የሳዑዲዎቹ ሁለት እህትማማቾች ምስጢራዊ አሟሟት በአውስትራሊያ

የፎቶው ባለመብት, New South Wales Police
ሰኔ መጀመሪያ አካባቢ ነበር ወቅቱ፣ የአውስትራሊያ ባለሥልጣናት በመዲናዋ ሲድኒ የሚገኝን አፓርታማ በር አንኳኩ፣ ነገር ግን ምላሽ አላገኙም።
ደብዳቤዎች ከበሩ ውጪ ተከምረው ነበር፣ እንዲሁም ተከራዮቹ ከሦስት ወራት በላይ የቤት ኪራይ አልከፈሉም።
እናም አፓርታማው ውስጥ ሲገቡ ከሳዑዲ አረቢያ የመጡት እህትማማቾችን ሞተው አገኟቸው። ፖሊሶች ሲያገኟቸው ከሞቱ ሳምንታት ያለፋቸው ሲሆን፣ በተለያዩ የመኝታ ክፍሎችም ውስጥ ነበር የተገኙት።
አስከሬናቸው ከተገኘ ሁለት ወር ቢያልፈውም እንዲሁም መጠነ ሰፊ ምርመራዎች ቢደረጉም የ24 ዓመቷ አስራ አብዱላህ አልሴህሊ እና ታናሽ እህቷ አማል አብዱላህ አልሴህሊ አሟሟታቸው እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው። ፖሊሶችም በተፈጠረው ነገር ግራ ተጋብተዋል።
አፓርታማውን ሰብሮ የመግባት ምልክቶች እንዲሁም በግለሰቦቹ ላይ በግልፅ የሚታይ ጉዳት ፖሊስ አላገኘም። በዚህም ሳቢያ አሟሟታቸውን “አጠራጣሪ” እና “ያልተለመደ” ነው ይላል ፖሊስ።
እህትማማቾቹ እንዴት እንደሞቱ ለመደምደም አሁንም የምርመራ ባለሙያ እየጠበቁ ናቸው።
የአውስጥራሊያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የመጀመሪያ ደረጃ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ምንም ፍንጭ ያልሰጠ ነበር።
“ስለሴቶቹ ብዙ የምናውቀው ነገር የለም” በማለት መርማሪ ኢንስፔክተር ክላውዲያ አልክሮፍት ሕዝቡ እንዲረዳቸው ጠይቀው ባለፈው ወር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“የሆነ ሰው መርማሪዎቻችንን ሊረዳ ይችላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Realestate.com
እህትማማቾቹ እነማን ነበሩ?
ስለ እህትማማቾቹ ይፋ የተደረገው መረጃ በጣም ውስን ነው። ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አውስትራሊያ ለኑሮ ያቀኑት በአውሮፓውያኑ 2017 ሲሆን፣ ባለሥልጣናት ምክንያታቸውን ባይገልጹም በአውስትራሊያ ለመኖር ጥገኝነት ጠይቀዋል።
ፖሊስ ቤተሰቦቻቸውን እንደ ተጠርጣሪ ለመቁጠር “የሚጠቁም ምንም መረጃ የለም” ብሏል።
እህትማማቾቹ በአውስትራሊያ የሙያ ትምህርት እየተከታተሉ በትራፊክ ተቆጣጣሪነት ይሰሩ ነበር። ምን አይነት የሙያ ትምህርት ይማሩ እንደነበረ ግን አልተገለጸም።
ጎረቤቶቻቸው ከሰው ጋር እንደማይቀላቀሉና ብዙውን ጊዜም በራሳቸው እንደሚያሳልፉ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ይኖሩበት የነበረው አፓርታማ ህንፃ ሥራ አስኪያጅ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው፣ ከመሞታቸው በፊት ባሉት ወራት ውስጥ የሕንፃውን ቪዲዮዎች እንዲያዩና አብረው እንዲያጣሩ ጠይቀውት ነበር።
እንደ ማይክል ቤርድ ገለጻ ምግብ የሚያመጣላቸው ግለሰብ የሆነ ነገር እያደረገው ነው በሚል አሳስቧቸው ነበር። ቪዲዮው ግን ምንም አላሳየም።
ሥራ አስኪያጁ በመጋቢት ወር ፖሊስ ነገሩን እንዲያጣራ የጠየቀ ሲሆን፣ እህትማማቾቹም ደህና ነን ሲሉ ለፖሊስ ተናግረዋል።
በኋላ ብቻውን ሄዶ ሲያናግራቸው የሆነ ነገር የንደፈሩና በድንጋጤም ላይ እንደነበሩ ማይክል ለሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ተናግሯል።
የተገኙ ፍንጮች ይኖሩ ይሆን?
ምንም እንኳን ፖሊሶች በአሟሟታቸው ላይ ዝምታን ቢመርጡም በአውስትራሊያ ውስጥ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። ምንድን ነው የተፈጠረው ራስን ማጥፋት፣ ግድያ ወይስ ሌላ?
አንዳቸውም በፖሊስ ባይረጋገጡም የአውስትራሊያ ሚዲያ ዘገባዎች ግን አንዳንድ ፍንጮችን እየሰጡ ይገኛሉ። ሆኖም ያሉት መረጃዎች ግልጽ ያልሆኑ እርስ በርሱም የሚጋጭ ሥዕልም ይሰጣል።
የአውስትራሊያ ጋዜጣ አንደኛዋ ሟች ከፆታ ዝንባሌዋ ጋር ተያይዞ ጥቃት ይደርስብኛል በሚል ስደትን እንደመረጠች፣ ሌላኛዋ ደግሞ ኢ-አማኒ መሆኗን ዘግቧል። በወግ አጥባቂዋና እስላማዊቷ አገር ሳዑዲ የተመሳሳይ ፆታ ማፍቀርም ሆነ ኢ-አማኒነት ሕገ-ወጥ ናቸው።
የአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኤቢሲ) እንደዘገበው በእህትማማቾቹ ክፍል ውስጥ የክርስቲያን መስቀል ያለባቸው የአንገት ሐብሎች መገኘቱን ዘግቧል።
የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ እንደተደረገ እና የቤት ኪራይ ለመክፈል መቸገራቸውን ሌላ ዘገባ አመልክቷል።
ሌላ ስሙ ያልተጠሰ ግለሰብ ለኤቢሲ እንደገለጸው ከመሞታቸው በፊት አንድ የማያውቀው ሰው ከእህትማማቾቹ አፓርትመንት ሲወጣና ሲገባ በርካታ ጊዜ ማየቱን ተናግሯል። ይህ ግለሰብም ሲጠየቅ ከእህትማማቾቹ አፓርታማ እንደወጣ ተናግሯል።
እንዲሁም ትልቋ አስራ በአውሮፓውያኑ 2019 ስሙ ባልተገለጸ ሰው ላይ የእግድ ትእዛዝ ብታወጣም ብዙም ሳይቆይ እንዳነሳችው ተዘግቧል።
ፖሊስ በእነዚህ ዘገባዎች ላይ የሰጠው አስተያየት የለም እንዲሁም ቢቢሲ ሊያረጋግጥ አልቻለም።
ሟቾቹ ሲኖሩበት የነበረውን አፓርትመንት ለማከራየት የወጣ ማስታወቂያ ላይ “እንደ ፖሊስ ከሆነ ወንጀል አልተፈጸመም እናም ለማኅበረሰቡ ጠንቅ ሊሆን አይችልም” የሚል አረፍተ ነገሮችን ይዟል።

የፎቶው ባለመብት, Saffaa
በሳዑዲ ዲያስፖራ ላይ የፈጠረው ፍራቻ
የአስራ እና የአማል ሞት በአውስትራሊያ የሚኖሩ የሳዑዲ ሴቶችን አስደንግጧል፣ አሳዝኗል እንዲሁም ፍራቻ አንግሶባቸዋል።
“ብዙዎቻችን በፍራቻ ውስጥ ነው ያለነው” በማለት ሳፋ የተባለች አርቲስት እና አክቲቪስት ተናግራለች።
የሳዑዲ ባለሥልጣናት እና ቤተሰቦች ወደ ውጭ አገር ለወጡና በስደትም ላይ ላሉ ሴቶች አደጋ ሆነው መቀጠላቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።
ዋቢ አድርጋም የምትጠቅሰው በአውሮፓውያኑ 2017 ከፊሊፒንስ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንድትመለስ በዘመዶቿ የተገደደችውን የዲና አሊ ላስሎምን ታሪክ ነው። ዲና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያለችበትም አልታወቀም።
አስራ እና አማል ሳዑዲ አረቢያን ለቀው መውጣት እንደተሳካላቸውና ለአምስት ዓመታት በኖሩባት ሲድኒ ከተማ ውስጥ ራሳቸውን ገድለዋል ብሎ ማመን እንደሚከብዳት ሳፋት ተናግራለች።
አብዛኛው የከተማዋ የሳዑዲ ጥገኞች ከስድስት ወራት በፊት ግንኙነታቸውን ከማቋረጣቸው በፊት ስለእነሱ ያውቁ ነበር ትላለች።
“በግልጽ የሆነ ችግር ተፈጥሯል፣ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍርሃትና መገለል እንዲደርስባቸው አድርጓል” ትላለች።
‘አውስትራሊያ አልረዳቻቸውም’
እህትማማቾቹ የሞቱበት መንገድ ምንም ይሁን ምን አውስትራሊያ እንዳልደረሰችላቸው ግልፅ ነው በማለት የሂዩማን ራይትስ ዎች ተመራማሪ ሶፊ ማክኔል ተናግረዋል።
ለማንኛውም ጥገኝነት ጠያቂ ሕይወት “በሚያሳዝን ሁኔታ ከባድ ነው” ነገር ግን የሳዑዲ ሴቶች “በተለይ ለከፋ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው” ሲሉም ያስረዳሉ።
“ሶሪያዊ ወይም አፍጋኒስታናዊ ከሆኑ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እያለፉ ያሉ በርካታ ሰዎች ያሉበት ማኅበረሰብ ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን የሳዑዲ ጥገኝነት ጠያቂ ሴቶች በጣም አናሳ ስለሆኑ ከፍተኛ ፍርሃትና መረበሾች አሉባቸው” በማለት ያስረዳሉ ።
በዚያ ላይ በርካታዎቹ የገንዘብ ችግር ይገጥማቸዋል። በአውስትራሊያ ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳያቸውን እየተጠባበቁ አነስተኛ አበል ያገኛሉ።
“ብዙዎቹ በአስተዳደጋቸው ሃብታም ከሚባሉ ቤተሰቦች የመጡ ናቸው። ይህንን ሁሉ ትተው መምጣት ድፍረት የተሞላበትና የማይታመን ውሳኔ ነው” ይላሉ።
ሳፋ እንደእነዚህ አይነት ሴቶች ለየት ያሉ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥማቸው ትናገራለች። እህትማማቾቹ ቪዛ ተከልክለዋል የሚለው ዘገባ እውነት ከሆነ “ግዴለሽነት እና ቸልተኝነት የተሞላበት” እንዲሁም በእርግጠኝነት አስጨንቋቸው እንደሚሆን ተናግራለች።
“የሚደግፋቸው እና ከጎናቸው አይዟችሁ የሚላቸው ሰው አለመኖሩ አሳዛኝ ነው” ትላላች ሳፋ።
የእህትማማቾቹ ሞት አውስትራሊያ የሳዑዲ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በተሻለ ሁኔታ መደገፍ እንዳለባት አጽንኦት ይሰጣል ሲሉ ሁለቱም ሴቶች ይናገራሉ።
“በእርግጥ የብቸኝነት ስሜት ተሰምቷቸው ነበር። ፈርተውም ነበር” በማለት ሶፊ ማክኔል ያስረዳሉ።
“እዚህ የመጡት ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ነበር፣ እኛ ግን አልረዳናቸውም” ብለዋል።












