በምዕራብ ኦሮሚያ ሰላማዊ ዜጎች እየተገደሉ ያሉት ለምንድነው?

በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመሸሽ ከወለጋ ተፈናቅለው ሐይቅ ውስጥ በተፈናቃዮች ማዕከል ውስጥ የሚገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመሸሽ ከወለጋ ተፈናቅለው ሐይቅ ውስጥ በተፈናቃዮች ማዕከል ውስጥ የሚገኙ

አቶ ሞሐመድ ዩሱፍ* ድርቅ ሽሽት ከመኖሪያ ቀየያቸው ሃርቡ ስድስት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ያቀኑት በ1990ዎቹ ነበር።

በጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ኑሯቸውን መስርተው ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ለዘመናት ኖረዋል።

ነገር ግን የ64 ዓመቱ ሞሐመድ ሰኔ 11/2014 የልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ተነጠቁ።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ሞሐመድና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች የተገደሉት ብሔርን መሠረት ባደረገ ጥቃት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአቶ ሞሐመድ መጀመሪያ ልጅ የሆነችው የ40 ዓመቷ ሰሚራ ሞሐመድን እና የአራት ቀን የሕጻን ልጇን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በዚህ ጥቃት ተገድለዋል።

"ልጆቼን እና የልጅ ልጆቼን ጨምሮ በጠቅላላው 61 ሰዎችን በአንድ መቃብር ቀበርን" ሲሉ አቶ ሞሐመድ ከጥቃቱ በኋላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለቢቢሲ ምስክርነታቸው የሰጡ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ግድያው ቢያንስ ለስድስት ሰዓታት ቆይቷል ይላሉ።

ከዚህ ጥቃት የተረፉ አብዛኞቹ ሰዎች በመስጂዶች ተጠልለው ይገኛሉ።

"በጣም ያስፈራ ነበር። 25 ገደማ ወጣቶች ወደ ጫካ ተወስደው እንደተገደሉ ሰምተናል። ሬሳቸውን እስካሁን አላገኘንም" ሲል አንድ የዐይን እማኝ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ይህ አሰቃቂ ጥቃት ያስከተለው ሐዘን ሳያባራ በሁለተኛ ሳምንቱ እዚያው ኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈፀመ።

ሰኔ 27/2014 የተፈፀመውን ጥቃት ቀድሞው ያሳወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ለጥቃቱ "ተጠያቂው ኦነግ-ሸኔ ነው" ብለው፤ ቡድኑን ለማጥፋት "ቃል እንገባለን" አሉ።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ለጥቃቶቹ ተጠያቂው ማነው?

ብሔር ተኮር ጥቃቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መታየት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። አብዛኞቹ ጥቃቶች የሚፈፀሙት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተለመከተ ጣት መጠቋቆም ከጀመሩ ሰንብተዋል።

መንግሥት፤ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃቶች ይፈጽማል ሲል በተደጋጋሚ ይከሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም. ለሕዝብ እንደራሴዎች ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት "እንደ ሸኔ [ኦሮሞ ነፃነት ግንባር] ያሉ አሸባሪ ድርጅቶች ብሔርና እምነትን መሠረት አድርገው ብጥብጥ ለመፍጠር እየጣሩ ነው" ብለው ነበር።

በመንግሥት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን [ኢሰመኮ] ለጥቃቶቹ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና የክልሉ ፀጥታ አካላት ተጠያቂ ናቸው ይላል።

ኮሚሽኑ ሰኔ 30/2014 ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባስገባው ሪፖርት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በተደጋጋሚ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ፈፅሞ ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል ብሏል።

"ቡድኑ ሰኔ 11/2014 በቶሌ ቀበሌ በፈፀመው ጥቃት የአማራ ብሔር ተወላጆችን ገድሏል።"

ኮሚሽኑ ባለፉት 12 ወራት አጠናቀርኩት ባለው ዘገባው የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ አካላት በከረዩ በፈፀሙት ጥቃት የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎችን ተገድለዋል ብሏል።

ኢሰመኮ ስለሰኔ 27ቱ ጥቃት ምርምራ እያደረገ እንደሆነ ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በቅርቡ ስለተፈፀሙት ጥቃቶች ምርመራ እያደረግን ነው። ስለጥቃቱ ሰለባዎች የተጣራ መረጃ ለጊዜው የለንም" ሲሉ ኮሚሽነሩ ምላሻቸውን በኢሜይል አሳውቀዋል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የተሰኘው ድርጅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጥቃት የሚደርስባቸው የአማራ ተወላጆችን ድምፅ በማስተጋባት ይታወቃል።

ማኅበሩ መንግሥትም ሆነ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ለጥቃቱ ተጠያቂ ናቸው ይላል።

የማኅበሩ ተጠሪዎች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሆነ ማንደፍሮ ጥቃቶቹ ብሔር ተኮር ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በበኩሉ "መንግሥት ጥቃቶችን ፈጽመዋል ብሎ ጣቱን ወደኛ የሚጠቀሙው ስማችንን ለማጥፋት ነው" ሲል ያስተባብላል።

የሠራዊቱ አዛዥ ኩምሳ ድሪባ ከሁለት ተከታታይ ጥቃቶች በፊት "ሠራዊታችን ሰላማዊ ሰዎችን አያጠቃም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ጥቃቶች አሁን ለምን ጨመሩ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከጨበጡ ወዲህ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በርከተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የቀድሞ ጠበቃና ዲፕሎማት የሆኑት ባይሳ ዋቅዋያ "ከጥቃቶቹ ጀርባ ያለው ምክንያት ውስብስብ ነው" ይላሉ።

"በዚህ ወቅት ጥቃቶች እንደህ መበራከታቸው ምክንያቱ ጥልፍል እና ሥር የሰደደ ነው ብዬ አምናለሁ። ባለፈው ታሪካችን የሆነ የተሳሳትነው ነገር አለ። ተመልሰን እሱን ለማቃናት ካልሞከርን መፍታት እንችላለን ብዬ አላስብም" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

"በአገር ምሥረታችን ላይ አንድ የሳትነው ጡብ አለ" ሲሉ ያክላሉ።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በበኩሉ በኢሕዴግ ዘመን ሥራ ላይ የዋለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለዘመናት የአማራ ተወላጆች ላይ ለደረሰው ጥቃት ተጠያቂ ነው" ይላል።

ማኅበሩ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ "የአማራ ተወላጆች ላይ ጭፍጨፋ እየተፈፀመ ያለው በአፓርታይዱ ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ምክንያት ነው። ሥርዓቱ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት 1990ዎቹ ጀምሮ የአማራ ተወላጆችን አናሳ አድርጓል" ብሏል።

ባለፈው ታኅሣሥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚል ብሔራዊ የምክክር ኮሚቴ እንዲቋቋም ሕግ ማውጣቱ ይታወሳል።

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጥቃት እየፈፀመ ያለው የዚህ ብሔራዊ ምክክር አካል ለመሆን ነው ይላሉ።

ጃል መሮ በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አዛዥ ኩምሳ ድሪባ በቅርቡ "ሃቀኛ ውይይት ካለ" ለመሳተፍ ዝግጁ ነን ሲል ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

"ሁሉም ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ካልሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ሊኖር ይችላል" ሲልም አስጠንቅቋል።

አቶ ሆነ ግን ችግሩ የሚመነጨው ከሕገመንግሥቱ ነው የሚል እምነት አላቸው።

"ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእኩል ዐይን የሚታዩበት ሕገመንግሥት ያስፈልገናል። ሕገመንግሥቱ መሻሻል አለበት።"

የሚጠቀሙበት መሳሪያ ይህንን ምስል ላያሳይ ይችላል

የጥቃቱ ሰለባዎች

በጥቃቶቹ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በውል አይታወቅም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በሰኔ 11ዱ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 338 ነው ቢልም በአሜሪካን የአማራ ማኅበርን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች ቁጥሩ ከአንድ ሺህ ይልቃል ይላሉ።

ማኅበሩ እንደሚለው ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት [2021] ብቻ 213 ጥቃቶች የአማራ ተወላጆች ላይ ተፈፅመዋል።

"በእነዚህ ጥቃቶች ቢያን 3308 ሰዎች ተገድለዋል። አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የተፈፀሙት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው። 124 ጥቃቶች ቀጥታ የተፈፀሙት በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ነው። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ጥቃት ፈፅመዋል" ይላሉ አቶ ሆነ።

በኦሮሚያ ክልል የሌሎች ብሔር ተወላጆችም ጥቃት ደርሶባቸዋል።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ኦሮሞ ሌጋሲ ሊደርሺፕ ኤንድ አድቮኬሲ ማኅበር መሥራች ሴና ጂምጂሞ እንደምትለው "ባለፉት አራት ዓመታት ከ3 ሺህ በላይ የኦሮሞ ተወላጆች ተገድለዋል።"

ቢቢሲ እኒህን ግድያዎች ማጣራት አልቻለም። መንግሥትም ሆነ ኢሰመኮ እነዚን ቁጥሮች በተመለከተ ያወጡት የተጣራ መረጃ የለም።

ለፍርድ የቀረበ አለ?

ቢቢሲ ለእነዚህ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ተጠያቂ ሆኖ ለፍርድ የቀረበ አካል ስለመኖሩ የሚያሳይ መረጃ አላገኘም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ እንደራሴዎች እንደተናገሩት ከሆነ በርካታ የፓርቲያቸው አባላት በኦሮሚያ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ተባረዋል።

ለተባበሩት መንግሥታት ለ30 ዓመታት ያክል ያገለገሉት አቶ ባይሳ የመንግሥት ዋነኛ ሥራው የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ ነው ይላሉ።

አክለው ባለሥልጣናት ይህን ማስጠበቅ እንዳልቻሉ ይገልጣሉ።

"ባለፈው ሳምንት ለተፈፀመው ጥቃትም ሆነ፣ ባለፈው ዓመት በየትኛውም ሥፍራ ለተፈፀሙት ጥቃቶች ተጠያቂው መንግሥት ነው።"

ጨምረውም "ጥቃቶቹ ብሔር ተኮር መሆናቸው ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ" ይላሉ።

"ለምሳሌ በቶሌም ሆነ ጉሊሶ በተፈፀመው ጥቃት የተገደሉት የአማራ ተወላጆች ናቸው። ጥቃት የደረሰባቸውም በብሔራቸው ምክንያት ነው።"

ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ተኮር ጥቃቶች መበራከታቸውን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ የማኅበረሰብ አንቂዎች ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል የሚል ድምፅ ማሰማት ጀምረዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብቷል?

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመራው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው ጥቃት እንዳሳሰበው ገልጧል።

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ዓለም አቀፍ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ዓለም ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውን ችላ እንዳይል አሳስበዋል።

"በጥላቻ ንግግር ታጅቦ እየተስፋፋ ያለው አለመረጋጋትና ብሔርና ፆታ-ተኮር ጥቃት ወደፊት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከባድ አደጋ እንደሚመጣ ማሳያ ነው።"

የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ በቅርቡ የተፈፀሙትን ጥቃቶች የሚያጣራ ምርመራ እንደሚያካሂድ መግለጹ ይታወሳል።

ይህ ሁሉ እየሆነ ሳለ አቶ ሞሐመድ እና ሌሎች ከጥቃት የተረፉ ዜጎች ጥቃቱን የፈፀሙ ለፍርድ እስኪቀርቡ ከመጠበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ ያላቸው አይመስልም።

"ጭንቅላቴ ማሰብ ተስኖታል" ይላል አቶ ሞሐመድ እንባ በተናነቀው ድምፅ።

*ስማቸው ተቀይሯል።