ዕጸ ፋርስ እና የእባብ መርዝ የወጪ ንግድን አቀላጥፋለሁ የሚሉት የኬንያ ዕጩ ፕሬዚዳንት

ጆርጅ ዋጃኮያህ

የፎቶው ባለመብት, George Waackoyah

በልጅነታቸው የኬንያ ጎዳና ተዳዳሪ በኋላም በአንድ ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም የመቃብር ቆፋሪ የነበሩት የአሁኑ የኬንያ ዕጩ ፕሬዝዳንት፣ ጆርጅ ዋጃኮያህ ለአገራቸ ዕጸ ፋርስ፣ የእባብ መርዝ እና የጅብ ዘር ፍሬን የወጭ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ አቀላጥፋለሁ እያሉ ነው።

ብዙዎች የዕቅዳቸውን ተግባራዊነት ቢጠራጠሩትም የኬንያው ዕጩ ፕሬዚዳንት የምርጫ ቅስቀሳ በርካቶችን አስደምሟል።

የ63 ዓመቱ ፕሮፌሰር እንዲሁም 17 ዲግሪ እንዳላቸው የሚናገሩት ዋጃኮያህ በመጪው ነሐሴ በሚካሄደው የኬንያ ምርጫ ከሚወዳደሩት አራት ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች መካከል እንደ እንግዳና ድንቅ ነገር በመታየት ቀልብን ስበዋል።

የብዙዎችን ትኩረት ቢስቡም በምርጫው ያሸንፉ ይሆን? የሚለው ላይ የተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት ያንን አያሳይም።

ከቀናት በፊት በወጣው የሕዝብ አስተያየት መሰረት 'ሩትስ' የተሰኘ ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩት ዋጃኮያህ፣ 4 በመቶ ድምፅ ብቻ እንደሚያገኙና በደረጃም ደካማ በሚባል ሁኔታ ሦስተኛ ላይ ነው የተቀመጡት።

ነገር ግን የዘርፉ ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ዕጩ ተወዳዳሪ ለሆኑ ግለሰብ ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው ይላሉ።

በተለይም ግንባር ቀደም ተፎካካሪዎቹ 43 በመቶ የተሰጣቸው የተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ እና 39 በመቶ የተተነበየላቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ምንም አይነት ድምፅን ማጣት ባይፈልጉም ዋጃኮያህ የተወሰነውን መውሰድ እንደሚችሉ ተገምቷል።

“ዋጃኮያህ ከዚህ ቀደም በርካቶች ሊስቁበት የሚችሉበትን ሃሳቦች አንስቶ እየሞገተ ነው ቅስቀሳ እያደረገ ያለው። ነገር ግን በከተማም ሆነ በገጠር የተናደዱ፣ ምጣኔ ሀብቱ ያጎሳቆላቸው ወጣቶችን ቀልብ መግዛት ችሏል። በተለያየ ብሔር፣ እምነትና ፓርቲ አባላት ወጣቶችም እየተሰማ ነው” በማለት በኬንያ ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዋና አምደኛ የሆነው ማቻሪያ ጋይቶ ጽፏል።

በምርጫ ቅስቀሳ ጎዳናዎች ላይ በሚወጡበት ወቅት ሙሉ ሱፍ ኮትና ሱሪ ከማድረግ ይልቅ ቲሸርት፣ ኮፍያ፣ ስካርፍ፣ ጂንስ፣ ቱታ በማድረግ ነው። በዚህም በአገሪቱ የሰፈነው የሚወቅሱት እና የሚጠየፉት መጠነ ሰፊ ሙስና አካል አለመሆናቸውን ያሳያሉ።

በተጨማሪም ዕጸ ፋርስ እንደሚያጨስ በማስመሰል በጣቶቻቸው ምልክት ያሳያሉ፤ በሬጌ ዘፈኖችም በሚጨፍሩበት ወቅት የተሰበሰበው ሕዝብም በደስታ ይዘላል።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ የፕሬዝዳንቱን መንበር ካሸነፉ የኬንያ ሁለቱን ትላልቅ ችግሮች፣ ሥራ አጥነትን ለመፍታት እና ብሔራዊ ዕዳዋን ለማቃለል፣ ለኢንዱስትሪ እንዲሁም ለህክምና አገልግሎት የሚውል የዕጸ ፋርስ ግብርና እና ምርቱን የሚቆጣጠር ሕግ እንደሚያወጡ ተናግረዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ይህ እርምጃ ኬንያን በዓመት ከዘጠኝ ትሪሊዮን ሽልንግ በላይ ወይም 76 ቢሊዮን ዶላር ያስገኝላታል፣ በዚህም መንግሥት እንደገና “አንድ ሳንቲም መበደር የለበትም" ይላሉ።

“የምዕራባውያን አገሮች ዕጸ ፋርስን (ማሪዋና) ሕጋዊ አድርገውታል። እኛስ ለምንድን ነው ሕጋዊ የማናደርገው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ጆርጅ ዋጃኮያህ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት

የፎቶው ባለመብት, George Waackoyah

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምንም እንኳን የሚሏቸውን ጉዳዮች በጥናት ባያስደግፉም ዕጸ ፋርስ (ማሪዋና) ለኢንዱስትሪ እንዲሁም ለመድኃኒትነት ለመጠቀም ሕጋዊ ማድረግ የምርጫ ቅስቀሳቸው ዋነኛ ማጠንጠኛ ነው።

የአፍሪካ ቼክ ድረ ገፅ ዕቅዶቻቸውን አሳሳች ናቸው ሲል ገልጾታል።

ሆኖም በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ መነጋገሪያ መሆናቸው ቀጥሏል፣ እንዲሁም በሥራ አጥነት ክፉኛ የተጎዱ የአገሪቱ ወጣቶችን ደስ አሰኝቷል።

የፕሮፌሰር ዋጃኮያህ ሃሳብ የሚሳካ ከሆነ ኬንያን ዓለም አቀፍ የዕጸ ፋርስ (ማሪዋና) ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሞከሩ ካሉት የአፍሪካ አገራት ከሌሶቶ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከዛምቢያ እና ከዚምባብዌ ጋር ያሰልፋታል።

የዕጸ ፋርስ (ማሪዋና) በአንዳንድ ግምቶች መሰረት በአውሮፓውያኑ 2028፣ 70 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ ማሪዋና አጭሰው እንደማያውቁ ቢናገሩም፣ ነገር ግን ኬንያ ዕጹን ሕጋዊ ካደረገችው ደስታቸውን ለመግለፅ ማሪዋና የሚያጨሱ የመጀመሪያው ሰው እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

“ዕጸ ፋርስ (ማሪዋና) ሕጋዊ ከሆነ፣ ተቆጣጣሪ አካላትም የሚፈቅዱ ከሆነ ማጨሱ ምንም ችግር የለውም” ይላሉ።

የፕሮፌሰር ዋጃኮያህ አስተያየት በኬንያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውግዘት ደርሶበታል። ቤተ ክርስቲያኗ ማሪዋና ሕጋዊ ከሆነ ወጣቶች የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚነታቸው ይባባሳል ስትል ወቅሳለች።

“ቤተሰቦች የአደንዛዥ ዕጽ ስጋት ተደቅኖባዋል። ይህም ወደ መለያየት፣ ሁከት አልፎ አልፎም ለሞት ይዳርጋል” ሲሉ ጳጳስ ጄምስ ማሪያ ዋይናና አስጠንቅቀዋል።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ በተጨማሪም በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መንግሥት ለቻይና ኩባንያዎች የተሰጡ ውሎችን በሙሉ እንደገና እንደሚገመግሙም ቃል ገብተዋል።

ኬንያ ካለባት የውጭቻ ዕዳ 21 በመቶውን ከቻይና የተወሰደ ሲሆን ይህም ብሔራዊ ቅሬታን አስከትሏል። በተለይም በአብዛኛው እንደ መንገድ እና ባቡር ያሉ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት አገራቱ የገቧቸው ውሎች ሲሆኑ፣ ለሕዝብ ይፋ አለማሆናቸው የዕጩው ፕሬዝዳንት የሚያነሱት ጥያቄ ነው ነው።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ የእባብ እርባታን እንደ ሌላው የኬንያ ምጣኔ ሀብት ዋና ምሰሶ አድርገው ይመለከቱታል።

እባብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ከወርቅ የበለጠ ውድ ነው” የሚሉትን የእባብ መርዝ፣ ለመድኃኒትነት የሚውል ፀረ-የእባብ መርዝ ለማምረት እንዲሁም የእባብ ሥጋን ደግሞ እንደ ጣፋጭ ምግብ ለሚቆጥሩት እንደ ቻይና ላሉ አገራት እንደሚላክ ይናገራሉ።

“ምጣኔ ሀብቱን በተረጋጋ ሁኔታ ለማስቀጠል በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊኖረን ይችላል” ይላሉ ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ።

በተጨማሪም በቻይና ለመድኃኒትነት የሚያገለግለውን የጅብ የዘር ፍሬን ኬንያ ወደ ውጭ መላክ አለባት በማለት ከማሪዋና የበለጠ ገቢ እንደሚያስገኝ ያስረዳሉ።

ይህ ንግግራቸው ከዱር እንስሳት ጥበቃ ቡድኖች እና ከኬንያ የእንስሳት ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር በኩል ቁጣን አስከትሏል።

“የጅብ ዘር ፍሬዎች እና እባቦች ንግድ የተከለከለ እና ለዱር ዝርያዎች ህልውና ስጋት ነው” ሲል የእንስሳት ማኅበር በመግለጫው አስታውቋል።

የዕጩው ፕሬዝዳንት ዕቅድ “ለሌላ ወረርሽኝ ግብዓት ነው” ምክንያቱም ቫይረሶች፣ ባክቴሪያዎች እና ጥገኛ ተህዋሲያን ከጅብ እና ከእባቦች ወደ ሰው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲዛመቱ ሊያደርግ ይችላል ብሏል መግለጫው።

ጆርጅ ዋጃኮያህ

የፎቶው ባለመብት, George Waackoyah

ምንም እንኳን ተቺዎች ተወዳጅነትን ፍለጋ ነው በሚል የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸውን ቢያወግዙትም፣ የፕሮፌሰር ዋጃኮያህ ደጋፊዎችና ወዳጆች ፈታኝ የሚባል የሕይወት ችግሮችን ድል በመንሳት ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር በመነሳታቸው ያደንቋቸዋል።

ፕሮፌሰሩ ትውልዳቸው በምዕራብ ኬንያ ገጠር ሲሆን፣ ወላጆቻቸው መፋታታቸውን ተከትሎ ወደ ዋና ከተማዋ ናይሮቢ ጎዳናዎች ላይ ወጡ።

የሃሬ ክሪሽና ቤተ ምኩራብ አገልጋዮች ቤት የተቸገሩና የሚበሉት የሌላቸውን እየመገቡ በነበረበትም ወቅት ነው ታዳጊውን ያገኙት። 

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ በቤተ ምኩራቡም መኖር ጀመሩ በኋላም የሃሬ ክሪሽና ካህን ሆኑ።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ድጋፍ ተደረገላቸው። ከተመረቁ በኋላም የኬንያ ፖሊስን ተቀላቀሉ። በደረጃም ከፍ በማለት የደኅንነትና የስለላ ክፍሉን ተቀላቀሉ።

ምንም እንኳን ለዝርዝር መረጃው ግልፅ ባይሆኑም ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ በአውሮፓውያኑ 1990 በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮበርት ኦኮ ግድያ ዙሪያ ምስጢራዊ መረጃ ካገኙ በኋላ ችግር እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ እንደታሰሩ እና እንደተሰቃዩ የተናገሩ ሲሆን፣ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ናይሮቢ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እርዳታ ከኬንያ መሰደዳቸውን አስረድተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2010 የፓርላማ አጣሪ ኮሚቴ ባደረገው ምርመራ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተገደሉት በፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ አንደኛው መኖሪያ ቤት መሆኑን ይፋ እስካደረገበት ድረስ የባለሥልጣኑ ግድያ ለሕዝብ ምስጢር ሆኖ ቆይቷል።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ ኬንያን ጥለው ከወጡ በኋላ ወደ እንግሊዝ አመሩ። እዚያም ዝቅተኛ የሚባሉ ሥራዎችን እየሰሩ በለንደኑ ሶአስ ዩኒቨርሲቲ፣ በዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ እና በዎልቨርሃምፕተን ዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። 

በዎልቨርሃምፕተን ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ የጥበቃ ሠራተኛ፣ የመቃብር ቆፋሪ እና የሬሳ አጥቢ ሆነው ሰርተዋል።

እነዚህ ሥራዎች “ትሁት እንዳደረጓቸውና ዕይታቸውንም እንዳሰፋላቸው” ለዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ተናግረዋል።

በወቅቱም ለትምህርት እና ለሥራ የሚሆናቸውን ጊዜ አመጣጥኖ መሄድ ፈታኝ ነበር ይላሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም ሳሉ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለውጥ ለማምጣት በፖለቲካ ዘመቻዎች ውስጥ ተሳትፈዋል።

በአውሮፓውያኑ 1981 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ይዘው እስከ 2000 ድረስ ጋናን ከመሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጄሪ ራውሊንግስ ጋር በቅርበት ሰርተዋል።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ መኖሪያቸውን ወደ አሜሪካ ካደረጉ በኋላም፣ አፍሪካ አሜሪካዊት ባለቤታቸውን ተዋወቁ። ጥንዶቹ ሦስት ልጆች እንዳሏቸው ተነግሯል።

ከዋልደን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ጨምሮ፣ በተለያዩ የአሜሪካ ተቋማትም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

በአጠቃላይ 17 ዲግሪዎች እንዳላቸው የሚናገሩ ሲሆን፣ ትምህርታቸውም ስደት፣ ዓለም አቀፍ እና የስደተኛ ሕግን ያካትታል።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ ወደ ኬንያ የተመለሱት በአውሮፖውያኑ 2010 ሲሆን፣ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር እንደሚፈልጉ አስታውቀው ነበር።

ሆኖም በወቅቱ የነበረውን ሃሳባቸውን የተውት ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በሚደረገው ምርጫም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን ለየት ያሉ ሃሳቦችን እያነሱ መራጩን ሕዝቡ እየቀሰቀሱ ይገኛሉ።

የፕሮፌሰሩ ሌላ አወዛጋቢ የምርጫ ቅስቀሳ ተስፋ የተባለው ሠራተኞች በሳምንት አራት ቀን ብቻ እንዲሰሩ በማድረግ የሥራ እና የሕይወት ሁኔታን እንደሚያሻሽሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለሙስሊሞች አርብን፣ ቅዳሜ ለአድቬንቲስቶች እና ለሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ እሁድን የአምልኮ ቀናት እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።

ፕሮፌሰር ዋጃኮያህ የሞት ቅጣትን ለመመለስ ቃል የገቡ ሲሆን በሙስና የተከሰሱ ሰዎች “ኡጋሊ [የኬንያ ባህላዊ ምግብ] ከተመገቡ በኋላ” በጥይት ወይም በመሰቀል ሞትን መርጠው ቅጣቱ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።