አልሻባብ እና አይኤስን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ መያዛቸው ተነገረ

አዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office of Addis Ababa/FB

ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሰርገው በመግባት የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ ናቸው የተባሉ ከ450 በላይ የተለያዩ ቡድኖች አባላት በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።

ይህ የተገለጸው የፌደራል የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በአገሪቱ ያለውን አጠቃላይ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 16/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ ነው።

በዚህም ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት “የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ነበሩ” የተባሉትና በቁጥጥር ስር የዋሉት “የፋኖ፣ የህወሓት፣ የሸኔ፣ የአልሻባብ፣ የአይኤስ አባላት እንዲሁም ሁከትና ብጥብጥ ለማስናሳት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ” የተባሉ 454 ተጠርጣሪዎች ናቸው ተብሏል።

የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል ከተባሉት ተጠርጣሪዎች መካከል ከፍተኛው ቁጥር ያላቸው 174ቱ የህወሓት አባላት ሲሆኑ፣ 100 በአዲስ አበባ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሙከራ አድርገዋል የተባሉ፣ 98 የሸኔ፣ 51 ጽንፈኛ የተባሉ የፋኖ አባላት ናቸው።

በተጨማሪም የሶማሊያው አስላማዊ ቡድን አልሻባብ እና ዓለም አቀፉ የሽብር ቡድን አይኤስ 31 አባላት በአዲስ አበባ ውስጥ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም እና ትርምስ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል ከተባሉት 454 ተጠርጣሪዎች መካከል ይገኙበታል።

መግለጫው ጨምሮም ከአንድ ወር በፊት በጋምቤላ፣ በጊምቢ እና በደምቢ ዶሎ ከተሞች ለተፈጸሙት ጥቃቶች ህወሓትን፣ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ)፣ የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅንቄ (ጉህዴን) እና ኦነግ-ሸኔን ተጠያቂ አድርጓል።

እነዚህ ጥቃቶችን ተከትሎ የአገሪቱ የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በወሰደው እርምጃ “137 የቡድኖቹ አባላት መደምሰሳቸውንና በርካቶች መማረካቸውን” ጠቅሶ፤ በተጨማሪም ከሰኔ 07 እስከ ሐምሌ 07 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደ ዘመቻ “ከ153 በላይ የሽብር ቡድኑ አባላት ተደምስሰው፣ ከዘጠኝ መቶ በላይ በቁጥጥር ስር ውለው በህግ እየተጣራ ይገኛል” ብሏል፡፡

መግለጫው ከዚህ ባሻገር ፋኖን ሽፋን በማድረግ በህቡዕ የተደራጁ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ያላቸው “የንፁሃን ዜጎችን ህይወት እያጠፉ፣ ከቤት ንብረት እያፈናቀሉ እና እየዘረፉ የነበሩ” እና በተለያዩ ወንጀሎች ሲፈለጉ ነበር ያላቸውን 5804 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብሏል።

ግብረ ኃይሉ በአማራ ክልል እና በፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጥቃት ለመፈፀምና መንግሥትን በኃይል ለመጣል እንዲሁም የሽግግር መንግስት ለማቋቋም በህቡዕ ሲንቀሳቀሱና ሲያሴሩ በነበሩ ያላቸው “14 የጽንፈኛ የፋኖ አባላት” ከተለያዩ ምስጥራዊ ሰነዶቻቸው መያዛቸውን በመግለጫው ጠቅሷል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥቱ፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል መስተዳደሮች ከሁለት ወር በፊት ጀምሮ ሕግ የማስከበር ያሉትን ዘመቻ እኣካሄዱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

በአማራ ክልል ፋኖ ከተባለው ቡድን ጋር በተያያዘ በሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ናቸው የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፣ በክልሉ የጦር መሳሪያ ምዝገባም ተካሂዷል።

በኦሮሚያ ክልልም መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀውና ሸኔ በሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ላይ ዘመቻ መክፈቱንና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መታሰራቸው ተገልጿል።

ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በጋምቤላ ከተማ እና በምዕራብ ወለጋ ውስጥ ታጣቂ ቡድኖች በፈጸሟቸው ጥቃቶች አብዛኞቹ ሴቶችና ሕጻናት የሚገኙባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መገደላቸው ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችት የተሰነዘረበት ሲሆን የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወታ ከሕዝቡ፣ ከሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ጥያቄዎች ቀርቦለታል።