በአማራ ተወላጆች ላይ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ አምነስቲ ጠየቀ

ቀደም ሲል ወለጋ ውስጥ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከተፈጸሙ ጥቃቶች በኋላ ተፈናቅለው አማራ ክልል ሐይቅ ከተማ በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቀደም ሲል ወለጋ ውስጥ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከተፈጸሙ ጥቃቶች በኋላ ተፈናቅለው አማራ ክልል ሐይቅ ከተማ በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ከ400 በላይ የአማራ ተወላጆች ላይ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ላይ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ገለልተኛ የሆነ ምርመራ እንዲያከናውኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

የመብት ተቆርቋሪው ድርጅት በዛሬው ዕለት ሐምሌ 14/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም. በተፈጸመው ጭፍጨፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም በርካቶች መቁሰላቸውን ገልጿል።

“በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ተፈፅሟል የተባለው በቶሌ የተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ለሰው ሕይወት ያላቸውን ግድየለሽነት ያሳየ ነው። ሴቶች እና ህጻናት ሕይወታቸውን ያጡበት ይህ አሰቃቂ ግድያ ገለልተኛ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ መመርመር አለበት” ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮስ ሙቼና ተናግረዋል።

አክለውም “የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እነዚህን ግድያዎች የፈጸሙ ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ እስከ መጨረሻው ድረስ ሊሄዱ ይገባል” ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያነጋገራቸው የአካባቢው የአስተዳደር ባለሥልጣን በጥቃቱ ቢያንስ 450 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። 

በጊምቢው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ብዛት 338 መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ከዚህ ቀደም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

አምነስቲ ከጥቃቱ የተረፉ እና የተጎጂ ቤተሰቦችን ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረው ግድያዎቹ የተፈጸሙት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሆኑን ነው።

ቢቢሲ ያናገራቸው ከጭፍጨፋው የተረፉ ነዋሪዎችና መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው ‘ሸኔ’ በሚል የሚጠራው ታጣቂው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደሆነ ሲገልጹ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጎ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ መጠየቁ ይታወሳል። 

ተቋሙ የዐይን እማኞችን፣ ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎችን፣ የተጎጂዎችን ቤተሰብ አባላት እና የአካባቢውን ባለሥልጣናት ጨምሮ 10 ግለሰቦችን አናግሯል።

በዚህም ጥቃት የጅምላ ግድያ፣ ቤቶች ማቃጠልና ዘረፋ ተፈፅሟል ብለዋል። በተጨማሪም የአምነስቲ የምርመራ ቡድንም የሳተላይት ምስሎችን የመረመረ ሲሆን ሰኔ 11/2014 ዓ.ም. በቶሌ ቀበሌ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱንም አረጋግጧል።

በምዕራብ ወለጋ በሁለት ሳምንት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ወገኖች ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጭፍጨፋውን በተመለከተ ምርመራ አድርጎ ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ማዘዙ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም በጥቃቱ ዙሪያ ምርመራ እንደሚያደርግ አሳውቋል።

“ባለሥልጣናቱ ጥቃቱን ሊከላከሉ አልቻሉም”

አንድ የአካባቢ ባለሥልጣን ለአምነስቲ እንደገለጹት ጥቃቱ ወዲያውኑ ለወረዳ እና ለዞኑ ባለሥልጣናት ሪፖርት መደረጉን ጠቁመው መንገዱ በመዘጋቱ ምክንያት ምላሽ መስጠት አልተቻለም ብለዋል።

ጥቃት አድራሾቹ በቶሌ መንደሮች ነዋሪዎችን ሲገድሉ፣ ቤት ሲያቃጥሉና ሲዘርፉ አምስት ሰዓታት ያህል መቆያታቸውን የዐይን እማኞች ለአምነስቲ የተናገሩ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የመንግሥት ኃይሎች አልተከላከሉም ማለታቸው ሰፍሯል።

የአካባቢው ወረዳ አስተዳደር መቀመጫ ጊምቢ ከቶሌ በ49 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ስፍራው የደረሱት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ከወጡ ከሰዓታት በኋላ ሲሆን፣ በወቅቱም የቤተሰቦቻቸውንና የዘመዶቻቸውን አስከሬን እየሰበሰቡ እንደነበርም ተናግረዋል።

“በኦሮሚያ ክልል የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን ከዘፈቀደ ግድያ እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ረገጣዎች መጠበቅ አለበት” ሲሉ ዴፕሮስ ሙቼና አሳስበዋል። 

“በድንገት መጥተው ነው ጥቃት ያደረሱብን”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥቃቱ የጀመረው ሰኔ 11/2014 ዓ.ም. ከጥዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ሲሆን በርካቶች ወደ እርሻዎቻው ወይም ሌሎች ጉዳዮች ከወጡ በኋላ መሆኑን አምነስቲ ከዐይን እማኞች ተረድቷል።

በወቅቱ በቶሌ ቀበሌና በአካባቢው ነበርን ያሉት የዐይን እማኞች የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በአካባቢው የሚገኙ መንደሮችን ከከበቡ በኋላ ጥቃቱ መጀመሩን የሚያሳይ የተኩስ ድምፅም ተሰምቷል ብለዋል።

በመንደሮቹ ውስጥ በአብዛኛው የነበሩት ከአጥቂዎች መሸሽ ያልቻሉ ህፃናትና እናቶች መሆናቸውንም እነኚሁ የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

አምነስቲ ያናገራቸው ሁሉም የዐይን እማኞች በጭፍጨፋው በርካታ ዘመዶቻቸውን እንዳጡና አብዛኞቹም ሴቶች እና ህፃናት ናቸው ብለዋል።

ከጥቃቱ የተረፈችው ጀሚላ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ባሏን እርሻ እያረሱ በነበረበት ወቅት በገጀራ እንደገደሉትና እሷንም በጥይት እንደመቷት ተናግራለች። እርዳታ እስከምታገኝ ድረስም ከሌሎች ከሞቱ ሰዎች መካከል ወድቄ ነበር በማለት ለአምነስቲ ደረሰብኝ ያለችውን አስረድታለች።

22 ልጆች እና የልጅ ልጆቻቸውን ማጣታቸውን የሚናገሩት የ64 ዓመቱ ሁሴን* ሴቶቹ እና ህፃናቱ ከጥቃቱ እንተርፋለን በሚል እሳቤ ቤታቸው የተቀመጡ ሲሆን እሳቸውን ግን ህይወታቸውን ለማትረፍ ሸሽቻለሁ ብለዋል።

ቤተሰቦቻቸውን ከ42 አስከሬኖች መካከል ተከምሮ ያገኙት አቶ ሁሴን የተወለዱ የልጅ ልጆቻቸውን ጨምሮ በርካታ ህፃናትና ሴቶች ተገደለው መጣላቸውን አስረድተዋል።

ከነዋሪዎች በተጨማሪ በጥቃቱ ሶሰት ልጆቻቸውን እና የሰባት ወር ነፍሰ ጡር የሆነችውን ባለቤታቸውን ያጠት የአካባቢው አስተዳደር ባለስልጣን አቶ ጀማል* ናቸው።

የሳቸውን ቤተሰብ ጨምሮ 112 ሰዎች ስልሳው በተባለ ስፍራ እንዲሁም ጨርቆሳ በተባለ ሰፈር 104 ሰዎች ተገድለዋል የሚሉት እኚሁ ባለስልጣን "ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ ህፃናት አራስ እና ጨቅላ ይገኙበታል” ብለዋል።

አስከሬናቸው በጥይት እንደተበሳሳም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በእርሻ ስፍራቸው ላይ የነበሩት አቶ አብዲ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ጥቃቱ ጥዋት 2፡30 ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በሳቸው መንደር እንደቆየ ገልጸው በሌሎች መንደሮች እስከ አመሻሹ 10 እና 11 የዘለቀ ለሰዓታት የቆየ መሆኑን ያስረዳሉ።

አንዳንድ ነዋሪዎች የታጠቁ ቢሆንም ታጥቀው ከመጡት ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አንፃር ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆናቸው ራሳቸውን መከላከል እንዳልቻሉም ገልጸዋል። ከተገደሉት መካከል አብዛኞቹ ያልታጠቁ ሴቶችና ህፃናት ናቸው።

“በኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው ተጠያቂነት ያለመኖር ባህል የግጭቶች ዑደቶችን እየፈጠረ ነው። ባለሥልጣናቱ በአገሪቱ የተፈጸሙ ጥሰቶች ሁሉ ተዓማኒነት ያለው እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲከናወን ማድረግ አለባቸው። በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ለተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲመረምር ማመቻቸት አለባቸው ብለዋል ዴፕሮስ ሙቼና።

“የጎረቤቴን ቤት ከነቤተሰቡ አቃጠሉት”

በአማራ ተወላጆች ላይ ከተፈፀመው ጭፍጨፋ በተጨማሪ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቤቶችን ማቃጠልን ጨምሮ፣ ከብቶች፣ ብር እና እህል ዘርፈዋል ተብሏል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎቹ ጎረቤታቸው ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ መመልከታቸውን ዳውድ የተባሉ ግለሰብ ተናግረዋል

“የጎረቤቴን ሻምበል መሐመድን ቤት አቃጥለዋል፣ ቤተሰቡ ከልጆቹ እና የልጅ ልጆቹ ጋር በአጠቃላይ ቤት ውስጥ 12 ሰዎች ነበሩ። አንዷ የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ስትሆን ከሁለት ልጆቿም ጋር ነበረች። ሙሉ በሙሉ በመቃጠላቸው እዚያው ግቢው ውስጥ ተቀብረዋል” ብለዋል።

አብዲ የተባሉ ሌላ እማኝ ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከመኖሪያ ቤታቸው 4 በሬዎችን እና 70 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ መዘረፋቸውን አስረድተዋል።

የዐይን እማኞቹ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሆናቸውን መለየት የቻሉት ረዥም በሆነውና በተሰራ ፀጉራቸው፣ ወታደራዊ መለያ ልብሳቸውና ኦሮምኛ ቋንቋ ስለሚናገሩ ነው።

በተጨማሪም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በአካባቢው ቢያንስ ለአራት ዓመታት ሲንቀሳቀስ እንደነበርም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ወደ አገር ተመልሶ ወደ ፖለቲካው መድረክ ከተቀላቀለው ኦነግ በመነጠል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በትጥቁ ትግል ቀጥሏል።

መንግሥት ሸኔ በማለት የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አሸባሪ ተብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈረጀ ሲሆን በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎችም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በተደጋጋሚ ውጊያ አድርጓል።

አምነስቲ ቀደም ሲል በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መፈጸሙ የተገለጸ በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት ሪፖርት አውጥቷል።

ነገር ግን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በቶሌ የደረሰውን ጥቃት ጨምሮ በአባላቱ የሚደርሰውን ክስ ያጣጣለ ሲሆን በምትኩ ግን የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።

*አምነስቲ ለሪፖርቱ ያናገራቸው ግለሰቦች ስም ለደኅንነታቸው ሲባል እንዲቀየር ተደርጓል።