በአሜሪካ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው የአልሻባብ መሪ በኢትዮጵያ ሠራዊት መገደሉ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, ENA
የሶማሊያ ታጣቂ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጥቃት ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃ ሦስት ከፍተኛ የአልሻባብ መሪዎች መገደላቸው ተገለጸ።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከተገደሉት የአልሻባብ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የአሜሪካ መንግሥት መገኛውን ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እከፍላለሁ ያለችው ኃላፊ ፉአድ መሐመድ ካህላፍ ይገኝበታል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት ስምሪት ኃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው፣ የአልሻባብ የቅስቀሳ እና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊ ፉአድ መሐመድ ካህላፍን ጨምሮ ሦስት የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሦስቱን ከፍተኛ የአልሻባብ አመራሮች መግደሉን ይፋ ማድረጉን በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከታጣቂው ቡድን በኩል የተባለ ነገር የለም።
ከፉአድ መሐመድ ካህላፍ በተጨማሪ የቡድኑ ቃል አቀባይ ነው የተባለው አብዱላዚዝ አቡ ሙሳ እና የባኩል ዞን እና የኢትዮጵያ ድንበሮች አዋሳኝ ኃላፊ ኡቤዳ ኑር ኢሴ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥቃት መገደላቸውን ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ፉአድ ሾንጋሌ በሚል መጠሪያ ስም ጭምር የሚታወቀው ፉአድ መሐመድ ካህላፍ የአልሸባብ መሪ መሆኑን እና ለጽንፈኛ ቡድኑ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይገልጻል።
አልሻብብ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊቱ በአየር ኃይል በመታገዝ በወሰደው እርምጃ ቡድኑ ለጥቃት የሚጠቀምባቸውን የትጥቅና ስንቅ ማከማቻዎች ማውደም እንደቻለ ጄነራሉ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀው እና ጎረቤት አገር ሶማሊያ በስፋት የሚንቀሳቀሰው አልሻባብ ባለፉት ቀናት በአዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች እና ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በመግባት ጥቃቶችን ሲፈጽም ነበር።
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እና የፌደራሉ መንግሥቱ ሠራዊት እስላማዊ ቡድኑ የከፈተውን ጥቃት መመከት መቻላቻውን ሲገለጽ ቆይቷል።
በተመሳሳይ ቡድኑ ዛሬም አርብ ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም. ጠዋት ለኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው አቶ ጥቃት መሰንዘሩን እና ውጊያ መካሄዱን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የሶማሌ ክልል ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. የሶማሊያው እስላማዊ ቡድን አልሻባብ ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኑት የሶማሊያ ከተሞች፣ አቶ እና ዬድ ላይ ጥቃት በመክፈት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ከባድ ጦርነት ማድረጉ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የቡድኑ ታጣቂዎች ከአንድ መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው በመግባት ጥቃት ሰንዝረው በሶማሌ ክልል እና በፌደራሉ ሠራዊት በተወሰደ እርምጃ ከሁለት መቶ በላይ አባላቱ መገደላቸውን መንግሥት ገልጿል።
አልሻባብን በሽብር ቡድንነት የፈረጀችው አሜሪካ፣ የአፍሪካ ወታደራዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ጄኔራል ስቲፈን ታውንሰንድ ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገሩት "ኢትዮጵያ ወደ ግዛቷ ዘልቆ የገባውን የአልሸባብ ኃይል ጥቃት ቀልብሳለች" ብለዋል።
ጄኔራሉ ጨምረውም ታጣቂው እስላማዊ ቡድኑ አሁን ያሰበው ቢጨናገፍበትም በቀጣዮቹ ወራት ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሊፈጽም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።












