የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ሸኔ የፈጸማቸው ጥቃቶች ምን ያመለክታሉ?

መንግሥት ሸኔ የሚለው እና በሽብርተኝነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባ ሦስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
የፌደራሉ እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ሰላም እንዲያወርዱ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ባለመሳካታቸው ወደ ጦርነት ገብተዋል።
በመንግሥት በኩል የተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎች ተደርገው፣ ታጣቂ ቡድኑ የአገሪቱ የደኅንነት ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል ቢባልም፣ ሰሞኑን የፈፀማቸው ጥቃቶች ግን የመንግሥትን እርምጃ ስኬታማነትን ጥያቄ ላይ ጥሎታል።
ባለፈው ሳምንት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር በመሆን በጋምቤላ ከተማ ጥቃት ከፍቶ ከ40 በላይ የሰው ሕይወት መጥፋቱ ይታወሳል።
በተመሳሳይ ዕለትም በቄለም እና ምሥራቅ ወለጋ፤ ደምቢዶሎ እና ጊምቢ ከተሞችም ጥቃት በመክፈት “የተሳካ ኦፕሬሽን” ማካሄዱን ገልጾ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም ቅዳሜ፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ ጥቃት ፈጽሞ ሴቶችና ህጻናት የሚገኙባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው ተገልጿል።
ነገር ግን ቡድኑ ጥቃቱን የፈፀመው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ያደራጀው፣ ለየት ያለ የሚሊሻ ቡድን መሆኑን በመግለጽ ጥቃቱ ሲፈፀም ሠራዊቱ በአካባቢው እንዳልነበር ገልጿል።
አክሎም ገለልተኛ በሆነ ወገን ምርመራ እንዲካሄድም ጥያቄ አቅርቧል።
ቡድኑ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ነው?
የኦሮሚያ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ከሳምንታት በፊት የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት ጀምረውት የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻ አስመልክቶ መግለጫ ሲሰጡ፣ የታጣቂው ቡድን የአገሪቱ ደኅንነት ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀው ነበር።
ብሔራዊ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በገመገመበት ጊዜ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ከሺህ በላይ ታጣቂዎች መገደላቸውን እና ዘመቻውም የተሳካ እንደነበር ገልጿል።
የጋምቤላው፣ ደምቢዶሎ እና የጊምቢ ጥቃትም ከእነዚህ መግለጫዎች በኋላ የተከሰተ ነው።
ከቶሌ ቀበሌ ጥቃት በፊት ያነጋገርናቸው የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ “በስፍራው የሚገኙ የመንግሥት አካላት [ለተከፈተው ጥቃት] እርምጃ መውሰዳቸውን ነው የማውቀው” በማለት ስለሰሞኑ ጥቃት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በጊምቢ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ቀበሌዎች ተኩስ ተከፍቷል። ልክ እንደ ደምቢዶሎ እና ጋምቤላ ሁሉ ተኩስ መክፈት ነበር። ግን እርምጃ ተወስዶባቸው ከተሞቹ ወደ ሰላማቸው ተመልሰዋል” ብለው ነበር።
ታጣቂ ቡድኑ ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል ከተባለ በኋላ የዞን እና የክልል መቀመጫ የሆኑ ከተሞችን ገብቶ ጥቃት መፈፀሙ እንዴት ይታያል ተብለው ለተጠየቁት አቶ ከበደ ሲመልሱ “እኔ መንግሥት ታጣቂዎችን አጥፍቷቸዋል የሚል መረጃ የለኝም” ብለዋል።
“. . .እርምጃ እየወሰድን ነው፤ ለአገር ደኅንነት ስጋት ሆነዋል። ለዚህም ነው በአዲስ መልክ እርምጃ እየወሰድን የምንገኘው።”
የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት ኦዳ ተርቢ፣ ዘመቻዎቹን አስመልክቶ መንግሥት እያቀረበው ያለው ሪፖርት “የተለመደው ፕሮፓጋንዳ ነው” ሲሉ አጣጥለው አካባቢዎቹን “በስትራቴጂ” መልቀቃቸውን ተናግረው ነበር።
‘ወደ ከተሞችም እየገባን ነው’
የኦሮሞ ነጻነት ጦር አዛዥ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉበት የቶሌ ወረዳ ጥቃት በፊት ለቢቢሲ እንደተናገረው “አሁን፣ በረሃዎችን እና ገጠሮችን ብቻ ሳይሆን ጥበቃ ያላቸው ከተሞችም እየገባን ነው፤ የፖለቲካ ሰዎችን አስታጥቀው ቢያዘምቱም ጥበቃቸውን እያለፍን ነው” ሲል ተናግሯል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ታጣቂ ቡድኑ የጋምቤላ፣ የደምቢዶሎ እና የጊምቢ ከተሞችን የማጥቃታቸውን አስፈላጊነት ሲገልፁ፣ “አጥፍተናቸዋል የሚለውን የመንግሥትን ሐሰተኛ መረጃ እና ከፖሊስ በነጠቁት ያረጀ መሳርያ ነው የሚዋጉት ለሚለው [ፕሮፓጋንዳ] መልስ እንዲሆን ነው” ይላል መሮ።
የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር በመሆን በጋምቤላ ከተማ ላይ ከከፈቱት ጥቃት ጋር በተያያዘ 40 የሚሆኑ ግለሰቦች መገደላቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ ማረጋገጥ ችሎ ነበር።
ኩምሳ ድሪባ ይህንን አስመልክቶ ሲናገር፣ በጦርነት በኩል መቁሰል እና መሞት ቢኖርም የደረሰው ጉዳት “የተባለውን አይደለም” ሲል ያስተባብላል።
“እኛ ከተማይቱን ተቆጣጥረን በፈለግነው ሰዓት የፈለግነውን ፈጽመን ወጥተናል። ምን ፈጽማችሁ የሚለውን መግለጽ አያስፈልግም” ሲልም አክሏል።
በተመሳሳይ ዕለት በተለይ በደምቢዶሎ ከተማ የመንግሥትን ኃይሎች ከሦስት ካምፖች ማባረር መቻላቸውን ኩምሳ ድሪባ ይናገራል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች፣ ታጣቂዎቹ ደምቢዶሎ ከተማ ማለዳ ከገቡ በኋላ ወደ ሆስፒታል አምርተው መድኃኒቶችን ጭነው መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር ዴታው አቶ ከበደም፣ ከተማ ውስጥ ገብተው ተኩስ መክፈታቸውን አረጋግጠዋል። የመንግሥት ታጣቂዎችም እርምጃ እንደወሰዱ ተናግረዋል።
የታጣቂው ቡድን ዝርፊያ እና ግድያ እየፈፀመ ሕዝቡ እንዳያርስ እያደረገ ስለሆነ፣ መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል።
ጃል መሮ ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ “ሆስፒታል ገብተን ቁስለኞቻችንን አክመን ወጣን እንጂ ጭነን የወሰድነው መድኃኒት የለም” ይላል።
የመከላከያ ሠራዊትን በሁሉም ስፍራ ማሰማራት ስለማይቻል፣ ሕዝቡ በዚህ በኩል የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ጠይቀዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተጋጋለበት ጊዜ ይህ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በምሥራቅ ወለጋ፣ ቤጊ እና ጊዳሚ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ነበር።
ታጣቂዎች ከተሞች ገብተው መውጣታቸው፣ ለሕዝቡ ሰላም ስጋት አይሆንም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ምላሽ ሲሰጡም “አሁን ሕዝቡን ይዘናል፤ መሬቱንም ሕዝቡንም የምንይዝበት ጊዜ አለ” ብለዋል።
“ያለነው በጦርነት ውስጥ እንጂ ጭፈራ ቦታ ወይንም የእምነት ቤት አይደለም፤ በአንድ ሌሊት አገር መያዝ አይቻልም። እርምጃችንም በዚሁ ሂደት ውስጥ ያልፋል፤ ጦርነት ሞት እና መፈናቀልን ያዘ መሆኑ ይታወቃል” ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ታጣቂዎቹ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በሁለት ጦር መካከል ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ለቢበሲ ሲገልፁ ነበር።
መንግሥትም፣ ሲከሰቱ ለነበሩት ግድያዎች እና መፈናቀሎች፣ በሽብርተኝነት የፈረጀውን ይህንን ታጣቂ ቡድን ሲከስ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚፈልገው ምንድን ነው?
የኦሮሞ ነጻነት ጦር እና ግንባር በጋራ በ1976 (እኤአ) በወቅቱ የነበረውን ሥርዓት በመቃወም ነጻ አገር ለመመስረት በሚል ነበር የተቋቋሙት።
የኦሮሞ ነጻነት ጦር፣ የግንባሩ የጦር ክንፍ ሆኖ ላለፉት 50 ዓመታት “ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት” ከተለያዩ ሥርዓቶች ጋር በትጥቅ ሲፋለም ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አመራሩን በዋነኛነት ኤርትራ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ክንፍ፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ቤት ተመልሷል።
በአገር ውስጥ ታጥቆ የነበረው ኃይል ግን የትጥቅ ትግልን የሙጥኝ በማለቱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በይፋ ከጦሩ ራሱን መነጠሉን እንዲያሳውቅ አድርጓል።
የኦሮሞ ነጻነት ጦር መሪ፣ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) “ዓላማችን የፖለቲካም የጦርም ግፊት የማይደርስበት የኦሮሞን ሕዝብ ነጻነትን ማረጋገጥ ነው፤ ነጻ እና ራሱን የቻለ ኦሮሞ እና ኦሮሚያን ለመመስረት እና የራስን እድል በራስ ለመወሰን ነው” ይላል።
እንዲሁም “ኢትዮጵያ ውስጥ መጨቆን ቀርቶ፣ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በእኩልነት መኖር እፈልጋለሁ ካለም [የኦሮሞ ሕዝብ] እርሱን ለማስከበር እንታገላለን።”
የሰላም እድል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ሲወያዩ፣ ህወሓትን ጨምሮ በትጥቅ ትግል ከሚታገሉ የትኛውም አካላት ጋር በውይይት ችግሮችን ለመፍታት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀው ነበር።
የመንግሥት ኮሙኑኬሸን ጉዳዮች ቢሮ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ከበደም፣ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለስ እንፈለጋለን ብለዋል።
“የኦሮሞ ሕዘብ ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ አልቋል የሚል እምነት ባይኖረኝም ጥያቄዎቹን በሰላማዊ መንገድ ማንሳት ይቻላል” ይላሉ።
“ወደ ምሥራቅ ኦሮሚያ ያሉ ሕዝቦች፣ በአብዛኛው እያረሱ አይደለም። ቡናም እየሰበሰቡ አይደለም። ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስም አስቸጋሪ ነው። ዝርፊያ እና ንብረት ማቃጠል በዝቷል። ስለዚህ መንግሥት ሰላም ለማውረድ ትልቅ ፍላጎት አለው” ብለዋል።
ጦሩ ወደ ሠላማዊ መንገድ ለመምጣት ዝግጁነት እንዳለው የተጠየቀው ጃል መሮ፣ “እንደ ሕጻን ልጅ በትንሽ ነገር ተደልሎ የሚገባ ኃይል የለም። የምንፈልገው ነገር አለ። እርሱን ትተን እጅ የምንሰጥበት ምክንያት የለም” ሲል መልሷል።
አክሎም “እኛ በመረጥነው ስፍራ መንግሥትም እኛም ይሆንልናል በምንለው ሰው፣ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት ጥሪ የሚቀርብልን ከሆነ፣ ለድርድር ዝግጁ ነን” ብሏል።
ከዚህ ውጪ “እንደ ልጅ በከረሜላ ደልሎ የሚጠሩን ከሆነ የሚሞኝ የለም።”
መንግሥት ሸኔ የሚለው ይህ ታጣቂ ቡድኑ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ በፈጸማቸው ተከታታይ ጥቃቶች ምክንያት ባለፈው ዓመት ከህወሓት ጋር ሽብርተኛ ቡድን መባሉ ይታወሳል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከህወሓት ጋር ግንኙነት አለው በሚል መንግሥት በተደጋጋሚ ሲከሰው የቆየ ሲሆን፣ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ተስፋፍቶ የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች ሲገቡ ሁለቱ ቡድኖች በጋራ መንግሥትን ለመውጋት እንደሚተባበሩ በይፋ አሳውቀዋል።












