አዲሱ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ “የሥነ ልቦና ጦርነትን የመመከት ሥልጣን’’ ምን ስጋት ይዟል?

የፎቶው ባለመብት, niss
የሥነ ልቦና ጦርነት ቃሉ በራሱ እጅግ አከራካሪ አንዲሁም አተረጓጎሙም የተለያየ መልክ ያለው ነው። ነገር ግን ፕሮፓጋንዳ ዋነኛ ይዘቱ ነው።
ነገርግን ከመደበኛ ጦርነት እና የትጥቅ ትግል ጋር ተያይዞ በጠባቡ የሚተረጉሙት አሉ።
ሌሎች የሲቪል ዜጎችንም ጭምር ኢላማ በማድረግ ሆነ ተብሎ በተቀናጀ መልኩ የሚመራ የፕሮፓጋንዳ ሥራ አድርገው ይመለከቱታል።
ዋና አላማው ተዋጊዎች የጠላታቸውን ሞራል ዝቅ ማድረግ ነው።
ለዘመናት በተለይም የጦር መሪዎችን ብሎም ወታደሮችን ኢላማ ያደረገ እንዲሁም በባሕላዊ የመገናኛ ዘዴዎች የሚተላለፍ ነበር።
ነገር ግን ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ከኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሥነ ልቦና ጦርነት በተዋጊውም ሆነ በኢላማው መካከል ግራጫ መስመር ተፈጥሯል።
ከምክንያቶቹ አንዱ ከዚህ ቀደም መንግሥታት የሚመሩት የነበረው ዘመቻ አሁን መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ጭምር የሚሳተፉበት መሆኑ ነው።
ክንፈ ይልማ (ዶ/ር) በአዲስ አባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። በተለይም በበይነ መረብ (ሳይበር) ሕግ ልምድ ካካበቱ ምሁራን መካከል ናቸው።
ኢንተርኔት ያቀለለው የመረጃ ማስተላለፍ ተግባር ብሎም ሰዎች ማንነታቸው ሳይታወቅ ጭምር መረጃዎችን ማሰራጨት መቻላቸው የሥነ ልቦና ጦርነትን ጉዳይ አገራት በአንክሮ እንዲመለከቱት አድርጓል ብለው ያምናሉ።
የሥነ ልቦና ጦርነት እና ኢትዮጵያ
የሥነ ልቦና ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ እና ከቀዝቃዛው ጦርነት መጀመር ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ ቃል ነው።
የወታደራዊው ደርግ ሊቀ መንበር ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በ70ዎቹ መገባደጃ ላይ “ኢምፔሪያሊስቶቹ የሥነ ልቦና ጠርነት ከፍተውብናል” ሲሉ ምዕራባውያንን የወቀሱበት ንግግራቸው በኢትዮጵያም ይህ እንግዳ ጉዳይ እንዳልሆነ ማሳያ ነው።
በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ስለሥነ ልቦና ጦርነትን ሲናገሩ ተሰምተዋል።
ነገር ግን እስካሁን የሥነ ልቦና ጦርነትን በተመለከተ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ሆነ በሌሎች መንግሥታዊ ሰነዶች ላይ በተብራራ ሁኔታ አልሰፈረም።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. ባደረጉት ስብሰባ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤቱን ማቋቋሚያ አዋጅ አሻሽሏል። ማሻሻያው ከያዛቸው አንቀጾች መካከል አንዱ ተለይ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ቀልብ ስቧል።
የማሻሻያ አዋጁ ስድስት ተጨማሪ ሥልጣንና ኃላፊነቶችን ለብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ተቋም ተሰጥቷል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሥነ ልቦና ጦርነትን መመከት ነው።
በዚህም ማሻሻው “በአገር ላይ የሚቃጡ የሥነ ልቦና ጦርነቶችን የመመከት ሂደትን በበላይነት የመምራት፣ የማስተባበር” ኃላፊነት ለተቋሙ መሰጠቱን አመልክቷል።
እንዲሁም ከዓመታት በፊት ተጠሪነቱ ለሰላም ሚኒሰቴር ተሰጥቶ የነበረው የኢምግሬሽን እና ዜግነት ጉዳዮች አገልግሎት እንዲሁም የስደተኞች እና የስደት ተመላሾች አገልግሎትን የመቆጣጠር ኃላፊነቱም ተመልሶለታል።
“እንዲሁም ማንኛውም ሰው ከአገልግሎቱ የተሰጠውን መረጃ መጠቀም እና ሥራ ላይ ማዋል አለበት” ይላል አዲሱ አዋጅ። ይህንን ግዴታ ያለመወጣትም በወንጀል ሕጉ መሰረት ተጠያቂነት እንደሚያስከትል አዋጁ ይገልጻል።
የሥነ ልቦና ጦርነት መካተቱ ለምን ያሰጋል?
አዲስ የጸደቀው አዋጅ በሌሎች ሕጎች ላይ እንደሚደረገው ሁሉ ስለ ተግባሩ በቂ ትርጉም አያስቀምጥም። እንዲሁም ማንን ይመለከታል የሚለውን ጨምሮ ኃላፊነቱን ከመስጠት ያለፈ ማብራሪያዎች የሉትም።
የፀረ ሽብር ሕግ፣ የኮምፒተር ወንጀሎች ሕግ፣ ሐሰተኛ መረጃን ለመቆጣጠር የወጣ ሕግ ብሎም የወንጀል ሕጉ እያለ ይህንን አዋጅ ማውጣት ለምን አስፈለገ የሚለው በቂ ምላሽ ያልተገኘለት ነው።
የዘርፉ ባለድርሻዎች በጉዳዩ ላይ በቂ ምክክር አልተደረገም የሚል ቅሬታ እያሰሙ ባሉበት ወቅት አዋጁ በችኮላ እንዲጸድቅ የተደረገበት ምክንያት ጥያቄን አስከትሏል።
“ይህንን የሕግ ማሻሻያ የወለደው አገሪቱ ውስጥ ከሁለት ዓመት በላይ የቆየው የፀጥታ ችግር እና አለመረጋጋት ይመሰልኛል። የመንግሥት አካላት ይህ ጉዳይ ችግሩን አባብሶታል ብሎ ከማመን የመነጨ የመጣ ይመስለኛል” ሲሉ ክንፈ ይልማ (ዶ/ር) ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
የሕግ ባለሙያው ‘የመረጃ ጦርነት’ ብሎም ‘የሳይበር ኦፕሬሽን’ የመሳሰሉ ተግባራት አሁን በአገሪቱ በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች የተሸፈኑ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።
ከተቋቋመበት አላማ አንጻርም ይህ ሥልጣን የአገሪቱ የመረጃ መረብ ደኅንት ተቋም (ኢንሳ) እነዚህን ሥራዎች ለመስራት ተገቢው ተቋም ይሆን ነበር ሲሉም ያክላሉ።
“ሁኔታው ሕጉን ባረቀቁት ሰዎ እና በሚመለከታቸው ሰዎች መካከል ምን ያህል ንግግር ነበር የሚለውን የሚያሳይ ይመስለኛል” ሲሉ ክንፈ ይናገራሉ።
መፍትሄው ምንድነው?
የሥነ ልቦና ጦርነትን የሚያስተዳድር ገዢ አለማቀፍ ሕግ የለም። ለዚህም አገራት የአገር ውስጥ የሕግ እና የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ተጠቅመው ቀዳዳውን ለመሸፈን ይሞክራሉ።
ለምሳሌ አሜሪካ በጦር ኃይሏ ውስጥ የሥነ ልቦና ጦርነትን እንዲዋጉ የተደራጁ ክፍለ ጦሮች አሏት። ነገር ግን ይህ ሠራዊትም ሆነ አባላቱ በዜጎች ላይ ይህንን ሥልጣናቸውን መጠቀም እንደማይችሉ በሕግ ተደንግጓል።
ከአሜሪካ ባሻበር በርካታ የዓለም ኃያላን አገራት ይህንን የፕሮፓጋንዳ ጦርነት የተመለከቱ ሕጎች፣ መዋቅሮች ብሎም የሥራ ክፍሎች አሏቸው። ነገር ግን በጠንካራ ቁጥጥር ይህ የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ብሎም ሰብአዊ መብቶቻቸውን አደጋ ውስጥ እንዳይከት ለማድረግ ይጥራሉ።
በዓለም አቀፍ ሕግጋት በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በማሰብ በተባበሩት መንግሥታት ደረጃ ጥረቶች እንዳሉ የሚናገሩት ክንፈ፤ ጥረቶቹ በቅርቡ ውጤት ያመጣሉ ብለው አያምኑም። ይህም በተለይ በኃያላን አገራት መካከል ባለው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ምክንያት ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት ከፀረ ሽብር ሕጉ ላይ ከሰፈሩት ወንጀሎች ጋር ያለው ልዩነት ምንድነው? የሚለው አሁንም ግልጽ አይደለም።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ግለሰቦች፣ መገናኛ ብዙኃን እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በወቅታዊ ወይም በፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው ሃሳቦች በዚህ አዲስ ሕግ ጫና ስር እንዳይወድቁ ስጋቶች አሉ።
“በመናገር ነጻነት እና ተያያዥ መብቶች ላይ ጫና ይዞ እንዳይመጣ ብሎም ተቋማት እና ግለሰቦች ራሳቸውን ሳንሱር ማድረግ ውስጥ እንዳይገቡም እሰጋለሁ” ሲሉ የሕግ ምሁሩ ክንፈ ይልማ (ዶ/ር) ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ጨምረውም ሕጉ ለመብት ጥሰት እንዳይውል የማድረግ ኃላፊነት አሁንም መንግሥት ላይ መሆኑንም ያሳስባሉ።
“ግልጽ ያልሆኑ እና እርግጠኝነት የጎደላቸው ነገሮችን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢያንስ በደንብ መልክ ወይም የጸጥታ ተቐሙ ተጨማሪ መመሪያዎችን በማውጣት መብራራት ይኖርበታል” ሲሉም ይመክራሉ።
እነዚህ ትርጓሜዎችም የመናገር መብትን ጨምሮ ሰብአዊ መብትን በማይነካ ሁኔታ መተርጎም እንደሚኖርበት ይናገራሉ።
ከዚህ በዘለለ ግን የሲቪል ማኅበራት ትልቅን ሥራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው በመጥስ፣ ከዚህ በፊት በተለያዩ ሕጎች ዙሪያ ሲያደርጉ እንደቆዩት አሁንም ቅስቀሳዎችን በማድረግ ይህ አዲስ ሥልጣን ለመብት ጭፍለቃ እንዳይውል ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉም ያሳስባሉ።












