ቻይና ለወታደራዊ ልምምድ ስትዘጋጅ የታይዋን ጦር በተጠንቀቅ እንዲቆም ታዘዘ

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን ማቅናታቸውን ተከትሎ ቻይና ወታደራዊ ልምምድ ልታካሂድ ነው።
ፔሎሲ ወደ ታይዋን ቢያቀኑ መዘዙ ከባድ ነው ስትል የቆየችው ቤጂንግ በራስ ገዝ ደሴቷ ዙሪያ ለሶስት ቀናት ወታደራዊ ልምምድ ታደርጋለች ተብሏል።
ለዚህም ምላሽ ታይዋን ጦሯ በተጠንቀቅ እንዲቆም አዛለች።
ፔሎሲ ከታይዋን ፕሬዝዳንት ታዒ ኢን-ዌንግ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት የአገሪቱ ካቢኔ የአገሪቱ ጦር በተጠንቀቅ እንዲቆም አዟል።
ቀደም ሲል የቻይና ባለሥልጣናት ፔሎሲ ታይዋንን ቢጎበኙ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ሲሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ነበር።
ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ብትቆጥርም ቻይና ግን እንደ ተገንጣይ ግዛቷ ነው የምትመለከታት። ቻይና አስፈላጊ ከሆነም በኃይል ታይዋንን መልሳ የግዛቷ አካል ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ከዚህ ቀደም ገልጻለች።
ስለዚህም ቻይና እንደ አንድ የራሷ ግዛት አድርጋ የምታየት ታይዋን ከዋሽንግተን ዲሲ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት ማጠናከሯ እረፍት ነስቷታል።
ለፔሎሲ ጉብኝት የቻይና ምላሽ
አፈ ጉባኤ ፔሎሲ ለቻይናን ዛቻ እና ማስጠንቀቂያ ቁብ ሳይሰጡ ታይዋን ከተገኙ በኋላ፤ የቤጂንግ ምላሽ ወታደራዊ ልምምድ ሆኗል።
ቻይና ከነገ ሐሙስ ሐምሌ 28/2014 ዓ.ም. ጀምሮ፤ በታይዋን ዙሪያ ወታደራዊ ልምምዶችን ለማድረግ አቅዳለች።
ይህ ለቀናት ይዘልቃል የተባለው የአየር እና የባሕር ላይ ወታደራዊ ልምምድ ጦር መሳሪያዎችን መተኮስን ያካትታል።
ታይዋን በበኩሏ የቻይናን ወታደራዊ ልምምድ አጥብቃ የኮነነች ሲሆን የአገሪቱ ጦር በተጠንቀቅ እንዲቆም አዛለች።
የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር የአገሪቱ ጦር፤ “ማንኛውንም የታይዋን ሉዓላዊ ግዛትን ለሚጥስ እንቅስቃሴን ምላሽ ይሰጣል” ብሏል።
'ለማይናወጥ ድጋፍ እናመሰግናለን
የታይዋን ፕሬዝዳንት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲን ባገኙ ወቅት፤ አሜሪካ ለራስ ገዝ ግዛቷ ለምታደርገው “የማይናወጥ ድጋፍ” ታመሰግናለች ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ታዒ ኢን-ዌንግ ናንሲ ፔሎሲን የታይዋን “የቅርብ ወዳጅ” ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን የክብር ሜዳሊያም ሸልማዋቸዋል።
ፔሎሲ ይህን ሜዳሊያ በአሜሪካ እና በታይዋን መካከል ያለውን “ጠንካራ እና ዘላቂ ወዳጅነት ያመላክታል” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።












