በወንዶች የበላይነት በተያዘው ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ የሚታገሉት የኬንያ ሴቶች

ወ/ሮ ጌዲያ አደም ማሞ 34 ዓመቷ ሲሆን የሁለት ልጆች እናት ነች።
ሰዎች በጎሳ ተከፋፍለው ግድያ ሲበረታ እሷም የገፈቱ ቀማሽ ስለሆነች ይህንን ለማስተካከል የበኩሏን ለማድረግ የምትኖርበት ግዛት (ካውንቲ) አስተዳዳሪ ለመሆን ፈለገች።
ለዚህ የኃላፊነት ቦታ ለመወዳደር የፈለገችው ግን የፀጥታ ችግር ስላለ ብቻ አይደለም።
“የፓርላማ አባላት በሙሉ፣ ሴናተሮች አስተዳዳሪው እንዲሁም ምክትሉ ወንዶች ናቸው” ስትል ቅሬታዋን ታሰማለች።
ጌዲያ አደም ነገር ግን ፈተና ገጠማት። “ፖለቲካ ውስጥ ስለሌለሁ አያውቁኝም” ስትል አስተዳዳሪ የመሆን ህልሟ በዚህ የተነሳ ፈተና ውስጥ እንደሚወድቅ ትናገራለች።
ከዚህ የበለጠ ችግር ግን ነበር። አስተዳዳሪ ለመሆን ያሰበችው ህልሟን የጎሳዋ አባላት ጠየቋት። የእርሷ ጎሳ ሳኩዬ እና የባለቤቷ ጎሳ ሬንዲላ፣ ይህንን የመወዳዳር ሃሳቧን እንድትተው ጠየቋት።
ያቀረቡት ምክንያት ደግሞ ሌላ ድምጽ የምንሰጠው ሰው ስላለ ድጋፋችንን ልታጪ ትችያለሽ በማለት “ሌላ ነገር ሞክሪ” አሏት።
በዘንድሮው የኬንያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት የሚወዳደሩ ሴቶች ቁጥር ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ከነበረው ይሻላል።
ነገር ግን አሁንም ትንሽ ነው።
ከኬንያ የምርጫ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በ2017 ከተወዳዳሪዎች ውስጥ 7 በመቶው ብቻ ሴቶች ነበሩ። በዚህ ዓመት ግን ይህ ቁጥር ወደ 11 በመቶ ከፍ ብሏል።
ነገር ግን ብዙዎቹ በባህል፣ በልማድ እንዲሁም በእምነት ያሰቡትን እንዳያሳኩ እክል ይገጥማቸዋል።

‘ሴቶችን ያንኳስሳሉ’
“አርብቶ አደሮች ብዙውን ጊዜ ወንዶች በሚወዳደሩበት ቦታ ላይ፣ ሴቶችን ዝቅ አድርገው ነው የሚያዩት። የአገር ሽማግሌዎች ከውድድር ካስወጡኝ በኋላ ዝም ብዬ መቀመጥ አልፈለግኩም። ጠንካራ ሰው የሚሰራውን ሥራ ሴትም መስራት ትችላለች” በማለት ሌላ ውድድር ውስጥ ገባች።
ጌዲያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰነው የሰሜን ኬንያ፣ መርሳቤት ካውንቲ፣ የግዛቲቱ የሴቶች ተወካይ ለመሆን ራሷን በዕጩነት አቅርባለች።
ለዚህ የኃላፊነት ቦታ የሚወዳደሩት ሴቶች ብቻ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ከጌዲያ በተጨማሪ ስድስት ሴቶች ለዚህ የኃላፊነት ቦታ እየተወዳደሩ ይገኛሉ።
ከጌዲያ ጋር ከሚፎካከሩት ሴቶች መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ፋጡማ ሐዋ ረሪ ናቸው።
ራሳቸውን ዕጩ ለማድረግ ብለው ሥራ ማቆማቸውንም ይናገራሉ።
ኬንያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ውክልና ለመጨመር በሚል ለየግዛቶቿ የሴቶች ተወካይነት ስፍራን ክፍት አድርጋለች።
ወ/ሮ ፋጡማ ለ15 ዓመታት በመምህርነት ሙያ ላይ አገልግለዋል።
ወ/ሮ ፋጡማ እንደ ወ/ሮ ጌዲያ በፖለቲካ ፓርቲ ዕጩነት ሳይሆን በግላቸው ነው የሚወዳደሩት።
“አንድ ሴት ልጅ በረሃብ ራሷን ስታ አየሁኝ። ይህንን የታዘብኩት በሶሎሎ አካባቢ ነው። የዚያን ቀን ባየሁት በጣም ተከፋሁኝ” ይህ ፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ከሆናቸው ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።

‘ይጠራጠሩናል’
በሰሜን ኬንያ፣ ራሳቸውን ለዕጩነት አቅርበው እየተወዳደሩ ካሉ ዕጩዎች መካከል ወ/ሮ ሐሊማ ቀሊፍ ኩሴ ሌላኛዋ ሴት ናቸው።
በአሁኑ ሰዓት በመርሳቤት ካውንቲ ምክር ቤት አባል ለመሆን እየተወዳደሩ ይገኛሉ።
እኚህ ተወዳዳሪ እንደሚሉት፣ በሚወዳደሩበት የምርጫ አካባቢ፣ ሴት እርሳቸው ብቻ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ስምንቱ ወንዶች ናቸው።
“በዚህ የምርጫ አካባቢ በብዛት የሚወዳደሩት ወንዶች ናቸው። እኔ አነዚህን ወንዶች ተፎካክሬ የምርጫ ቅስቀሳ አድርጌ፣ አሸንፋቸዋለሁ ብዬ እናገራለሁ። መጀመሪያ አካባቢ ይጠራጠሩ ነበር” በማለት የአካባቢው ማኅበረሰብ የሴቶች አመራር ላይ ጥርጣሬ እንዳለው ይገልጻሉ።
“እናንተ ሴት ልጅ ካላችሁ እባካችሁ ድምጽ እንዳትከለክሉኝ እያልኩኝ ሆዳቸውን እበላለሁ” እንደ እርሳቸው ከሆኑ የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ የተወሰነ ተለውጧል።
ወ/ሮ ሐሊማ 18 ዓመት በመምህርነት ካገለገሉ በኋላ ነው ወደ ፖለቲካ ሕይወት የገቡት።
ምክንያታቸውንም ሲገልፁ፣ “እኔ ለውጥ እፈልጋለሁ፤ ፖለቲካን በጣም እወዳለሁ” ይላሉ።

‘ሰላም! ሰላም!!’
በሰሜን ኬንያ በመርሳቤት ካውንቲ በማኅበረሰቡ መካከል ግጭት ስለበዛ ከግንቦት ወር ጀምሮ የማዕከላዊ መንግሥት ሰዓት እላፊ አውጇል።
የማኅበረሰቡም ትልቁ ችግር የሰላም እጦት ነው።
ወ/ሮ ፋጡማ “ብዙ ሴቶች ባሎቻቸው ተገድሎባቸዋል። እንዲሁም ብዙ ልጆች አባታቸውን አጥተዋል” በማለት እንደሌሎች ተወዳዳሪዎች ትልቁ አጀንዳቸው የሰላም ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደምም ትምህርት ቤት በነበሩበት ወቅት የሰላም ሙዚቃ በማዘጋጀት ተማሪዎች እንዲዘምሩ ያደርጉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ወ/ሮ ጌዲያ በበኩላቸው በአካባቢው በተደጋጋሚ በግጭት ውስጥ ከሚሳተፉት ጎሳዎች ውጪ መሆናቸው በመጥቀስ፣ ትልቁ አጀንዳቸው አድርገው ስለ ሰላም ቢሰሩ ተቀባይነት እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል።
ወ/ሮ ሐሊማ የመጡት በተደጋጋሚ ግጭት ከሚያጠቃው አካባቢ መሆኑን በማንሳት የሰላም ጉዳይን “እንደ ሴትነቴ አንድ ነገር በማድረግ እወጣዋለሁ” ሲሉ ይደመጣሉ።

‘ለመወዳደር ባለቤቴ እና ማኅበረሰቡ መፍቀድ ነበረባቸው’
ኬንያ ካሏት ግዛቶች መካከል 14ቱ የተገለለ ማኅበረሰብ የሚኖርባቸው እንደሆነ የ2014 የዓለም ባንክ ሪፖርት ይጠቅሳል።
በእነዚህ ማኅበረሰቦች ውስጥ የወንድ የበላይነት በመግዘፉ እና ሴቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ላይ እንዳይወስኑ መገደባቸው በአመራር ውስጥ ያላቸውን ሚና ጎድቶታል።
ወ/ሮ ኬሊ ማሪና የማሳይ ጎሳ አባል ናቸው።
በአሁኑ ሰዓት የምሥራቅ ካጂያዶ የምክር ቤት አባል ለመሆን በዕጩነት ቀርበዋል። አባወራዎች እና ማኅበረሰቡ ስምምነት ላይ ካልደረሱ ሴቶች የፖለቲካ ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ አይፈቅዱም።
“ትልቁ ችግር ሴቶች እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ካነሱ፣ ባለቤቷን እና ልጇን ትታ እንደሄደች ይታሰባል። ሴቶች ቤት ውስጥ ብቻ መሆን እንዳለባቸው።”
የተገፉ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች መዳረሻቸውን ለማሳካት ሌሎች የተጓዙበት ርቀት ድረስ መሄድ ይቻላለ ብለው ያምናሉ።












