ71 ዓመቱ የአል ቃኢዳ መሪ ላይ እርምጃውን ለመውሰድ ለወራት ዕቅድ ከወጣ በኋላ “የተመጠነ እና ትክክለኛውን ኢላማ የመታ ጥቃት” እንዲሰነዘር የመጨረሻውን የይለፍ ፍቃድ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
የሽብር ቡድን መሪው ግድያም እ.ኤ.አ. በ2001 በተፈጸመው ጥቃት 3,000 የሚጠጉ ወዳጅ፣ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አሜሪካዊያን ለሐዘናቸው መልስ የሚሆን የመጨረሻውን መደምደሚያ የሚሰጥ እርምጃ ነውም ሲሉ አክለዋል።
“የቱንም ያህል ጊዜ ይፍጅ፣ የትም ይደበቁ፣ ለሕዝባችን ስጋት የሆነ አካል ካለ አሜሪካ ታገኛቸዋለች፣ ቀጥሎም ታስወግዳቸዋለች” ያሉት ባይደን አክለውም “አገራችንን እና ሕዝባችንን ከመከላከል ወደ ኋላ አንልም” ሲሉም አክለዋል።
ባይደን ዛዋሂሪ እ.ኤ.አ በጥቅምት 2000 በኤደን የአሜሪካ የባሕር ኃይል ግዙፍ የጦር መርከብ ላይ በተሰነዘረ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 17 የአሜሪካ መርከበኞችን የገደለውን ጥቃት መርቷል ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም ለ223 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት የሆኑት በ1998 በኬንያ እና በታንዛኒያ በአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶችንም በማስተባበር ዛዋሂሪ ኃላፊነት እንዳለበትም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን አፍጋኒስታን ከእንግዲህ የአሸባሪዎች መሸሸጊያ አትሆንም ሲሉም አጥብቀው ተናግረዋል።
የታሊባን ቃል አቀባይ የአሜሪካን ዘመቻ ዓለም አቀፍ መርሆችን የጣሰ ነው ሲሉ ገልፀውታል።
አክለውም “እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ላለፉት 20 ዓመታት ያልተሳኩ ሙከራዎችን መደጋገም ናቸው። ድርጊቱም የአሜሪካን፣ የአፍጋኒስታንን ብሎም የቀጠናውን ጥቅም ጥቅም የሚፃረር ነው’’ ብለዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው በአል ዛዋሂሪ ላይ የተካሄደው ዘመቻ ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ብለዋል።












