አልሻባብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰነውን የድንበር ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ አጠቃ

የፎቶው ባለመብት, AFP
አልሻባብ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰነው የሶማሊያዋ የድንበር ከተማ አቶ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ አርብ ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም. ጠዋት ጥቃት መፈጸሙን አንድ ባለሥልጣን ለቢቢሲ አረጋገጡ።
አልሻባብ ከአንድ ሳምንት በፊት በዚህችው የድንበር ከተማ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች ጋር መዋጋቱ ይታወሳል።
ቡድኑ ዛሬ አርብ ጠዋት ለኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው አቶ ላይ በሁለት ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ጥቃት መሰንዘሩን እና ውጊያ መካሄዱን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የሶማሌ ክልል ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዛሬ ወደ አቶ ዘልቆ ጥቃት የመፈጸም ዓላማ የነበረው የአልሻባብ ታጣቂ ኃይል፤ ያሰበው ሳይሳካ ሽንፈት እንዳጋጠመው ባለሥልጣኑ ጨምረው ተናግረዋል።
በግጭቱ በአካባቢው ተሰማርተው በነበሩት የፀጥታ ኃይሎችና በአልሻባብ ታጣቂዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ያመለከቱት ባለሥልጣኑ፣ በአሁኑ ወቅት ዝርዝር ሁኔታውን መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. የሶማሊያው እስላማዊ ቡድን አልሻባብ ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኑት የሶማሊያ ከተሞች፣ አቶ እና ዬድ ላይ ጥቃት በመክፈት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ከባድ ጦርነት ማድረጉ ይታወሳል።
ከዚያም ባኩል ከተሰኘችው የሶማሊያ ግዛት የተነሱ እና በበርካታ ተሽከርካሪዎች የተጫኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ ታጣቂዎች ወደ የኢትዮጵያ ግዛት አፍዴር ዞን ከገቡ በኋላ ውጊያ መደረጉንና በርካታ የአልሻባብ አባላት መገደላቸውን የክልሉ መስተዳደር ገልጾ ነበር።
በተጨማሪም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሰርገው ከገቡ የአልሻባብ ታጣቂዎች ጋር በተከታታይ ቀናት በተደረጉ ውጊያዎች ከሁለት መቶ በላይ የቡድኑ ተዋጊዎች ሲገደሉ፣ በርካታ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኑኬሽን ጽህፈት ቤት አመልክቷል።
አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር በጎረቤት አገራት ውስጥ ጥቃቶችን ሲፈጽም የቆየ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ላይ ግን ከሙከራ የዘለለ ጥቃት ለመፈጸም ሳይችል ቆይቶ ነበር። ባለፈው ሳምንት ግን ባልተለመደ ሁኔታ ተዋጊዎቹን በድንበር በኩል በማስገባት ጥቃት ሰንዝሯል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ቡድኑን በሽብርተኛነት የምትመለከተው አሜሪካ፣ የአፍሪካ ወታደራዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ጄኔራል ስቲፈን ታውንሰንድ ለአሜሪካ ድምጽ ኢትዮጵያ ወደ ግዛቷ ዘልቆ የገባውን የአልሸባብ ኃይል ጥቃት መቀልበሷን ገልጸው፣ ታጣቂው ቡድን ግን በቀጣዮቹ ወራት ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሊፈጽም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ቡድኑ የጥቃቱ ኢላማ ያደረጋቸው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች ባሉ የድንበር ቦታዎች ላይ ሲሆን፣ ቀደም ባለው እና በአሁኑ ጥቃት በሁለቱም ወገኖች ላይ ጉዳት መድረሱን የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።
ይህን በአልሸባብ የተከፈተውን ጥቃት ለመከላከል ተጨማሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ መሰማራቱን የሶማሌ ክልል መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።
አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀስ ታጣቂ እስላማዊ ቡድን ሲሆን፣ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል። ቡድኑ በሶማሊያ ውስጥ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ በርካታ የቦምብ እና የደፈጣ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።
አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር በኬንያ ውስጥ ተደጋጋሚ ከባድ የሽብር ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን፣ ጥቃቱ እስከ ኡጋንዳ ድረስ የዘለቀ ነው።
አልሻባብ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም በተደጋጋሚ ሲዝት የቆየ ቢሆንም ከሙከራ ያለፈ ጥቃት አድርሶ አያውቅም። አሁን ታጣቂዎቹ እየፈጸሙት ያለው ጥቃት ያልተጠበቀ ነው።
አልሻባብ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አስርጎ ያስገባቸው ታጣቂዎቹ የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በወሰደው እርምጃ ወደ 200 የሚጠጉ የቡድኑ አባላት መገደላቸው ተገልጿል።
ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ለሮይተርስ እንደተናገረው በፈጸመው ጥቃት ከ80 በላይ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላትን ገድያለሁ ብሎ ነበር።












