ቻይናን ያስቆጡት ፖለቲከኛዋ ናንሲ ፔሎሲ ማን ናቸው?

 ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና እንደ ተገንጣይ ግዛቷ የምታያት፣ ከአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍን የምታገኘውን ታይዋንን አሜሪካዊቷ ፖለቲከኛ ናንሲ ፔሎሲ መጎብኘታቸው አወዛጋቢ ቢመስልም፣ የፔሎሲን ፖለቲካዊ ጉዞን ለተከታተለ ግን የሚያስደንቅ አይደለም።

የአሜሪካ የኮንግረስ አባልና የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የሆኑት ናንሲ ወደ 40 ዓመት በሚጠጋ የፖለቲካ ሕይወታቸውም ቻይናንን በጠንካራ ሁኔታ በመተቸት ይታወቃሉ።

ናንሲ በአውሮፓውያኑ 1991 ቤይጂንግ ባደረጉት ጉብኝት አቋማቸውን የሚያመለክቱ ሁኔታዎች በማንጸባረቃቸው የቻይና ባለሥልጣናትን አስቆጥተዋል እንዲሁም አስገርመዋል።

ፖለቲከኛዋ የቲያንሚን አደባባይ ጭፍጨፋ ሰለባዎችን የሚዘክር መፈክር በማውጣት የዲሞክራሲ ደጋፊ ተቃዋሚዎች ቻይና ፀጥታ ኃይሎች ጥቃት በፈጸሙባቸው ቦታ ላይ ቆመው ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል።

የ82 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋዋ ናንሲ ፔሎሲ በቻይና ኮሚኒስት አገዛዝ ላይ ጠንካራ ትችት ያላቸው ሲሆን፣ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ውዝግብ ውስጥ የከተታቸው ሌላኛው ጉዳይ በግዞት ላይ ካሉት የቲቤት መሪ ዳላይ ላማ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠራቸው ነው።

ባለፈው ዓመት የአሜሪካ መንግሥት ቻይና በዊጋ እና በሌሎች ግዛቶች በሚገኙ ሙስሎሞች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የዘር ማጥፋት ነው በሚል ዕውቅና እንዲሰጠው በዋነኝነት ሲያንቀሳቅሱም ነበር አፈ ጉባኤዋ።

“በቻይና ውስጥ በንግድ ትስስር ምክንያት ለሰብዓዊ መብቶች መቆም ካልቻላችሁ በሌሎች ቦታዎች ላይ ስለ ሰብዓዊ መብት መከበር ለመናገር የሞራል ሥልጣን ታጣላችሁ” በማለት ናንሲ 'ፖለቲኮ' ከተሰኘው ዜና ድረ-ገጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት አፈ ጉባኤዋ ያደረጉት የታይዋን አወዛጋቢ ጉዞ ከአውሮፓውያኑ 1997 ጀምሮ ሃገሪቱን የጎበኙ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ያደርጋቸዋል።

የፔሎሲ የጉብኝት ውሳኔ በቻይና ብቻ ሳይሆን በአገራቸው ባለሥልጣናትም ጥያቄ አስነስቷል። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በታይዋን መገኘት በቻይና እንደ ትንኮሳ ሊተረጎም እንደሚችልና የሕዝቡን ስጋት በመጥቀስ ጉብኝት “ጥሩ ሃሳብ አይደለም” ብለው ነበር።

በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ ለተናገሩት ነገር ፔሎሲ ጉዞውን ቀጥታ ባያረጋግጡም ታይዋንን በመደገፍ ረገድ ያላቸውን ጠንካራ አቋም አሳውቀዋል።

"ለታይዋን ድጋፍ ማድረጋችን ጠቃሚ ይመስለኛል" ሲሉም ተናግረዋል።

የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለፖለቲካ የታጩት ናንሲ

በአውሮፓውያኑ 1940 የተወለዱት ፔሎሲ አባታቸው የባልቲሞር የቀድሞ ከንቲባ ቶማስ ዲ አሌሳንድሮ ጁኒየር ናቸው።

በመጀመሪያ በዴሞክራቲክ ፓርቲ ጉባኤ ላይ ሲገኙም ገና የ12 ዓመት ታዳጊ ነበሩ፤ በ20 ዓመታቸውም በፕሬዝዳንት ጆን ኬኔዲ ሲመተ በዓል ላይ ተገኝተዋል።

በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ለዲሞክራቶች የምርጫ ዘመቻዎች እና የገንዘብ ማሰባሰቢያ ላይ በመስራት የመጀመሪያ የፖለቲካ ተሳትፏቸው ከመጋረጃ ጀርባ ነበር።

በቀጥታ ወደ ፖለቲካው ተሳትፎ የገቡት ከአምስት ልጆቻቸው የመጨረሻዋ ዩኒቨርስቲ ስትገባ ነበር። ለሞት ተቃርበው የነበሩት የሳንፍራንሲስኮ ኮንግረስ ተወካይ ሳላ በርተን ተተኪያቸው እንዲሆኑ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረትም ነበር በምርጩነት የተወዳሩት።

ፔሎሲ በአውሮፓውያኑ 1987 የምክር ቤት መቀመጫን አሸንፈው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሳን ፍራንሲስኮ ግዛትን በኮንግረስ ወክለው ይገኛሉ።

በተጨማሪም በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤነት ለሦስተኛ ጊዜ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፤ ይህ ሚና ከምክትል ፕሬዝዳንቱ ቀጥሎ በፕሬዚዳንትነት ተተኪነት ውስጥ እንዲቀመጡ ያደርጋቸዋል።

ፔሎሲም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናቸው።

ምንም እንኳን በሰላ ሁኔታ ቻይናን ቢተቹም የፓለቲካ ሕይወታቸው በቻይና ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም።

ፔሎሲ ለኮንግረስ በተመረጡበት በአውሮፓውያኑ 1987 ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፔሎሲ በአውሮፓውያኑ 2003 የነበረውን የኢራቅ ጦርነት በይፋ ከተቃወሙት ፖለቲከኞች አንዷ ናቸው።

በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት (የኤልጂቢቲ) መብቶች ተሟጋች የነበሩ ሲሆን በዚያን ወቅት እንደነዚህ አይነት ርዕሰ ጉዳዮች በአሜሪካ ውስጥ ከፖለቲካዊ ዋና ዋና ጉዳዮች በጣም የራቁ ነበሩ።

በተጨማሪም የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ 'የሮ ቨርሰስ ዌድ' የጽንስ ማቋረጥ ሕገ መንግሥታዊ የሴቶች መብት ነው የሚለውን ሕግ የመቀልበስ ውሳኔን በመቃወም ከፍተኛ ትቸት ሰንዝረዋል።

"አሜሪካውያን ዛሬ ከእናቶቻቸው ያነሰ ነፃነት አላቸው" በማለትም የሴቶችን የጽንስ ማቋረጥ መብት በሕግ መታገድ በመቃወም ተናግረዋል።

"ውሳኔው በጥፊ የመመታት ያህል ነው" ብለዋል።

ነገር ግን ፔሎሲ ሌሎች ሥራዎችን ቢሰሩም በዋነኝነት የጎሉበት ከቻይና ኮሚኒስት ገዥዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ በታይዋን ያደረጉትም ጉዞ ይህንን የበለጠ አጠናክሮታል።