ናንሲ ፔሎሲ የቻይናን ዛቻ ከቁብ ሳይቆጥሩ ታይዋን ገቡ

ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ናንሲ ፔሎሲ

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት ናንሲ ፔሎሲ የቻይናን ዛቻ ወደጎን በማለት ለጉብኝት ታይዋን ገቡ።

ቀደም ሲል ቻይና አፈ ጉባኤዋ ወደ ታይዋን ቢያቀኑ መዘዙ ከባድ ነው ስትል ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።

ፔሎሲ ታይዋን ዋና ከተማ ታይፔ መግባታቸው ከተሰማ በኋላ ቤይጂንግ ታይዋናን ከኢሲያ ወደሚለየው የውሃ ክፍል ተዋጊ ጄቶቿ ልካለች ተብሏል።

ቀደም ሲል የቻይና ባለሥልጣናት ፔሎሲ ታይዋን ቢጎበኙ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ሲሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ነበር።

ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ብትቆጥርም ቻይና ግን እንደ ተገንጣይ ግዛቷ ነው የምትመለከታት። ቻይና አስፈላጊ ከሆነም በኃይል ታይዋንን መልሳ የግዛቷ አካል ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ከዚህ ቀደም ገልጻለች።

ስለዚህም ቻይና እንደ አንድ የራሷ ግዛት አድርጋ የምታየት ታይዋን ከዋሽንግተን ዲሲ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት ማጠናከሯ እረፍት ነስቷታል።

ለፕሬዝዳንት ባይደን ጽህፈት ቤት በቀረበው መረጃ መሠረት ቻይና ምናልባትም በታይዋን አቅራቢያ ሚሳኤል መተኮስን ጨምሮ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የአየር ወይም የባሕር ላይ እንቅስቃሴዎችን ልታደርግ እንደምትችል ተገልጿል።

ለአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ መንበር ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፔሎሲ፤ የራስ ገዝ ግዛት ወደሆነችው ታይዋን ጉዞ ሲያደርጉ ከእአአ 1997 ወዲህ ግዛቷን የጎበኙ ከፍተኛ ባለሥልጣን አድርጓቸዋል።

የታይዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ሱ ሴንግ ጉብኝቱን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ እንዳሉት፣ ደሴቲቱ የትኛውንም የውጭ እንግዳ “በአክብሮት ትቀበላለች” ብለዋል።

ጨምረውም ታይዋን የትኛውም ጎብኚ ለመቀበል “ተገቢ የሆነውን ዝግጅት ታደርጋለች” ብለዋል።

የፔሎሲ ጉብኝት ከባድ ዲፕሎማሲያዊ ራስ ምታትን በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ መፍጠሩ እየተነገረ ነው።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው የከፍተኛ ባለሥልጣኗን ጉብኝት በተመለከተ የጉዳዩን ክብደትና አሳሳቢነት በተመለከተ ከዋሽንግተን ጋር ግንኙነት መደረጉን አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር በደሴቲቱ አቅራቢያ የሚካሄዱ የትኛውንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እየተከታተለ መሆኑን እና ከቻይና የሚመጣን ማንኛውንም ስጋት ለመመከት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ቻይና የፔሎሲን ጉብኝት ለምን ትቃወማለች?

ፔሎሲ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ስልጣን ያላቸው ተጽእኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ ናቸው። ፔሎሲ በአሜሪካ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሲሆኑ፣ ጉብኝታቸው ጉልህ አንደምታ አለው።

ይህን ያክል ተጽእኖ ያላቸው ፖለቲከኛ ወደ ራስ ገዟ ግዛት መሄዳቸው፤ ዋሽንግተን ዲሲ ለታይዋን ነጻ አገርነት ያላትን ቁርጠኝነት ስለሚያመላክት ቻይናን የማያስደስት ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪ በምክር ቤት አባልነት ከ35 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ፔሎሲ ቻይናን አጥብቀው በመተቸት እና ለታይዋን ድጋፍ በመስጠት ይታወቃሉ።

ፔሎሲ ከቀናት በፊት “ለታይዋን ድጋፍ ማሳየታችን ለእኛ አስፈላጊ ነው” ብለው ነበር።

ይህ ጉብኝት ከ25 ዓመታት በኋላ በከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ወደ ታይዋን የተደረገ ሲሆን፣ ፔሎሲ ይህንን ጉብኘታቸውን ከሌሎች የምክር ቤት አባላት ጋር ባለፈው ሚያዝያ ነበር ለማድረግ አቅደው የነበው።

ፔሎሲ በኮቪድ ታመው በመቅረታቸው ሌሎቹ የምክር ቤቱ አባላት ብዙም ውዝግብ ያላስከተለ ድንገተኛ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ግራፍ

ፍጥጫው ወዴት ያመራል?

የፔሎሲን የታይዋን ጉዞ ተከትሎ በቻይና እና በራስ ገዝ ግዛት በሆነችው ታይዋን መካከል ያለው ፍጥጫ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ተባብሶ ይገኛል።

ታይዋንን አስፈላጊም ከሆነ በኃይል መልሼ እጠቀልላሁ የምትለው ቻይና፤ ከዚህ ቀደም በርካታ የጦር አውሮፕላኖቿ ወደ ታይዋን የአየር ክልል ጥሰው መግባታቸው መዘገቡ ይታወሳል።

የታይዋን እና ቻይና ወታደራዊ ኃይል ንጽጽር

ከአሜሪካ በመቀጠል ለሠራዊቷ ትልቁን ወታደራዊ በጀት የምትመድበው ቻይና፤ በተለያዩ ወታደራዊ መስኮች አስገራሚ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ትጠቀማለች።

ቻይና ከታይዋን ጋር ዳግም የመዋሃድ ውጥኗን በተቻለ መጠን ወታደራዊ ባልሆነ መንገድ ለማሳካትና በተለይ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በመፍጠር ነገሮችን ለማሳለጥ ስትሞክር ቆይታለች።

ነገር ግን ቻይና ወታደራዊ አማራጭ ለመከተል የምትወስን ከሆነ ታይዋን በራሷ የቤጂንግን ክንድ መከላከል የምትችልበት አቅም አይኖራትም።

የቻይና እና የታይዋን ጦር ኃይሎች ንጽጽር

ቻይና በታይዋን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ብትከፍት የአሜሪካ እርምጃ በትክክል ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም።

አሜሪካ ታይዋን ራሷን እንድትከላከል ለመርዳት የሚያስገድድ ሕግ አላት። ይህ ሕግ ግን ሆነ ተብሎ ግልጽ እንዳይሆን ተደርጓል። በዚህም ቻይና ታይዋንን ብታጠቃ የአሜሪካ ምላሽ በአካባቢው ከባድ ቀውስን ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ይሰጋል።

አሜሪካ ምንም እንኳ ታይዋንን እንደ ሉዓላዊ አገር ባትቆጥራትም፤ ዴሴቲቱ አራሷን መከላከል እንድትችል በሚል የጦር መሳሪያ በሽያጭ መልክ ታቀርብላታል።