የመንግሥትና የህወሓት ድርድር ከኬንያ ምርጫ በኋላ ሊጀመር ይችላል ተባለ

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ንግግር በነሐሴ ወር ሊጀመር ይችላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘገበ።
ባለሥልጣኗ ሞሊ ፊ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት በሽምግልና ለመፍታት ቁልፍ ሚና አላት ባሏት ኬንያ ውስጥ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ድርድሩ እንደሚጀመር ጥንቃቄ የተሞላበትን ተስፋቸውን ለአገራቸው ምክር ቤት ኮሚቴ መናገራቸውን ኤኤፍፒ አመልክቷል።
ኬንያ ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም. ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
አሜሪካ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና ኬንያ ጦርነቱን ለማስቆም ውይይት እንዲደረግ የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርጉም ጦርነቱ ቀጥሎ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አስከትሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት አመራሮች ጋር የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ኅብረት መሪነት እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳለው አሳውቆ የነበረ ሲሆን፣ አማጺያኑ ግን ንግግሩ በኬንያው መሪ ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪነት እንዲካሄድ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ሞሊ ፊ፤ ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ እንዳስረዱት፤ በኬንያ ሊካሄድ የተቃረበው ምርጫ በድርድሩ የጊዜ ሰሌዳ ላይ መዛባትን ሳይፈጥር እንዳልቀረ ገልጸዋል።
ባለሥልጣኗ ጨምረውም ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በተለያዩ አገራት ጉብኝታቸውን የጀመሩት አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር “ድርድሩ ወደፊት እንዲራመድ አሜሪካ ምን ማድረግ እንደምትችል ከሁለቱም ወገኖች ጋር ይወያያሉ” ሲሉ ለኮሚቴው ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተክትሎ ጦርነቱ በተፋፋመበት አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለቱም ወገኖች ለመደራደር ፍላጎት እንደሌላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ጋብ ካለ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል በተዘዋዋሪ መንገድ ንግግር እየተካሄደ መሆኑን ከተለያዩ ምንጮች ሲነገሩ ቢቆዩም ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይታይ አስካሁን ቆይቷል።
የኋላ የኋላ ግን በሁለቱም ወገኖች በኩል ጦርነቱን በድርድር ለመቋጨት ፍላጎት እናዳለ በይፋ ተናግረው ለውይይት በር በመክፈታቸው ጥረቶች እየተካሄዱ ነው።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከመንግሥት ጋር ለሚያደርገው ድርድር ቅድመ ሁኔታ እና የጊዜ ገደብ እንደተቀመጡ ተናግረዋል።
ከድርድሩ በፊት በትግራይ ክልል ተቋርጠው የሚገኙት መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ መጀመር እንዳለባቸው በመግለጽ፣ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ የማይጀመሩ ከሆነ ግን ጦርነት እንደሚጀመር ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል።
ሐሙስ ዕለት ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከአውሮፓ ኅብረት እና ከሌሎች ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ጋር የተወያዩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በየትኛውም ስፍራ፣ በማንኛውም ጊዜ እና ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአምባሳደሮቹ እና የልዩ መልዕክተኞቹ ቡድን ወደ መቀለ እንዲጓዝ መንግሥት መፍቀዱንም የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።
ይህንን በፌደራል መንግሥቱ በኩል ለድርድር ያለቅድመ ሁኔታ ዝግጁ መሆኑን ካስታወቀ በኋላ ከህወሓት አመራሮች በኩል እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ጦርነቱን ተከትሎ አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ስታሳርፍ የነበረች ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ባለሥልጣንት ላይ የቪዛ እቀባን እንዲሁም አገራት ሸቀጦችን ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ እንዲያስገቡ ከሚፈቅደው የአጎዋ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያ እንድትወጣ አድርጋታለች።
ይህንን የአሜሪካን እርምጃ በርካታ ሰዎችን የቀጠሩ አምራች ተቋማትን የሚጎዳ ነው በሚል ኢትዮጵያ አጥብቃ ብትቃወመውም እግዱ ተግባራዊ ከሆነ ወራት ተቆጥረዋል።
የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ሞሊ ፊ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ባብራሩበት ወቅት የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገድን እያጤነው መሆኑን ተናግረዋል።
የጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ አንጻር ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት እንድትመለስ ለማድረግ የተሻለ ሁኔታ መኖር አለመኖሩን “በቅርበት እያጤነ ነው” ሲሉም ፊ ገልጸዋል።












