ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን አልተመለሱም ስለተባሉ ኤርትራውያን እስካሁን የሚታወቀው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ ኦሪገን ተጉዘው ጠፍተዋል ከተባሉ 5 ኤርትራውያን አትሌቶች መካከል ሦስቱ ለውድድር ወደ ሌሎች አገራት መሄዳቸውን ተነገረ።
በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ ከሄዱት የኤርትራ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አባላት መካከል ወደ አገራቸው ያልተመለሱ ስለመኖራቸው ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ ተዘግቧል።
ቀደም ሲል የኦሪገን ግዛት ፖሊስ የአምስት የአትሌቲክሱ ቡድን አባላት ስም ዝርዝርን በማውጣት የደረሱበት አልታወቀም ብሎ አሳውቆ ነበር።
ይሁን እንጂ ኬፒቲቪ፣ ሪጅስታር-ጋርድ እና ኬዚ የተሰኙ የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ጠፍተዋል ተብለው የነበሩ አትሌቶች ተገኝተዋል ሲል የኦሬገን ዩኒቨርሲቲ ፖሊስ ገልጿል በማለት ዘግበዋል።
እንደ የአካባቢው ሚዲያዎች ዘገባ ከሆነ፤ የአትሌቶቹን አድራሻ አግቻለሁ ብሎ ለኦሪገን ዩኒቨርሲቲ ፖሊስ ያስታወቀው የኤርትራ ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው።
ዘገባዎቹ ይህን ይበሉ እንጂ አሁንም የአምስቱ ኤርትራውያን ስም በኦሬገን ግዛት ፖሊስ ድረ ገጽ ላይ አድራሻቸው በጠፉ ግለሰቦች ዝርዝር ላይ ይገኛል።
በግዛቷ ፖሊስ ድረ ገጽ ላይ አድራሻቸው አይታወቅም ተብሎ ስማቸው የተዘረዘሩት ኤርትራውያን በሙሉ ጾታቸው ወንድ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ አስልጣኝ ነው።
የ44 ዓመቱ አሰልጣኝ በርሄ አስገዶም፣ ፊልሞን አንደ፣ ሃብቶም ሳሙኤል፣ መርሃዊ መብርሃቱ እና የማነ ኃይለሥላሴ በድረ ገጹ ላይ ጠፍተው እየተፈለጉ ካሉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተው ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, LIVINGSTON ABRHAM
ኮሎምቢያ እና ስዊዘርላንድ
አድራሻቸው አይታወቅም ተብሎ ስማቸው ከረዘረዘሩት ኤርትራውያን አትሌቶች መካከል ሁለቱ፤ ማለትም መርሃዊ መብርሃቱ እና ሃብቶም ሳሙኤል ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ ለመሆን ወደ ኮሎምቢያ ማቅናታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የ18 ዓመት ወጣት የሆኑት ሁለቱ አትሌቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ትሻምፒዮና ላይ በ3 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር ውድድሮች እንደሚሳተፉ በይፋዊ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ሰነድ ላይ ስማቸው ተዘርዝሯል።
ጠፍተዋል ከተባሉ አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው የማነ ኃይለሥላሴ ደግሞ ለሌላ ውድድር ወደ ስዊትዘርላንድ ማቅናቱን ለቢቢሲ ተናግሯል። ቢቢሲም የአትሌቱ የጉዞ ሰነድና ቪዛን ተመልክቷል።
የዳይመንድ ሊግ አካል በሆነው እና በስዊትዘርላንድ ሎውዛን ከተማ በሚደረገው ውድድር ላይ ለመሳትፍ ወደ ስፍራው እንደሚያቀናም አትሌት የማነ ተናግሯል።
ቀደም ሲል የኦሬገን ፖሊስ አድራሻቸው ጠፍቷል ካላቸው ልዑካን ቡድን አባላት መካከል የአሰልጣኝ በርሄ አስገዶም እና ፊሊሞን አንደ ያሉበት አልታወቀም።
ኤርትራ 10 አትሌቶች በአራት ውድድሮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ወደተጠናቀቀው 18ኛው ኦሬገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ልካ ነበር።
በውድድሩ ላይ የማነ ኃይለሥላሴ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል 7ኛ ሆኖ አጠናቋል። መርሃዊ መብራቱ በ5ሺህ ሜትር ማጣሪያውን ሳያልፍ የቀረ ሲሆን ሃብቶም ሳሙኤል በ10 ሺህ ሜትር 17ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ፊልሞን አንደ ደግሞ በማራቶን ለለመወዳደር ተመዝግቦ ነበር።












